አርዕስተ ዜና

ያልገታነው “ናዳ”

19 Mar 2017
1949 times

በረከት ሲሳይ (ኢዜአ)

ፀሀይ ንዳዷን ጨርሳ ቀኑ ማለፉን ለማብሰር ስታዘቀዝቅ፤ ጀንበር መጥለቋን ተንተርሶ ሠማዩ ሲቀላ፤ ከዚህ ሠማይ ሥር ቀኑን ሙሉ ላይ ታች ሲል ኑሮን ለማሸነፍ ሲዋትት የዋለው የአዲስ አበባ ነዋሪ አንዳንዱ በባቡር፣ ሌላኛው በአውቶብስ፣ ገሚሱ በታክሲ፤ አንዱ በአንዱ ላይ ተደራርቦ አልያም ደግሞ በእግሩ እየተጓዘ “ዞሮ ዞሮ ከቤት” እንዲሉ ማልዶ የወጣበትን ቤቱን ከአመሻሹ ዳግም ለመመለስ የሚያደርገው ትግል ሁሌም የምንታዘበው የከተማችን ማኅበራዊ  ትዕይንት ሆኗል።

 

ከዚህ ሁሉ ትርምስና ግርግር ጀርባም በርካታ አዛውንቶች፣ ሕጻናት፣ አቅመ ደካሞች በሌላቸው አቅም ከጉልበታሙ ወጣት ከተሜ ጋር መሳ ለመሳ ቆመው የአቅማቸውን ተፍጨርጭረው ከቤታቸው ደጃፍ ይደርሱ ዘንድ የሚያደርጉትን ትንቅንቅ በአንክሮ ለሚመለከት ትካዜ የሚጭር ሌላኛው የአደባባይ ክስተት ነው።

 

ከዚሁ ሁሉ በኋላ፤ በለስ ቀንቶት የተሳፈረ ምንም እንኳን በሙሉ መቀመጫ ሳይቀመጥ፣ በኩርሲና ባለቀ የመኪና ባትሪ ፕላስቲክ ላይ ተቀምጦ፤ ከከፈለው ገንዘብ የሚገባውን መልስ ሳይቀበል ጉዞውን እንዲገፋ ይገደዳል።

 

እንደ ጀት እየበረረ በሚሄደው በዚሁ ተሽከርካሪ ወስጥም ግራና ቀኙን እያማተረ ነፍስና ስጋው ተላቆ “ኧረ! ሹፌር ቀስ ብለህ ንዳ እንጂ” ብሎ በኃላፊነት መንፈስ ላቀረበው ማሳሰቢያ “ምን አገባህ?” የሚል “ዱቄት ላበደረ አመድ” ዓይነቱ መልስ ይሰነዘርበታል። በዚኅ መሰሉ በተለያዩ ተዕይንቶች በታጀበ ጉዞ  ከቤቱ! ከቀዬው! ይደርሳል። ይህ አኳሀኋን በራሱ እንግልት ቢሆንም፤ በሰላም ከቤቱ መድረስ መቻሉን ሲያስብ ለአምላኩ ምስጋና አቅርቦ ነገ የተሻለ እንዲሆን ከመመኘት ውጪ ሌላ ነገር የማድረግ አቅም የሚኖረው አይመስለኝም። ለምን ቢሉ? የዕለት ጉርስ ፍለጋ ደፋ ቀና ብለው ቤታቸው ለመመለስ ወጥነው በትራፊክ አደጋ ምክንያት ወጥተው የቀሩ ወገኖች በርካታ መሆናቸው ነው። ጎበዝ! አያሌዎች ደግሞ ለከባድ አካል ጉዳት ተዳርገው ከሥራ ገበታቸው ርቀው፤ ከቀለም ትምህርታቸው ተስተጓጉለው በአንድ ጀንበር የአልጋ ቁራኛ በመሆናቸው ተስፋቸው ነጥፎ አዲስ ነገር ሳይታያቸው ዘመናቸውን ይቆጥራሉ። ከእነዚህ ሰዎች ጀርባም፤ በርካታ ሰዎችም የዕለት ተዕለት ኑራቸው  ሲመሰቃቀልባቸው፣ ያረፉ እጆች ያሏቸው እናቶችና አባቶች ደግሞ ጧሪ ቀባሪ አጥተው ሞታቸውን ይማጸናሉ።

ይህን ኩነት ተግ ብሎ ለሚከታተለው አስተዋይ ሰው፤ ጉዳዩ የሚያስተክዝ በንጹህ ህሊና ሲታይም የስንቱን ቤት ደስታ ገፎ ማቅ ያጎናጸፈ በመሆኑ እንባ ያራጫል። እውነት ለመናገር፤ ዛሬ በአገራችን ተሽከርካሪ ማሽከርከርም ሆነ ተሳፍሮ መሄድ በሞት ጥላ መካከል የመሄድ ያክል አስፈሪነቱን እኔ ከማስነብባችሁ በላይ ራሳችሁ ታውቁታላችሁ።

በየቀኑ በሚደርሱ አደጋዎች ልክ ተቆጥሮና ተሰፍሮ እንደሚሰጥ ያክል ገና ማልደን ስንነሳ በራዲዮ ከምንሰማው ቀዳሚ ንጋት ፈንጣቂ ክፉ ዜና ከሆነ ሰነባብቷል። በጣም የሚገርመው ደግሞ የትራፊክ አደጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ “ኧረ በእውነቱ ወዴት እየሄድን ነው ጎበዝ” ያሰኛል። ለምሳሌ ያክል ያለፈውን ዓመት እንኳን መረጃ ብናጣቅስ 4 ሺ 352 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ ከ13 በላይ ደግሞ ለቀላልና ለከፋ የአካል ጉዳት ተዳርገዋል። “ለችግሩ ዋነኛ መንስኤ ምንድን ነው?” ተብለው ለሚቀርቡት ጥያቄዎች በዋነኝነት በአገሪቷ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት አለመሟላት፣ የግንዛቤ ማነስ፣ የአሽከርካሪዎች ሙያና ሥነ - ምግባር ጉድለት - ለዚህም ደግሞ የተጠናከረ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት አለመኖር፣ ለመንገድ ደኅንነት ተብለው የሚወጡ ሕጎችና ደንቦች ተፈጻሚነት አለመኖር፣ የአስፈጸሚ አካላት የሥራ ግድፈትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ይነሳሉ።

ይሁን እንጂ ለበርካታ የትራፊክ አደጋዎች በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የአሽከርካሪዎች የሙያና የሥነ - ምግባር ጉድለት መሆኑን ልብ ይሏል። ይህ ምክንያት እኔም እንደ አንድ ዜጋ ለሚከሰቱት አደጋዎች ያለው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን በሙሉ ልቤ አምናለሁ። ይህ ከሁለት መልኩ ሊመጣ የሚችል ችግር መሆኑንም እገነዘባለሁ፤ አንድም በቸልተኝነትና ሌላም በግንዛቤ ማነስ ብዬ ለማስረደት እሞክራለሁ። ቸልተኝነት ስል በርካታ የአሽከርካሪ ፍቃድ ማረጋገጫ ከሚመለከተው ህጋዊ አካል የያዙና ነገር ግን በትራፊክ እንቅስቃሴ ላይ ያላቸውን ግንዛቤ በተገቢው መልኩ የማይፈጽሙ ናቸው። ለምን ብለን እራሳችንን ከዚያም እነኚሁ አሽከርካሪዎችን በምንጠይቃቸው ጊዜ መልሱ ያለ ምንም ምክንያት መሆኑን ስንረዳ ጉዳዩ ቸልተኝነት መሆኑን እናውቃለን። ኧረ እንደው አንድ ግለሰብ በፍጥነት ማሽከርከር አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል እያወቀ፤ የትራፊክ የመንገድ ዳር ምልክቶች፣ የትራፊክ መብራቶች  እንዲሁም ትራፊክ ፖሊስ አለማክበር የሚያመጣው ጉዳት የከፋ መሆኑን እያወቀ፣ ለእግረኞች ቅድሚያ አለመስጠት ህይወት እንደሚቀጥፍ እያወቀ እንዴት ሰው ተጠንቅቆ አያሽከረክርም? ለምንስ እርሱ አጥፍቶ ለሌሎች የጥፋት ሳንካ ምክንያት ይሆናል? ያው ቸልተኝነት ነው፤ ሌላ ምክንያት ያለው አይመስለኝም።

በሁለተኛ ደረጃ የግንዛቤ ማነስ ነው ብዬ የማነሳው በሁለት መንገዱ ቢታይ መልካም ይመስለኛል። አንደኛው ግንዛቤ ሊመጣ የሚችለው በሚሰጡ የትምህርትና የሥልጠና መርኃ ግብሮች እንጂ ግንዛቤ በራሱ እንደ ውቃቢ ሊሰፍር የሚችል ነገር አይደለም። በመሆኑም በአሽከርካሪዎች ላይ የሚስተዋለው የግንዛቤ ማነስ በቂ ትምህርትና ሥልጠና ባለመውሰዳቸውና ወደ ሙያው የገቡት በልምድ መሆኑ ነው። ይህስ እንዴት ነው ቢሉ? በአሁኑ ወቅት በትክክለኛው መንገድ ተከትለው የአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ የሚወስዱት ምን ያክል ናቸው? የሚል ጥያቄ ቢነሳ የሚገኘው ምላሽ “በጣም ትንሽ ቁጥር ያላቸው ግለሰቦች” የሚል ይመስለኛል። በርካታ ሰው ሕጋዊ ባልሆነ መልኩ በሰው በሰው ሕጋዊ ፍቃድ ያላቸው እንዲሁም ሕገ-ወጥ ፍቃድ ያላቸው መሆኑን ነው የምንረዳው። ቀላል የማይባሉ ደግሞ ያለ አሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ የሚያሽከረክሩ መሆናቸው ሌላኛው ሁኔታዎችን በትክክል የሚገልጽልን እውነታ ነው። ለምሳሌ ያክልም ባለፉት ስድስት ወራት በአዲስ አበባ ብቻ ከ700 በላይ የሚሆኑ ግለሰቦች የአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ ሳይኖራቸው ሲያንቀሳቅሱ ተገኝተዋል፤ በዚህች መዲና 15 ግለሰቦች ደግሞ በጥር 2009 ዓ.ም ብቻ ሕገ-ወጥ የአሽከርካሪዎች የብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ ይዘው ተገኝተዋል። 

 

በሁለተኛ ደረጃ ያለው የግንዛቤ ማነስ ሊመነጭ የሚችለው በአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት የሚሰጡት ትምህርቶች ጠንክራ ካልመሆናቸው አልያም ደግሞ ለሥልጠናው የሚጠየቀው የትምህርት ደረጃ አነስተኛ በመሆኑ ግለሰቦች ጉዳዩን በቅጡ ካለማጤናቸው ነው ባይ ነኝ። አንዳንድ የማሰልጠኛ ተቋማት በቂ ሥርዓትን የተከተለ የሥልጠና መርኃ ግብር እንደሌላቸው በሥፋት የሚነገር ሲሆን፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ የብቃት ማረጋገጫ ፍቃድም በቀላሉ እንደሚሰጡ ነው የሚነገረው። በሌላ በኩል አንድ ግለሰብ “አራተኛ ክፍል ከጨረሰ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም ገብቶ መሰልጠን ይችላል” የሚለው መርህ በራሱ በሥልጠናው ወቅት በሠልጣኞች ረገድ የጋራ መግባባት ወይንም ተግባቦት እንዳይኖር ያደረገ ሌላው ምክንያት ይመስለኛል። ይህም ወደ ሙያው ተቀላቅለው በሥራ ላይ የሚገጥማቸውን የቴክኒክና የሙያ ሥነ-ምግባራት ከማወቅ በዘለለ በገቢር ጥቅም ላይ አውለው ሊደርስ የሚችለውን የትራፊክ አደጋ መከላከል አለመቻላቸው ይህንኑ ያሳያል።

 

በቀላሉ ይህንን ለማጠናከር በአሽከርካሪዎች ሥልጠና መርህ መሰረት አንድ አሽከርካሪ ሊያደርገው የሚገባ ጥንቃቄ ተብሎ ከተዘረዘሩ መሰረታዊ ጉዳዮች መካከል አንድ አሽከርካሪ፤ ተሽከርካሪ ውሰጥ ከመግባቱ በፊት፣ የተሽከርካሪውን ኮፈን ከፍቶ፣ ተሽከርካርካሪ ውስጥ ከገባ በኃላና በእንቅስቃሴ ወቅት ተገቢውን ፍተሻ ማድረግ እንዳለበት ያስገድዳል። ምን ያክሉ አሽከርካሪ ይሆን ይህንን የሚያደርገው ? እኔ በበኩሌ በዚህ ረገድ ጥርጥር አለኝ። ከዚያ በዘለለ በከተማና በሌሎች በደረጃ አንድ ሁለት እንዲሁም ሦስት ተብለው እንደ አሽከርካሪ ዓይነቶቹ የተጠቀሱት የመንገድ የፍጥነት ወሰን የሚያከብሩት ሹፌሮች ምን ያክሉ ናቸው? እነዚህንና በመንገድ ደህንነት ዙሪያ የሚነሱትን ጥያቄዎች እያሰላሰላችሁ ለራሳችሁ መልስ ከመስጠት በዘለለ የበኩላችሁን ትወጡ ዘንድ ምኞቴ ነው። ይሁንና እኔም በአገራችን ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ በቀዳሚነት የአሽከርካሪዎች የሙያና የሥነ-ምግባር ጉዳይ በቅጡ ሊጤን እንደሚገባ ነው የማስበው።

 

ይህ በተለይም ለአሽከርካሪዎች የሚሰጠው የብቃት ማረጋገጫ ሥልጠና አሁን ካለበት የጊዜ ሰሌዳ ሊራዘም እንደሚገባና ቴክኒካል የሆኑ ጉዳዮች ላይ ትክክለኛ ገንዛቤ መፈጠሩን ማረገጋገጥ ተገቢ ይመስለኛል።  ከዚህ ጎን ለጎን፤ በሥልጠና ተቋማት የሚሰጡት የሥነ-ባህሪ ትምህርቶች በአሽከርካሪዎች ላይ ለውጥ እንዲያመጣ ከተፈለገ የተመደበው ጊዜም እንደ ቴክኒክ ክፍሉ ሊጠናከር ይገባል። በሌላ በኩል የሚጠየቀው የትምህርት ደረጃ አሁን ካለበት አራተኛ ክፍል እንደው ቢያንስ ከስምንተኛ ጀምሮ ቢሆን ይህም ግንዛቤ ለመፍጠር ቀላል የሚያደርገው ይመስለኛል። እነዚህ ከላይ የተደረጉት ጉዳዮች የሚሟሉ ከሆነ ቀሪው ለትራፊክ መንገድ ተብለው የሚወጡትን ሕጎችና ደንቦች በመጀመሪያ ከሚመለከተው አካል ጋር ስለ አስፈላጊነቱ መግባባት በመፍጠር ለተግባራዊነቱ መረባረብ ያስፈልጋል። በተለይም ሕግን- ተላልፈው በሚገኙ አሽከርካሪዎች ላይ ተገቢውን ቅጣት መጣልና ከድርጊታቸው እንዲማሩ ማድረግ ለነገ የማይባል መሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው። በአሽከርካሪዎች ላይ የሚካሄደው ፍተሻም በኃላፊነት ስሜት የሚደረግ መሆኑን ማረጋገጥም እንዲሁ ትኩረት ያሻዋል።

 

ኅብረተሰቡም ህግንና ደንብን በማወቅ፣በማክበር እንዲሁም ሊጣሱ ሲሉ በመከላከል እንዲሁም ተጥሰው ሲገኙም ለአስፈላጊ እርምት እርምጃ መተባበር ይገባል። ሌላው በረጅም ጊዜ እቅድ፤ የከተማዋን የመንገድ መሰረተ ልማት ማሟላትና የትራንስፖርት አቅርቦቱንም በማሻሻል ዘርፉን የተሻለ ማድረግ እንደሚገባ ይሰማኛል።  የትራፊክ አደጋ በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን በየዓመቱ ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊየን በላይ ሰዎችን ህይወታቸውን የሚነጥቅ ነው፤  በአሁኑ ወቅት እድሜያቸው ከ15 አስከ 29 የሆኑ ወጣቶች በቀዳሚነት ለህልፈተ ህይወት የሚዳረጉት በትራፊክ አደጋ መሆኑንም የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል። ከእነዚህም አደጋዎች መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት አደጋዎች የሚከሰቱት በእድገት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ባሉ የዓለም አገሮች ሲሆን፤ በአንጻሩ በእነዚህ አገሮች ያለው የትራንስፖርት አቅርቦት ደግሞ ዝቅተኛ መሆኑን ነው የተመለከተው። ለችግሩ ምንም ዓይነት መፍትሄ የማይሰጠው ከሆነ የትራፊክ አደጋ ተባብሶ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2030  ዓለም ላይ ካሉ ገዳይ በሽታዎች መካከል ሰባተኛ ደረጃን ይቆናጠጣል ተብሏል።  ይህም የችግሩን ግዝፈትና ለመፍትሄውም የሁሉም ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ አመላካች ነው።

 

ይግረማችሁና ይህን ጽሁፍ ለማዘጋጀት ምከንያት የሆነኝ ከሳምንታት በፊት ቤተሰብ ጠይቀው ከጎጃም ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ በተሽከርካሪ አደጋ ህይወታቸውን ባጡት ባለትዳሮች ነበር። ከዚህም በመቀጠል ከቀናት በፊት በትራፊክ አደጋ መንስኤና መፍህትሄ ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በተካሄደው ስብሰባ ላይ የትራፊክ አደጋ የደረሳባት አንዲት ወጣት ስላለችበት ህይወት የተናገረችው ንግግር እኔን ብቻ አይደለም ብዙዎች የስብሰባው ታዳሚዎችን ቅስም የሚሰብር መሆኑም ሌላው ለመጻፌ ገፊ ምክንያት ነው።  በሚያሳዝን መልኩ ይህንን ጽሁፍ በማዘጋጅበትም ወቅት አራት የካቶሊክ ደናግላን ህይወታቸውን በትራፊክ አደጋ ማጣታቸውን ስሰማ ስለጉዳዩ አውርተን አፍታም ሳንቆይ ሌላ አዲስ አደጋ ተቀባይ መሆናችን የችግሩን ግዝፈት የሚያሳይ ነው።

 

የትራንስፖርት ሚኒስትር  ዴኤታ አቶ አብዲሳ ያደታ እንደተናገሩት፤ የጊዜ ጉዳይ ነው አንጂ የትራፊክ አደጋ ኃይ ባይ የማባይባል ከሆነ የሁሉንም በር ያንኳኳል። ትምህርት አዘል መልዕክት “እኽ” ብሎ በመስማት ነገን የተሻለ ለማድረግ እንረባረብ።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን