አርዕስተ ዜና

ቀስቃሽ - ተቀባይ - ሸኚ = የዘመናዊው ባርነት ሰንሰለት

ከእንግዳ መላኩ /ኢዜአ/

የሰው ልጅ ጾታ፣ ዘር፣ ኃይማኖት፣እድሜና ቀለም ሳይገድበው ሰው በመሆኑ ብቻ ለሰው ልጆች ሁሉ ሰብአዊ ርህራሔ አለው፡፡ ያንዱ ቁስል ሌላውን ያመዋል፤ ረሃብ ጥሙ ያሳስበዋል፡፡ በአንደኛው የዓለማችን ጥግ በሰው ሰራሽም ይሁን በተፈጥሯዊ አደጋ ምክንያት በሰዎች ላይ ጉዳት ሲደርስ በሌላው የዓለማችን ጥግ ያለው ሰው ያዝናል፤ ሀዘኑንም በተለያየ ምክንያት ሲገልጽ ይስተዋላል፡፡

የዛሬ ሰባት ዓመት ገደማ አታካማ በረሃ ውስጥ ማዕድን በማውጣት ስራ ላይ በነበሩ 33 የቺሊ ዜጎች ላይ በደረሰው አደጋ ያልደነገጠና ያላዘነ አልነበረም፡፡ ማዕድን ቆፋሪዎቹ 700 ሜትር ጥልቀት ባለው ጉድጓድ ውስጥ እያሉ መሬት ቢጫናቸውም በሕይወት መኖራቸው በተሰማ ጊዜ ደግሞ ዓለማችን ቴክኖሎጂዋን፣ እውቀት ክህሎቷንና ጉልበቷንም ጭምር አፍስሳ ሰዎቹን በ69ኛ ቀናቸው ከተቀበሩበት በሕይወት አውጥታቸዋለች፡፡ ይህ የሰው ልጅ ለወገኑ ጥልቅ ሰብዓዊነትን ያሳየበት የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው፡፡

ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት በተለይ በሀገራችን ሰሜናዊ ክፍል  ተከስቶ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችንን የፈጀው አስከፊ ረሀብ ሌላው የዓለማችን ሰብዓዊነት ጎልቶ የወጣበት የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው፡፡ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት የቢቢሲ ጋዜጠኞች ቡድን ለዓለማችን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ እንግሊዛውያን በአየር ኃይላቸው አማካኝነት ለተጎጂዎቹ የምግብ እርዳታ ለማቅረብ ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡ ስዊድን፣ ምዕራብና ምስራቅ ጀርመን፣ ፖላንድ፣ ካናዳ፣ አሜሪካና የያኔዋ ሶቪየት ህብረት በረሀብ አለንጋ ክፉኛ እየተሰቃየ የሚያልቀውን ህዝብ ለመታደግ ተረባርበዋል፡፡

አየርላንዳዊው አቀንቃኝ ቦብ ጊልዶፍም መረጃውን እንደሰማ የእርዳታ ባንድ አቋቁሞ “Do they know it’s Christmas?”  በሚል ርዕስ ያወጣው ነጠላ ዜማ 3.67 ሚሊዮን ኮፒ ተሸጧል፡፡ “We are the world” እንዲሁም “USA for Africa” በሚሉ ርዕሶች በተከታታይ ያወጣቸው ነጠላ ዜማዎችም 20 ሚሊዮን ኮፒ ተሸጦ ገቢው ለተጎጂዎቹ እንዲደርስ ተደርጓል፡፡ ይሄን ያህል ኮፒ የተሸጠው የዓለም ህዝብ ለተጎጂዎቹ ለመድረስ በነበረው ፍላጎት እንጂ በሙዚቃዎቹ ጥልቅነትና በሰዎች የሙዚቃ ፍቅር ብቻ አለመሆኑን ልብ ማለት ያሻል፡፡

በርእደ መሬትና መሰል ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ  አደጋዎች የሰው ልጅ በተጎዳ ጊዜ ሁሉ በየትኛውም የዓለማችን ጥግ ያለ ሰው ሀዘኑን ከመግለጽ ባለፈ ፈጥኖ በመድረስም አጋርነቱን ከማረጋገጥ ወደ ኋላ አይልም፡፡ ይህ ሰብዓዊ ፍጡር ሁሉ በሰብዓዊነቱ ብቻ የሚጋራው ስሜት ነው፡፡ ይሕ መሰሉ መተባበርና መደጋገፍ  የዓለማችን የትናንት፣ የዛሬና ምንአልባትም የነገም ጭምር የሰብዓዊነት መገለጫ ነው፡፡

አሁን አሁን ግን ብቅ ብቅ የሚሉ ከሰብዓዊነት ያፈነገጡ ተግባራት አይነትና መጠናቸው እየሰፋ መጥቷል፡፡ የሰው ልጅ ለገንዘብ ያለው ፍቅርና አመለካከት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለወጠ መምጣቱን ተከትሎ የገዛ ወገኑን ሳይቀር እንደ ተራ ሸቀጥ ሸጦም ለውጦ ገንዘብ ለማግኘት በህቡዕ መሯሯጥ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡

በሰው ልጅ ላይ የሚደርስን አደጋ ለማስወገድና ለመቀነስ የሚደረገው ጥረት እንዳለ ሆኖ የራስን ከርስ ለመሙላት ሲባል ብቻ የሌሎችን ህይወት አደጋ ላይ መጣልም እንዲሁ እየተለመደ መጥቷል፡፡

ቀስቃሽ - ተቀባይ -ሸኚ በሚል የተደራጀው ዓለም ዓቀፍ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰንሰለት ለበርካቶች ሞት፣ለአካላዊና ስነ ልቦናዊ ጥቃቶች ምክንያት ሆኗል፡፡ ሀገራት ይህን ሰንሰለት ለመበጠስና የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ከተቻለም ለማስወገድ ብሔራዊና ዓለማቀፍ ህግጋትን ደንግገው ቢንቀሳቀሱም ከዚህ ግባ የሚባል ለውጥ አላመጡበትም፡፡

አንደኛው ሲመለምል ሌላው እየተቀበለ፣ ሌላኛው ደግሞ በባህር፣በየብስና በአየር እየሸኘ ወገኖቹ ላይ በሚፈጽመው ጭካኔ የተሞላበት ‘ንግድ’ ኪሱን የሚያደልበው በዝቷል፡፡ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ከአደገኛ እጽዋትና ሀገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ቀጥሎ የሶስተኛነት ደረጃን ወደ መቆናጠጥም  ተሸጋግሯል፡፡

አትላንቲክን አቋራጩ የባሪያ ንግድ ከተወገደ 200 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይሁን እንጂ የንግድ ስርዓቱ አይነቱንና መልኩን ቀይሮ ዛሬም ድረስ ዘልቋል፡፡ ፍሪ ዘ ስሌቭ የተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚጠቁመው 27 ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎች ዛሬም ቢሆን  ከባርነት አልተላቀቁም፡፡

ከዚህም የዘርፉ ተዋንያን በየዓመቱ 32 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ያጋብሳሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ ደግሞ 15.5 ቢሊዮን ዶላሩ በኢንዱስትሪ የበለጸጉ ሀገራት ድርሻ መሆኑ ይነገራል፡፡  ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውሩ ከሚያስገኘው ትርፍ ውስጥ 10 ቢሊዮን ያህል ዶላሩ መጀመሪያ ላይ ከግለ ሰቦች ግብይት /”ሽያጭ” የሚገኝ ሲሆን ቀሪው  የጥቃቱ ሰለባዎች ከሚሰጡት ምርትና አገልግሎት የሚገኝ ነው፡፡ ይህ ዓለማችን እጆቿን አስተባብራም መቋቋም ያልቻለችው ሀቅ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ 

በተባበሩት መንግስታት የአደንዛዥ እጽና ወንጀል ቢሮ (UNODC)  ዋና ዳይሬክተር አንቶኒዮ ማሪያ  ኮስታ የባሪያ ንግድ ከእንግሊዝ ግዛቶች የተወገደበትን 200ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ባደረጉት ንግግር የንግድ ስርዓቱ ከመጥፋት ይልቅ አዲስ መልክ ይዞ እያቆጠቆጠ መምጣቱ አሳሳቢ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውበታል፡፡ “በህገ ወጥ መልኩ በሚዘዋወሩ ሰዎች ጉልበት የሚመረቱ ምርቶችንና አገልግሎቶችን በርካሽ ዋጋ እየሸመትን ለጉዳዩ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለናል” ሲሉም ወቀሳ አዘል መልዕክት አስተላልፈዋል፤ጉዳዩ ከእያንዳንዱ አይንና ጆሮ የተሰወረ አለመሆኑን በመጠቆም፡፡

ከዘመናዊው ባርነት ተጠቂዎች ውስጥ በተለይ ሴቶችና ልጃገረዶች ለሴተኛ አዳሪነትና ለወሲብ ጥቃቶች እንደሚዳረጉም ነው ዳይሬክተሩ ጨምረው የገለጹት፡፡ በህገ ወጥ የሰዎች የዝውውር መረብ የገቡት ወንዶች ደግሞ በማዕድን ማውጣት፣ በእንስሳት አደንና መሰል አደገኛና ብዙ ጉልበት በሚጠይቁ የስራ ዘርፎች እንዲሰማሩ እንደሚገደዱ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀልም ምስጢራዊም በመሆኑ ትክክለኛ መረጃዎችን ለማግኘት አዳጋች ቢሆንም ዓለም ዓቀፉ የሰራተኞች ድርጅት ግን ለጉልበት ብዝበዛ የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር 12.3 ሚሊዮን እንደሚደርስ አስቀምጧል፡፡ መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው ፍሪ ዘስሌቭ የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም ደግሞ ቁጥሩን ወደ 27 ሚሊዮን ከፍ ያደርገዋል፡፡

ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ካለፉት አስር ዐመታት ወዲህ እጅጉን በመስፋፋት ላይ ያለ ዓለም ዓቀፍ ወንጀል ሲሆን የዝውውሩ መነሻ፣ መተላለፊያና መዳረሻ ከመሆን ያመለጠ ሀገር አለመኖሩ ደግሞ  የችግሩን ዓለማቀፋዊነት አጉልቶታል፡፡  

ምንም እንኳን የተባበሩት መንግሥታት እኤአ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን በወንጀልነት የሚፈርጅ ስምምነት ቢያጸድቅና 110 አገራትም በፊርማቸው ቢያረጋግጡት ችግሩን ለመቆጣጠርና ለማስቆም አልተቻለም፡፡

በሕጉ መሰረት ተገቢውን ቅጣት የሚያገኙት ወንጀለኞች ጥቂቶች ብቻ ሲሆኑ አብዛኞቹ ተጠቂዎች ደግሞ ተገቢው እርዳታ አይደረግላቸውም ይላል በተባበሩት መንግሥታት የአደንዛዥ እጽና ወንጀል (UNODC) ቢሮ ይፋ ያደረገው ሪፖርት፡፡ ከዚህ ይልቅ በህገ ወጥ መንገድ ገብታችኋል፤ ህጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ የላችሁም በሚል ወከባ እንግልቱ በተጠቂዎቹ ላይ እንደሚበረታ ነው ሪፖርቱ የጠቆመው፡፡

ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ዘመናዊ ባርነት የሚል ቅጽል ስም ወጥቶለታል፡፡ የዝውውሩ መነሻም ሆነ መዳረሻ በተንኮል፣ በክፋት፣ ሸፍጥ፣ጭካኔና ራስ ወዳድነት የተሞላ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ የሚያልፉ ሰዎችም ለአካላዊና አዕምሯዊ ጉዳት የሚዳረጉበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡ ችግሩ ምትክ አልባ ህይወትንም ሳይቀር ያስከፍላል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያም የዚህ ችግር ሰለባ ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ ናት፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን በኬንያና ታንዛንያ አድርገው ደቡብ አፍሪካ ለመግባት ሞያሌን በመውጫ በርነት ይጠቀማሉ፡፡ የመን ለመግባት ጂቡቲንና ሶማሊያን እንዲሁም በሱዳን፣ሊብያና ግብጽ በኩል ወደ አውሮፓ ሀገራት ለመግባት የመተማን በር ይጠቀማሉ፡፡

ለዚህ ደግሞ ህገ ወጥ ደላሎች በገጠር ከተማው ተሰግስገው አምራቹን ኃይል በማይያዝ በማይጨበጥ ተስፋ እየሞሉ የችግሩ ሰለባ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ሀገራችን በነዚህ ህገ ወጥ ደላሎች ቀስቃሽነት በርካታ ዜጎቿ የዝውውሩ ሰለባ የመሆናቸውን ያህል የሱዳን፣ኤርትራና ጂቡቲ ተዘዋዋሪዎችም ሀገሪቱን እንደ መሸጋገሪያ ይጠቀሙባታል፡፡

የቤተሰብና የጓደኛ ግፊቶች፣ የደላሎች በአቋራጭ የመክበር ፍላጎት፣ ለውጭ ሀገራት የሚሰጠው የተዛባ አመለካከትና የመሳሰሉት ለህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መንስዔዎች ናቸው፡፡

ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በሀገር ላይ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተግዳሮቶችን ያስከትላል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ በችግሩ ሰለባዎች ላይ ከመነሻ እስከ መዳረሻና ከዚያም በኋላ የሚደርሰው እንግልትና በደል ልብ ይሰብራል፡፡ ተጓጓዦች በጉዞ ላይ እያሉ ሊደበደቡ፣ ሴቶቹ የወሲብ ጥቃት ሰለባ ሊሆኑ፣ወደ ባህር ሊወረወሩ አሊያም ደግሞ በረሃብና ጥም ህይወታቸውን ሊያጡ የሚችሉበት አጋጣሚ በጣሙን ሰፊ ነው፡፡

የካቲት 6 /2004 ዓ.ም 77 ኮብላዮች በዕቃ መጫኛ ኮንቴነር ተጭነው ወደ ጂቡቲ በመጓጓዝ ላይ ሳሉ አየር በማጣትና በመተፋፈግ እንድፎ ከተባለው አካባቢ ሲደርሱ የ11 ኢትዮጵያን ህይወት ማለፉን ማስታወሱ የአደጋውን አስከፊነት በግልጽ ያሳያል፡፡

ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በዜጎቻችን ላይ እያደረሰ ያለውን ችግር ለማስቆምና ለመከላከል ይቻል ዘንድ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ኢትዮጵያ መሰል ዓለም ዓቀፍ ወንጀሎችን ለመከላከል ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶችንና ህግጋትን ተቀብላለች፡፡ እነዚህ ህጎችና ስምምነቶች ደግሞ የሀገሪቱ ህግ አካል መሆናቸውን በህገ መንግስቱ አንቀጽ 9/4/ አካትታለች፡፡

የግንዛቤ ማጎልበቻ መድረኮችን ከማዘጋጀት፣ ዜጎች በሀገራቸው ሰርተው የሚለወጡበትን እድል ከመፍጠር፣ በተለያዩ ሀገራት ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ከመመለስና መሰል ጥረቶች ጎን ለጎን ህጋዊ እርምጃዎችንም እየተሰራ ነው፡፡

ሀገሪቱ ፊርማዋን ያስቀመጠችባቸውን ዓለም ዓቀፍ ህግጋትና ስምምነቶችን ከመተግበር በተጨማሪ በተለይ ከህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር በተያያዘ በህገ መንግስቷም ሆነ በወንጀለኛ መቅጫ ህጓ ግልጽና የማያሻሙ ድንጋጌዎችን አስፍራለች፡፡

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 18 (2) ማንኛውም ሰው በባርነት ወይም በግዴታ አገልጋይነት ሊያዝ እንደማይችልና ለማንኛውም ዓላማ በሰው የመነገድ ተግባር የተከለከለ መሆኑን በግልጽ አስቀምጧል፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀጽ 596-98 ደግሞ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ውጪ መውጣት፣ እንዲወጣ ማነሳሳትና እንዲሰደድ ማድረግ ወንጀል መሆኑን በግልጽ አስፍሯል፡፡

የፍትህ ተቋማት  ህጉን የማስከበሩን ሃላፊነት በመወጣት ላይ ናቸው፡፡ የጸጥታ አካላቱ በጋላፊ፣ አይሻ፣ ደወሌ፣ ቶጎጫሌ፣ ሞያሌ፣ መተማና ኩሙሩክ በረሃ የተጠናከረ ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎችን ለህግ የማቅረብና የጥቃቱን ሰለባዎች ደግሞ ወደየመጡበት የመመለስ ስራዎችን አከናውነዋል፡፡

በዚህ መሰሉ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ሲሳተፉ ተይዘው ህጋዊ እርምጃ ከተወሰደባቸው አዘዋዋሪዎች መካከል በረከት ዳንኤል ሂዶቶ አንዱ ነው፡፡ በረከት ነሀሴ 4/2007 ዓ.ም ግዛቸው ባሳ፣ በኋላ ወልዴ፣ደለለኝ ሀንሳዎ፣ ተሰፋአለኝ ታደሰ፣ መድን አረጀና ዱረቶ በዛ የተባሉ ሰዎችን ሆሳዕና ከሚገኘው ቤቱ ድረስ እንዲመጡለት አደረገ፡፡ ግለሰቦቹ ቤት ለእንቦሳ ብለው በሩን ሲያንኳኩ ቤት ለእንግዳ ብሎ ተቀበላቸው፡፡

በረከት ጊዜ ሳያባክን ከእንግዶቹ ጋር መደራደር፣ የማሳመኛና ማደፋፈሪያ ክህሎቱን ማውጣት ጀመረ፡፡ ተሳካለት! ከሶስቱ እንግዶቹ ከእያንዳንዳቸው አምስት ሺህ አራት መቶ፣ ከሁለቱ ከእያንዳንዳቸው አምስት ሺህ እንዲሁም ከአንደኛው አራት ሺህ በጠቅላላው 30 ሺህ 200 ብር ቤቱ ሰተት ብሎ ገባለት፡፡

በብዙ ድካምና ጥረት የተገኘውን ገንዘብ ያለምንም ድካም ኪሱ ካስገባ በኋላም ጊዜ ሳያባክን ስድስቱንም ግለሰቦች እየመራ ወደ ሱዳን ድንበር አደረሳቸው፡፡ ኮብላዮቹ የሱዳንን ድንበር እንደረገጡ በሱዳን ፖሊሶች ተያዙ፡፡ የስደት ህልማቸው ተቋጨ፡፡ ወደ መጡበትም ተመለሱ፡፡

በአካባቢው የሚገኘው የጸጥታ ኃይል ደግሞ አስፈላጊውን መረጃ አጠናቅሮ ህገ ወጥ አዘዋዋሪው የህግ ውሳኔ እንዲያገኝ መዝገቡን ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቀረበው፡፡ የፌደራል አቃቤ ህግ የኢፌዲሪ ወንጀል ህግ አንቀጽ 598/1/ን ጠቅሶ ግለሰቡ ህጋዊ ፈቃድ ሳይኖረው ኢትዮጵያውያንን ለስራ ወደ ሱዳን አስገብቷል የሚል ክስ መሰረተበት፡፡

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የቀረቡለትን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች መርምሮ ሰሞኑን በተከሳሹ ላይ የ20 ዓመት ጽኑ እስራትና የስምንት ሺህ ብር ቅጣት በይኖበታል፡፡

ይህን መሰሉ ህጋዊ እርምጃ ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎቹ ከተግባራቸው እንዲታቀቡ ሊያስተምር፣ የድርጊቱን ሰለባዎችም እንዳይታለሉ ሊመክር ይችል ይሆናል፡፡ ዓለም ዓቀፍ የቀስቃሽ - ተቀባይ-ሸኚ ሰንሰለቱ የሚበጠሰው ግን የሀገራት መንግሥታትና የጸጥታ አካላት በሚያደርጉት ቁጥጥርና ክትትል ብቻ ሊሆን እንደማይችል በግልጽ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ህገ ወጥ ደላላዎችም ሆኑ ኮብላዮች ከህብረተሰቡ ጋር እንደመኖራቸው መጠን እንቅስቃሴያቸው ሁሉ ከህብረተሰቡ ዓይንና ጆሮ የተሰወረ አይደለም፡፡

የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መዘዙ ቤታችን ድረስ ዘው ብሎ እስከሚገባና የቅርብ ወዳጅ ዘመዶቻችንን እስከሚነጥቀንም መጠበቅ የሚኖርብን አይመስለኝም፡፡ ድርጊቱን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ሁሉ መተባበር ከቻልን ሰንሰለቱን የመበጣጠሱ ጉዳይ የተራራ ያህል አይገዝፍምና ሁላችንም በጉዳዩ ላይ ልንረባረብ ይገባል፤ ቸር ይግጠመን ፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Last modified on Wednesday, 12 April 2017 19:28
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን