አርዕስተ ዜና

የሚሊየነሮች መነሻ--- መዳረሻ

6695 times

                                                                    ደሳለኝ ካሳ (ኢዜአ)

 

ሃና  ተስፋዬ   ትባላለች:: ተወልዳ  ያደገችው   በተለምዶ  ኳስሜዳ  ተብሎ በሚጠራው   አካባቢ  ነው፡፡  በማርኬቲንግ  የዲፕሎማ ምሩቅም ነች፡፡  በተማረችው   የሙያ  መስክ   ተቀጥራ ለመስራት መንከራተቱን ግን ልቧ አልፈቀደም፡፡ ከዚህ ይልቅ እውቀቷን የግል ስራ ፈጥራ ለመስራት ለመጠቀም ወሰነች፤ ተሳካላትም፡፡

የዛሬ አራት አመት ገደማ በ30 ሺህ ብር  ካፒታል  አንድ ሰራተኛ ብቻ ጨምራ  የቆዳ  ውጤቶችን  የማምረቱን ስራ አሃዱ  ብላ  ተያያዘችው ፡፡

የቆዳ ጃኬቶችን፣ ዋሌቶችን፣ ቦርሳዎችን   እያመረተች   በመሸጥ  የጀመረችው ቢዝነስ ከአንድ እጅ ጣቶች ባነሱ ዓመታት ውስጥ  ወደ  1 ነጥብ 2 ሚሊየን  ብር  ካፒታል  ከፍ   ብሎላታል፡፡ የሰራተኞቿን ቁጥርም  ወደ 13 አሳድጋለች፡፡

ሃና እንደምትለው ምርቶቿን ደንበኞቿ ይወዱላታል፤ ጥሩ የገበያ ትስስርም አላት፡፡ በቀጣይ የፋይናንስ ችግሯን በአበዳሪ ተቋማት አቃልላ ምርቶቿን ለውጭ ገበያ የማቅረብ ህልም የሰነቀችው ሃና “በመንግስት   የሚቀርቡትንም   ሆነ   በዙሪያችን   ያሉትን    የቢዝነስ   አማራጮች   ማየት  ከቻልን”   በሃገር  ወስጥ  ሰርቶ  መለወጥ  እንደሚቻልም  ተሞክሮዋን  መሰረት   አድርጋ  አጫውታናለች፡፡

 “ስደት  አማራጭ   ይሆናል  ብየ  አስቤው   አላውቅም”    የምትለው  ሃና  የቢዝነስ አማራጮችን በሚገባ ማየት ከተቻለ በሀገር ውስጥ ሊሰራ የሚችለው ስራ ብዙ መሆኑን ተናግራለች፡፡ የራስን ስራ መስራት ተቀጥሮ ከመስራት እጅጉን የተሻለና አዋጪ መሆኑንም ነው ወጣቷ ስራ ፈጣሪ ያብራራችው፡፡

ስራዋን ከዚህ የበለጠ የማስፋት ህልም ቢኖራትም የፋይናንስ ውስንነትና በዘርፉ ብቃትና ክህሎት ያላቸውን ባለሙያዎች አለማግኘቷ ግን ባሰበችው ልክ እንዳትራመድ እንዳደረጋት አልደበቀችም፡፡

ወጣት ዮናስ ሽዋንግዛው ትውልድና እድገቱ  በቦሌ ክፍለ ከተማ ወሎ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡  በጄነራል  መካኒክነት  ዲፕሎማ  አለው፡፡  በተለያዩ ጋራዦች ተቀጥሮ እየሰራ የሚያገኘው ገቢ በቂ ባለመሆኑ የኖረውን ከእጅ ወደ አፍ  ህይወት ዛሬም ድረስ ያስታውሰዋል፡፡

ወጣቱ ካሳለፈው ውጣ ውረድ በኋላ በ10 ሺህ  ካፒታል  እና  በሶስት ሰራተኞች የቡና  መፈልፈያና ሌሎች ማሽኖችን  እያመረተ  ለግለሰቦችና   ለዩንየኖች  ማቅረብ ጀመረ፡፡  የወጣቱ ካፒታል በአሁኑ ወቅት  1 ነጥብ 5  ሚሊየን   ደርሶለታል፡፡  የማምረት   አቅሙ  እየጨመረ  በመምጣቱም የሰራተኞቹን   ቀጥር   ወደ   ዘጠኝ   ከፍ  ማድረግ  ችሏል፡፡

ወጣቱ እንደሚለው አንድ የቡና መፈልፈያ ማሽን ከውጭ ሀገር ለማስገባት በትንሹ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ይጠይቃል፡፡ እርሱ ግን ማሽኑን በ600 ሺህ ብር ብቻ  ለገበያ ያቀርባል፡፡

የራሱ ስራ ህይወቱን በተሻለ መልኩ ለመመራት እንደረዳው የሚናገረው ወጣቱ ስራ ፈጣሪ፣ ለማሽኑ ግዥ ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ በማስቀረት ረገድም የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ነው የሚናገረው፡፡

ከቡና  መፈልፈያ   ማሽኑ   በተጨማሪ   የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችንና ፖሊሸሮችን    በእንፋሎት    ለመቀቀል    የሚስያችሉ   ማሽኖችንም  ይሰራል፡፡ 

ወጣቱ እንዳጫወተን ስራውን የበለጠ ማስፋት ቢፈልግም ከስራ ቦታ ጋር በተያያዘ ችግሮች ተጋርጠውበታል፡፡ ስራውን ሲጀምር ለመስሪያ ቦታ በካሬ ሜትር ይከፍለው የነበረው ገንዘብ በስምንት እጥፍ እንዲጨምር መደረጉም እንዳሳሰበው አልደበቀም፡፡ አንድ የቡና መፈልፈያ ማሽን ሰርቶ ለማጠናቀቅ ከሁለት እስከ ሶስት ወራት ከመውሰዱም ሌላ ገበያውም የሚያኩራራ አለመሆኑ ለኪራይ የሚከፍለው ክፍያ አሳስቦታል፡፡

በሀገር ላይ ሰርቶ መለወጥ እንዳሚቻል ወጣት ዮናስ ራሱን ማሳያ አድርጎ ይናገራል፡፡  ወጣቱ ኃይል አመለካከቱን አስተካክሎ ያገኘውን ስራ ወረድ ብሎ ለመስራት እስከወሰነ ድረስ የማይለወጥበት ምክንያት እንደማይኖርም ነው የሚገልጸው፡፡ “በሀገር ውስጥ ሰርቶ መለወጥ እየተቻለ ስደትን ምን አመጣው?” ሲልም ይጠይቃል፡፡

ኤርምያስ ፋንታየ ደግሞ በልብስ  ስፌት  ዘርፍ  የተሰማራ  ስራ  ፈጣሪ   ወጣት ነው፡፡ በኮልፌ  ቀራንዮ ክፍለ ከተማ  ወረዳ  12  በሚገኘው  የማምረቻ  ማዕከል   ወስጥ   በ2007 ዓ.ም  የማምረቻ ቦታ ከማግኘቱ በፊት 20 ሺህ ብር በማይሞላ መነሻ ካፒታል ነበር አረብ ሀገር ቆይታ ከተመለሰች ባለቤቱ ጋር በኪራይ ቤት ስራ የጀመረው፡፡

መንግሥት ባዘጋጀው የማምረቻ ቦታ ስራ መጀመሩን ተከትሎም ካፒታላቸው ወደ 400 ሺህ ብር የሰራተኞቻቸው ቁጥር ደግሞ ወደ 32 አሻቅቧል፡፡

መንግስት ለማምረቻው ዘርፍ እያደረገ ያለው ድጋፍ ትልቅ ቢሆንም ከብድር ጋር ያሉ ውስንነቶች ስራቸውን እንዳያስፋፉ አድርገዋቸዋል፡፡ ለዚህም ድርጅቱ የሚፈልገው የካፒታል መጠንና የሚፈቀደው ብድር የማይመጣጠን መሆኑን ገልጾ ለስራው የሚያስፈልጋቸውን ብድር አግኝተው ቢሆን ኖሮ ከ60 እስከ 70 የሚደርሱ ሰራተኞችን መቅጠር ይችሉ እንደነበር አብራርቷል፡፡

የገበያ  ትስስሩ  ጥሩ  ቢሆንም በቦታ እጥረት የተነሳ ቢሮ የለውም፡፡ ለሰራተኖች መጸዳጃ ቦታ ባለመኖሩም ልምድ ያስጨበጣቸው ሰራተኞቹ እየለቀቁበት በጣሙን ተቸግሯል፡፡

የሰራተኞቹን ቁጥር በማሳደግ ምርቶቹን ወደ ውጭ የመላክ ህልም እንዳለው የሚናገረው ወጣቱ ስደትን እንደ አማራጭ የሚወስዱ ወጣቶችም ችግሮችን ተጋፍጠው በሀገራቸው ሰርተው እንዲለወጡ ምክሩን ሰንዝሯል፡፡

በፌደራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ  የማኑፋክቸሪንግ፣ ፋሲሊቴሽንና  ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ  ደጀኔ ገብረማርያም እንዳሉት የሼዶች  ክፍፍልም  ሆነ ታሪፍ  ፍትሃዊ እንዲሆን በኮርፖሬሽን  እንዲተዳደሩ  ከስምምነት ላይ  ተደርሷል፡፡ የክፍያ ታሪፉም ቢሆን ነባራዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ መሆኑን ገልጸው ክፍያው የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማቸውና ስራቸውንም ጠንከር ብለው እንዲሰሩ ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡

ከብድር ጋር በተያያዘ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመድፈንም ከብሔራዊ ባንክ ጋር በትብብር ለመስራት የየሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ነው አቶ ደጀኔ የገለጹት፡፡ አቶ ደጀኔ እንዳብራሩት ከማመረቻ ማዕከላት ጋር የተገናኙ ማነቆዎችን ለመቅረፍ ደግሞ ማምረቻ ማዕከላትን ለመገንባት በአቃቂና ላፍቶ ክፍለ ከተሞች በእያንዳንዳቸው 100 ካሬ ሜትር ቦታ ተረክቧል፡፡ በክልሎችም ተመሳሳይ ተግባራት ይከናወናሉ፡፡

የኤጀንሲው ተልዕኮ ስራ  ፈጥሮ  መስጠት ሳይሆን  ስራ  ፈጣሪዎችን   መፍጠር  መሆኑን  ያብራሩት አቶ ደጀኔ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ   መሰማራት  ለሚፈልጉ  ወጣቶች  በጨርቃጨርቅ አልባሳት፣ በቆዳ ውጤቶች ምርት፣  በብረታብረት ኢንጂነሪንግና መሰል ዘርፎች ስልጠና እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም  በኦሮሚያ 5፣  በአማራ 5፣  ደቡብ 3 ፣ በትግራይ 2  እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደግሞ አንድ  የስልጠና  ማዕከላት እንዳሉት ነው ያብራሩት፡፡  

በአምራች  ኢንዱስትሪው  ለሚሰማሩት  በሌሎች  ዘርፎች  ከሚሰማሩት ቅድሚያ   የመስሪያ ቦታ የሚሰጥበት አሰራር መዘርጋቱና  ከልማት ባንክ ጋር  በመተባበር  የማምረቻ ማሽን  ገዝቶ  የሚሰጥበት አግባብ መኖሩም ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት እንደሚያመላክት ነው አቶ ደጀኔ ያብራሩት፡፡

አቶ ደጀኔ እንዳብራሩት በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶችን የገበያ አድማስ ለማስፋት በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ በሚዘጋጁ ባዛሮች ላይ እንዲሳተፉ ይደረጋል፡፡ ለአብነት ያህልም በቅርቡ በቦትሶዋና በተካሔደው ባዛር 28 አምራቾች ተሳትፈዋል፡፡ በዚህም በተለይ የጫማ ምርታቸው አድናቆትን በማትረፉ 110 ሺህ ጥንድ ጫማዎች የታዘዘበትን አጋጣሚ አስታውሰዋል፡፡ ሱዳን በተካሔደው ባዛር 17 አምራቾች ተሳትፈው ምርታቸው ተቀባይነት ማትረፉንም አብራርተዋል፡፡

በተሰሩ ስራዎች እስካሁን ከስድስት ሺህ  800 በላይ   አምራች  ወጣቶች  ወደ ሚሊየነርነት  ተሸጋግረዋል፡፡ በዘርፉ የሚታዩ ማነቆዎችን በተጠና መንገድ መቅረፍ ከተቻለና የወጣቶችን የአመለካከት ክፍተት ደፍኖ ለስራ የሚታትር ወጣት መፍጠር ከተቻለ በዘርፉ ሚሊየኖች ሚሊየነር የሚሆኑበት ጊዜ እሩቅ አለመሆኑን ከላይ ያነሳናቸው አብነቶች ተጨባጭ ማረጋገጫዎች ናቸው፡፡

Last modified on Saturday, 17 March 2018 18:40
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን