አርዕስተ ዜና

የህጻናቱ ጉዳይ

በሚስባህ አወል /ኢዜአ/

እንደምን ከረማችሁ የፍትህ ዘገባ ታዳሚያን ዛሬ ስለህጻናት የፍትህ ስርዓት የተወሰነ ነገር ብናወሳስ ብለናል፡፡ እንደመግቢያ ይሆነን ዘንድም ቆየት ካለ አንድ ጋዜጣ ያገኘሁትን ቀልድ ቀመስ ቁም ነገር ላውጋችሁ፡፡

በሀገራችን ቆየት ካሉ ዘልማዳዊ የሆኑና ጥሩ ያልሆኑ አባባሎች መካከል በሴቶችና ህፃናት ላይ የተነገሩ በተለይ በልጆች ላይ ያለውን ለአብነት ብናነሳ ልጅ ያቦካው ለራት አይበቃም፣ የልጅ ነገር አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ፣ ከልጅ አትጫወት ይወጋሀል በእንጨት ወዘተ… የሚሉ አባባሎች አሉ፡፡

እነዚህኑ ቀልዶች መሰረት በማድረግ ትንሽ ነገር ማለት ፈለግሁ፡፡ በአንድ ገጠር አካባቢ የሚኖር የአንድ ቤተሰብ አባወራ የሰጋ አምሮቱን ለመወጣት ከአካባቢው ከሚገኙ ፍየሎች አንዱዋን ይሰርቅና ቤቱ በመምጣት በምሽት አርዶ ቤተሰቡን ይመግባል፡፡

የቤተሰቡ አባላት የሆኑት ህጻናትም በጣም ጠግበው በመብላታቸው ሳቢያ ይመስላል ቁንጣን ብጤ ይይዛቸውና እንቅልፋቸውን ያጣሉ በዚህ ጊዜ እናትና አባት ወደ ውጭ ወጣ ብለው የቤቱ ጣሪያ ላይ ውሃ በመርጨት ዝናብ መጣ ተኙ! ተኙ! በማለት ህፃናቱን በማባበል ያስተኛሉ፡፡

በማግስቱ ፍየል የጠፋበት ግለሰብ ለሀገር ሽማግሌዎች አቤቱታ ያቀርብና የአካባቢው ነዋሪ አውጫጭኝ ይቀመጣል፡፡

አውጫጭኝ በተለይ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የተለመደ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡

ታድያ በአውጫጭኑ ላይ የተሳተፉ የሀገር ሽማግሌዎች መቼም ልጆች አይዋሹም በሚል ህፃናቱን ለብቻ ይሰበስቡና ቤቱ ስጋ የበላ ልጅ እጁን ያውጣ!! ማነው ?  ብለው ይጠይቃሉ እነዛ ማታ ፍየሏን  የበሉ ህጻናትም እኛ በልተናል ሲሉ በመናገራቸው ለልዩ ምርመራ ለብቻቻው ገለል ተደርገው የመስቀለኛ ጥያቄ ይቀርብላቸዋል፡፡

ሽማግሌዎቹም ህጻናቱ ስጋ የበሉት መቼ እንደሆነ የማጣራት ጥያቄ ሲያቀርቡ ህፃናቱ በአንድ ድምፅ ዝናቡ የዘነበ ጊዜ ብለው መልስ ይሰጣሉ፡፡

በአውጫጪኑ ላይ የተሳተፉት ሽማግሌዎችም ‹‹አይ የልጅ ነገር !!›› ባለፈው ክረምት የበሉትን ነው የሚነግሩን በዚህ ጠራራ በጋ ዝናብ ከየት መጥቶ ብለው የህጻናቱን ትኩስ መረጃ በመተው አፈርሳታው ያለውጤት እንደበተኑት ይነገራል፡፡

ታድያ ዛሬ የህፃናት የፍትህ ጉዳይ የልጅ ነገር ተብሎ የሚተው አይደለም፡፡ ህጻናቱ ገለል ብለው የሚዳኙበት የህፃናት ችሎት በየመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ተቋቁሞ ይታያል፡፡

ለአብነትም  በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት  ልደታ ምድብ ችሎት የህፃናት ችሎትን ለመመልከት ወደድን፡፡

ይህ ችሎት ምን ይሰራል አስፈላጊነቱና ጥቅሙ ምንድን ነው ለሚሉና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አጭር ቆይታ  ከዚሁ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት  ልደታ ምድብ ችሎት ዳኛ እና የህፃናት ጉዳይ አስተባባሪ ከሆኑት አቶ ልዑለስላሴ ሊበን ጋር ጥቂት ቆይታ አድርገናል እነሆ!!

‹‹በመጀመሪያ›› ይላሉ አቶ ልዑለስላሴ ‹‹ በመጀመሪያ የህፃናቱ ችሎት የተቋቋመው ህፃናቱ የሚደርስባቸውን በደልና ጥቃት ያላንዳች ፍራቻ ቃላቸውንና ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ እንዲያግዝና ለፍትህ ስርዓቱ በቂ ግብዓት እንዲገኝ ታስቦ ህጻናቱ ፍትሀዊ ዳኝነት እንዲያገኙም ጭምር የተዘጋጀ  ችሎት ነው፡፡››

‹‹ ችሎቱ ህጻናት በመደበኛው ፍርድ ቤት ጉዳያቸው ሲታይ ጥቃት ያደረሰባቸውን ግለሰብ ፊለፊት በማየትና የመደበኛው ፍርድ ቤት ድባብ የዳኞች አቀማመጥ ፣ የተጠርጣሪዎች መቀመጫ ፣ የክርክሩ ሀይለቃልና አጠቃላይ የችሎቱ ድባብ በህፃናቱ ስነ ልቦና ላይ ሊፈጥር የሚችለውን የፍራቻ ስሜት በማስወገድ ህፃናቱ በነጻነት ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ የሚያስችል ነው፡፡››

‹‹በፍርድ ቤት ችሎት ላይ በክርክር ሂደት ውስጥ የስነ-ስርዓት ግድፈቶች ሲፈጠሩ ችሎቱ ጠንከር ያለ የዲሲፕሊን እርምጃ እንደሚወስድ ይታወቃል በዚህም ህጻናት ድንጋጤና ፍራቻ ውስጥ የሚገቡበት ሁኔታዎች ይፈጠራሉ››

‹‹የህጻናቱ ችሎት ለህፃናቱ ምቹ በሆነ መንገድ መዘጋጀት አለበት የተለያዩ ማጫዎቻዎች የያዘ ፤  ህፃናቱ የፈለጉትን በነፃነት እንዲናገሩ የሚያስችል ድባብ ያለው መሆን ይኖርበታል፡፡››

‹‹በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ህጻናት ባለጉዳዮች እድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች ሆኖ ወንጀል ፈፅመው ይመጣሉ ፣ እንዲሁም በቤተሰብ ጉዳይ በባልና ሚስት ፍቺ ፤ የቀለብ አለመከፈል ፤ አባትነትን ለማረጋገጥ ፤ እና በመሳሰሉት ጉዳዮችም ይመጣሉ፡፡

እነዚህን ጉዳዮች ለህፃናቱ ምቹ በሆነ ድባብ በስነልቦና ባለሙያዎች በመታገዝ ድጋፍ እንዲያገኙ የማድረግ ስራ ይከናወናል፡፡››

እንዲሁም ህጻናቱ በአዋቂዎች ጥቃት ተፈፅሞባቸው ለምስክርነት ፤ በተበዳይነት ይመጣሉ ይህ ማለት በሌሎች ጉዳዮች አይቀርቡም ማለት አይደለም፡፡ ››

‹‹ታድያ ይህን ጉዳያቸውን በነጻነትና ያለፍራቻ እንዲያስረዱና ትክክለኛ ፍትህ እንዲያገኙ ምቹ ድባብ መፍጠር በማስፈለጉ የህጻናት ልዩ ችሎት መቋቋሙን ጠቅሰው ይህን መሰል ችሎት በርካታ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች አቋቁመዋል፡፡

በመሆኑም ህጻናቱ በተበዳይነት ለምስክርነት ሲመጡ ከተመቻቸላቸው ቦታ በተጨማሪ የህፃናቱን ቃል በመቀበል ከዳኞች ጋር የሚያገናኙ የስነ ልቦና ባለሙያዎች ተቀጥረው በአግባቡ ፍትህ ሳይዛባ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛል፡፡

በተለይ አገናኝ ባለሙያዎች ለህጻናቱ ሊከብዱ የሚችሉ የህግ ቋንቋዎችን በመተርጎምና ህጻናቱ ሊረዱት በሚችሉት መንገድ በማቅረብ የህጻናቱን ቃል በመቀበል ለዳኞች በማቅረብ የፍትህ ስርዓቱ ላይ የህጻናቱ ምስክርነት ወሳኝ ሚና እንዲኖረው ያደርጋሉ››ብለዋል፡፡

ይህ ሁኔታ ከመፈጠሩ በፊት ህጻናቱ በመደበኛ ችሎት ቀርበው የመመስከር ግዴታ ነበረባቸው በዚህ ወቅትም ወንጀል የፈጸመባቸውን ሰው ፊት ለፊት ከማየት ንግግሩን የመስማትና በክርክር ወቅት አላስፈላጊ የሆኑ ንግግሮችን ድርጊቶችን በማየት የመረበሽና የመፍራት ሁኔታዎች ይስተዋልባቸው እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

በተለይ ከጾታዊ ጥቃት ጋር ተያይዞ በህጻናቱ ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በድብቅ እንደሚፈጸሙና ዋነኛ ተጠቂዎች እነሱ እንደመሆናቸው የምስክርነት ቃላቸው ለፍርድ ሂደቱ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑንና የነሱ የምስክርነት ቃል ያለመኖር በፍርድ ሂደቱ ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖ ቀላል አለመሆኑን ነው አቶ ልዑለስላሴ የሚናገሩት፡፡

የህፃናት ፍትህ አደረጃጀት ለህጻናቱም ሆነ ለፍትህ ስርዓቱ ከፍተኛ ለውጥ ያስገኘ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

በአሁኑ ወቅት የህጻናት ጉዳዮች እየተበራከቱ ነው፡፡ የሚሉ አስተያየቶች በስፋት ይነገራሉ ፤ ይህ ግን ተገቢ አይደለም ፋይሎች ሊበዙ ይችላሉ፤ ለመብዛታቸው አንዱና ዋነኘው ምክንያት የወንጀለኛው መቅጫ በህፃናትና ሴቶች ለይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመቅጣት የወጣው ህግ መሻሻል አንዱና ዋነኛው ምክንያት ቢሆንም የህብረተሰቡ ግንዛቤ እያደገ መምጣት ተደብቀው ይቀሩ የነበሩ ጉዳዮች አደባባይ እንዲወጡ እድል በመፈጠሩ መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡

ለአብነትም በጠለፋ ወንጀል የተከሰሰ አንድ ግለሰብ የጠለፋትን ሴት የሚያገባት ከሆነ ክሱ ይነሳ እንደነበር አስታውሰው አሁን ግን ቢያገባትም በመጥለፉ ብቻ ከህግ ሊያመልጥ እንደማይችል ህጉ ይደነግጋል፤ እንደነዚህ አይነት ሁኔታዎችም ወደ ፍርድ ሂደት የሚመጣውን የሚያበራክት ነው ያሉት፡፡

በ1949 ዓመተ ምህረት የነበረው የወንጀለኛ መቅጫ አንዲት ለአቅመ ሄዋን ያልደረሰችን ልጅ በማስገደድ የደፈረን ወንጀለኛ እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እስራት ብቻ እንዲቀጣ ይደነግግ እንደነበር አስታውሰው በዚህ ቅጣት አነስተኝነት ወደ ህግ የሚመጣው ፋይል ጥቂት ከመሆኑም ባሻገር የህብረተሰቡ ግንዛቤ አነስተኛነት ታክሎበት ተድበስብሰው የሚቀሩ ጉዳዮች ቁጥር ቀላል አለመሆኑን ያስረዳሉ፡፡

በ1996 ዓመተ ምህረት ወጥቶ በ1997 ዓመተ ምህረት ተግባራዊ የሆነው የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ግን እስከ ሀያ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንደሚያስቀጣ የተቀመጠ በመሆኑ መሻሻሉ ተጠቂዎች ጉዳያቸውን ወደ አደባባይ ለማውጣት ግፊት ማድረጉንም ነው ያስረዱት፡፡

ዛሬ ታድያ በሀገራችን የልጅ ነገር የሚለው ዘዬ ተቀይሮ ህጻናቱ የወደፊት ህይወታቸው ምን መልክ ሊይዝ እንደሚችል በነጻነት የሚተነብዩበት እንደ ህጻናት ፓርላማ የመሳሰሉ ፕሮግራሞች ተግባራዊ የተደረጉበት ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡

የህጻናት ኮንቬክሽን/የዓለም አቀፍ ስምምነት / በህፃናት ዙሪያ ተግባራዊ ሆኗል፡፡  የህጻናት ጉዳይ የሀገር ጉዳይ ሆኖ በሚኒስትር መስሪያ ቤት ደረጃ የሴቶችና ህጻናት ሚኒስቴር የተቋቋመበት  ሁኔታ እንዳለ እናያለን፡፡

ሀገር ተረካቢ ህጻናትን ከማንኛውም መጥፎ ድርጊቶች ለመከላከል እየተወሰደ ያለው እርምጃ እየተበረታታ መሄድ የሚገባው ነው እላለሁ፡፡ ቸር እንሰንብት

Last modified on Monday, 20 March 2017 16:59
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን