አርዕስተ ዜና

የኢትዮ- ኬንያ የትብብር ድልድይ

20 Mar 2017
3856 times

ከሰለሞን ተሰራ

በኬኒያና ኢትዮጰያ ድንበር ሞያሌና ቦረና አካባቢ የሚኖሩ ማህበረሰቦች በግጭት፣ ድህነትና  ለአካባቢ ጉዳት ተጋልጠው ለረዠም ጊዜ የኖሩ ህዝቦች እንደነበሩ ሮይተርስ የተባበሩት መንግስታት ያወጣውን ፅሑፍ መሰረት በማድረግ ዘግቧል፡፡

አአአ ከ2012 እስከ 2013 በሞያሌ ከተማ በተፈጠረው ግጭት ለበርካታ ሰዎች ሞትና ንብረት ጥፋት  ሆኖ እንደነበር አመልክቷል፡፡

ይህ ችግር ደግሞ ማህበራዊ ተጽእኖውን በማጉላት ነዋሪዎቹን ከመኖሪያ ቀዬአቸው እንዲፈናቀሉና ፣ ለወንጀልና ለአክራሪዎች መፈጠር ምክንያት ሆኖም እንደነበር ጠቅሷል፡፡

ነገር ግን  በኢጋድና በተባበሩት መንግስታት አጋርነት በኢትዮጵያና በኬንያ መንግስት መካከል በተከታታይና ስር ነቀል በሆነ መንገድ በተከናወነ የድንበር ተሻጋሪ ፕሮግራም ችግሮቹን መቅረፍ ተችሏል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒ ጉቴሬዝ በቅርቡ በኬንያ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በኢትዮ ኬንያ ድንበር ተሻጋሪ ፕሮግራም የተጠቃለለው አካባቢን መሰረት ያደረገ የልማት ፕሮግራም በሌሎች አካባቢዎች ቢተገበር ውጤታማ ተግባር ለማከናወን እንደሚያስችል መናገራቸውን ዘገባው ገልጿል፡፡

የፕሮግራሙ ጅማሮ አካባቢውን ወደ ተሻለ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ተስፋ እንዳላቸው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ለዋና ፀሐፊው ገልጸውላቸዋል፡፡ “ፕሮግራሙ ሞያሌን የአፍሪካ ዱባይ ያደርጋታል”  ብለዋል፡፡

የሁለቱን አገራት ቁርጠኛነት የሚያሳየው መዘርዝር በኢትዮጵያና ኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች አዘጋጅነት

ሰላምና ልማትን ለማፋጠን የኢትዮጰያና ኬኒያ ድንበር ተሻጋሪ ኢኒሼቲቭ በሚል ርዕስ  የቀረበ ጽሁፍ ለንባብ በቅቷል፡፡

ኢኒሼቲቩ ድንበር ተሻጋሪ በሆኑት መርሳቤት ካውንቲ ኬንያ እና በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ በቦረና ዳዋ ዞኖች ያለውን ሰላምና ብልፅግና ለማረጋገጥ ያለመ ነው፡፡

በኬንያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ዶክተር ስቴፋኖ ኢጃክ “ እኔ አዎንታዊ ለውጦችን ተመልክቻለሁ፡፡ እናም የአውሮፓ ህብረት ከኢጋድና ከተባበሩት መንግስታት ጋር በመተባበር ድንበር ተሻጋሪ ፕሮግራሙን ለመደገፍ ወስኗል፡፡ፕሮግራሙን ወደ ማንዴራ ሶስት ማዕዘን (ኬንያ-ኢትዮጵያ-ሶማሊያ) ወደ ኦሞ (ኬንያ-ደቡብ ሱዳን) ወደ ካራሞጃ  (ኬንያ-ኡጋንዳ)  ክላስተር ማሳደግ እንሻለን”.ብለዋል፡፡

ከታዩት አዎንታዊ ምልክቶች መካከል በአካባቢው ሰላምን በማስፈን የትብብር መሰረት መጣሉ ይጠቀሳል፡፡ ከተለያዩ ጎሳዎች የተውጣጡት የአካባቢው የሰላም ኮሚቴ አባላት ሰላምና አብሮነት እንዲጎለብት ደከመን ሰለቸን ሳይሉ እየሰሩ መሆናቸውን ዘጋቢው ጽፏል፡፡

በአክራሪነት መንፈስ የተሞሉትን ወጣቶች ከጥፋታችው እንዲቆጠቡ ለማድረግ የአካባቢው ሽማግሌዎች እውነታውን እንዲገነዘቡ እያደረጓቸው ነው፡፡ በዚህም አክራሪና አሸባሪ ድርጅቶችን የሚቀላቀሉ ወጣቶች ቁጥር በእጅጉ መቀነሱን ከፅሑፉ መገንዘብ ችለናል፡፡

የአካባቢውን ባለስልጣኖችና ማህበረሰቡን በማብቃት የድህነት ምጣኔውንና በመርሳቤት ካውንቲ ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል በመሰራት ላይ መሆኑም ተገልጿል፡፡የኢሶሎ-ሜርሊ-መርሳቤት-ሞያሌ መንገድ በመጠናቀቁ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረውና ድንበር ተሻጋሪ ንግዱንም እንደሚያሳልጠው ዘጋቢው ጠቅሷል፡፡

በተጨማሪ መንገዱ ከደቡብ አፍሪካ እስከ ግብጽ የሚዘልቀውን   መንገድ ግንባታ  እውን ለማድረግ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርም ተብራርቷል፡፡

በቀጠናው ያለው እምቅ የማህበራዊ ኢኮኖሚ ልማት እራሱን የቻለ ሐብት ነው፡፡ያልተነካው የቀንድ ከብት ሐብት ለቆዳ  ፣ ለስጋና ለወተት ኢንዱስትሪ መሰረት ነው፡፡በሁለቱ አገራት የድንበር አካባቢ ነዋሪዎች መካከል የሚከወናወነው ድንበር ተሻጋሪ ንግድ  ለሁለቱም አገራት ከፍተኛ ገቢ ያስገኝላቸዋል፡፡

በከተሞቹ ያለው የማህበረሰቦቹ ባህላዊ፣ታሪካዊና አካባቢያዊ ስብጥር የቱሪዝም ሐብትና ያልተበረዙ የኑሮ እውነታዎች የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስቡ ናቸው፡፡ ከዚህ ባለፈ አሰተማማኝ የሆነው የታዳሽ ሐይል እምቅ ሐብት ለአገራቱ ብልፅግና መሰረት መሆን የሚችል መሆኑን ፀሐፊው ጠቅሷል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን ይህንኑ ያልተነካ ሐብት በመጠቀም በአካባቢው የሚታየውን ድህነት ለመቀነስ እና በተለያዩ መስኮች ልማትን ለማምጣት እየሰራ ነው፡፡ በተለይ በድንበር ዘለሉ ንግድ በስፋት ተሳታፊ የሆኑትን ሴቶች ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻልም በፀሐፊው ተገልጿል፡፡

የተባበሩት መንግስታት በቅርቡ ይፋ የሚያደርገው “He for She” ኢኒሼቲቭ ሴቶችን ለማብቃት የጾታ መበላለጥ ችግርን ለማስወገድና በሁለቱም አገራት የሚገኙ ሴቶችን በልማት ስራው ተሳታፊ ለማድረግ ያግዛልም ተብሏል፡፡

ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመተባበር የተደረገው ጥናት በድንበር አካባቢው ለግጭት ምክንያት የሆኑትን መንስኤዎች ለመለየት ከማስቻሉ በላይ ባለድርሻ አካላት በቦታው የሚታየውን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ የሚያደርጉትን እገዛ የሚያጠናክርላቸው መሆኑን ፀሐፊው በዘገባው አካቶታል፡፡

ይህ ደግሞ የአፍሪካ ህብረት ሰላምንና ደህንነትን ለማስፈን የያዘውን አጀንዳ 2063 ራዕይ እውን ለማድረግ መንደርደሪያ እንደሚሆን ታምኖበታል፡፡

በድንበር ከተሞቹ አካባቢ ያለው የንግድ ዝውውር ዝቅተኛ ሲሆን ወደፊት ከፍተኛ እድገት እንደሚያስመዘገብ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡

የፕሮግራሙ አስተባባሪና የኬንያ ፕሬዝዳንት ቢሮ ሐላፊ የሆኑት ወይዘሮ ሩት ካጊያ   “ኢኒሼቲቩ በአግባቡ ተግባር ላይ ከዋለ የድንበር ግጭቱን በማስወገድ የአዲስ አማራጭ ድልድይ በመሆን ያገለግላል፡፡ በተለይ የተዘነጉትንና በድህነት ውስጥ ያሉትን ማህበረሰቦች በ2030 ከድህነት ለማውጣት ያስችለናል ”.ማለታቸውን ጠቅሶ ፀሐፊው ዘገባውን ድምድሟል፡

 

 

 

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን