አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

"ይርጋ አለም" በሽግግር ጎዳና

18 Mar 2017
3702 times

መንበረ ገበየሁ (ከኢዜአ)

ዙሪያዋ በገራምባ ተራሮች፣ በወይማና ጊዳቦ ወንዞች የተከበበ ነው ፡፡ እንደ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ከተሞች የጠላት ወረራን ለመከላከል የሚያስችል አቀማመጥ መያዟ ለምስረታዋ ምክንያት መሆኑን መገመት አያዳግትም፡፡

በ1928 ጣሊያን ከ40 ዓመታት በኋላ ዳግም መምጣቱን ተከትሎ አለም በተናወጠበት በዚያ ወቅት የጠቅላይ ግዛቱ ገዢ ለነበሩት ራስ ደስታ ዳምጠው ምርጫ ሆነች፡፡

እናም እንዲህ ተባለ አሉ "ጊዜ ያመጣውን ጊዜ እስኪመልሰው ሃገረ ሰላምን ይርጋለም ወረሰው"፡፡

የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት መቀመጫ የነበረችው ሃገረ ሰላም የጠላትን ጦር ለመመከት ስትራቴጅክ ቦታ በነበራት ይርጋለም ተተካች ማለት ነው፡፡ 

አባባሉ በአሉታዊም በአዎንታዊም የተለያየ ትርጓሜ የተሰጠው ሲሆን አዎንታዊው የወቅቱን የጣሊያን ጦር ለመከላከል የሚያስችል ምቹ ቦታ ላይ መሆኗን የሚያሳይ መሆኑ ነው፡፡

በተቃራኒው ሃገረ ሰላሞች ከተማነቱን ተነጠቅን በማለት ቅሬታቸውን ያቀረቡበት ነው፡፡

ለጠቅላይ ግዛቱ መቀመጫነት ከመመረጧ አስቀድሞ የተቆረቆረችው ይርጋለም ስያሜዋን ያገኘችው ግን በጦርነቱ ሳቢያ ካለመረጋጋቱ ጋር በተያያዘ ነው፡፡

የጠቅላይ ግዛቱ ገዢ ራስ ደስታ ዳምጠው አለም እንድትረጋጋና እንድትሰክን ፣  መናወጡም እንዲያበቃ በመመኘት  ከተማዋን ይርጋአለም እንዳሉዋት ይነገራል፤፤

በጠቅላይ ግዛቱ ዋና ከተማነት እስከ 1960ዎች የቆየችው ይርጋለም በወቅቱ ከስድስት አውራጃዎች ለሚመጡ የ2ኛ ደረጃ ተማሪዎች የመጀመሪያ ተቀባይ በመሆን በዙሪያዋ ላሉ የእውቀት ማዕከልም ነበረች፡፡

በተለያዩ የመሰረተ ልማት መስኮች ቀዳሚነቷ ቢነገርም ጦርን ለመከላከል ታሳቢ ያደረገው አቀማመጧ ምቹ አለመሆኑ በተራዋ ከተሜነቷን በሃዋሳ እንደትነጠቅ አድርጓታል፡፡

ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን ፈልገው ለመጡ ማዕከል የነበረችው ይርጋለም የተለያየ ቋንቋ፣ታሪክና ባህል ያላቸውን ተማሪዎች ማስተናገዷ የፈጠረው የእውቀት ሽግግር ለስልጣኔና ለጥበብ ቅርብ አድርጓታል፡፡

እናም ከትውልድ ቦታቸው ይልቅ ትምህርት ፍለጋ መጥተው እውቀት በቀሰሙባት ከተማ ይርጋለም  የሚታወቁ  ምሁራንና የጥበብ ሰዎችን አፍርታለች፡፡

ዛሬ ደግሞ ለአለም የሚደርስ፣ የሃገር ኢኮኖሚን የሚያሳድግ፣ ከግብርና ወደ ኢንዱሰትሪ የሚደረገውን መዋቅራዊ ሽግግር የሚያፋጥነው ቴክኖሎጂ ለማበርከትና ለማስተዋወቅ ቀዳሚ ሆናለች፡፡ 

ከአዲስ አበባ በ317 ኪሎ ሜትር ከሀዋሳ ደግሞ በ42 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ይርጋለም በአቅራቢያዋ በሚገኙ ዌኔናታና ሂዳ ቃሊቲ ቀበሌዎች በሚዋሰነቡትና 1ሺ ሄክታር በሚሸፍነው የተጠንጣላለ ሜዳማ መሬት በርካቶችን ተቀብላለች፡፡

 ሃገራቸው ወደ ኢንዱስትሪው መሸጋገሪያዋን በማየታቸው የተደሰቱ በርካቶች ናቸው ፡፡

በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን ከሚገኙ አራት ከተማ አስተዳደሮች አንዷ የሆነችው ይህችው ቀደምትና እድሜ ጠገብ ከተማ በዙሪያዋ በቡናና በተለያዩ ፍራፍሬዎች የታወቁ አርሶአደሮችን አፍርታለች፡፡

እነዚሁ የአካባቢው አርሶአደሮች የሰሙት የምስራች ደስታ ፈጥሮባቸው እንግዶቻቸውን ሊቀበሉ ማልደው ነው የተነሱት፡፡

አርሶአደር ማሞ ለማ እንደነገሩን ከሆነ የምስራቹን ከሰሙ ጊዜ ጀምሮ ጨዋታቸው ሁሉ ተቀይሯል ። ከበራቸው ድረስ የመጣው ልማት ከእነሱ አልፎ የሌሎችን አቅም የሚጠይቅ በመሆኑ ከጎረቤቶቻቸው መመካከር ከጀመሩም ሰነባብተዋል፡

መጋቢት 5 ቀን 2009 ዓ.ም የእለቱን እንግዳ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ሃይለማርያም ደሳለኝን  ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና ባለሃብቶችን የአካባቢው ማህበረሰብ በፍቅርና በላቀ የደስታ ስሜት ነበር የተቀበላቸው 

የመምጣታቸው ሚስጥር ለይርጋለም አካባቢ አርሶአደሮች ብቻ ሳይሆን የደቡብን ምስራቃዊ ክፍል ይዞ ለሲዳማና ጌዲኦና በመቶ ሜትር ርቀት ለሚገኙ ከፊል የኦሮሚያ አካባቢዎችና ለሃገሪቱ ጭምር የሚጠቅም የምስራች ለማብሰር ነው፡፡

የአርሶ አደሩን የተለያዩ የግብርና ምርቶች እሴት ጨምሮ በማቀነባበር ለአለምና ለሃገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመሰረት ድንጋይ  ለማስቀመጥ፡፡

የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ 1 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍን ሲሆን 215 ሄክታሩ በቅድሚያ የሚለማ ነው፡፡

ፓርኩ በ100 ኪሎ ሜትር ርቀት በ10 ሄክታር ላይ የሚያርፉ ስድስት መጋቢ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ማዕከላት የሚኖሩት ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃና መለስተኛ የግብርና ምርቶችን የማበጠር፣ የመለየትና የማቀነባበር ስራ ይከናወንበታል፡፡

የትራንስፎርሜሽን ማዕከላቱ በዲላ ዙሪያ፣ ይርጋጨፌ፣አለታወንዶ፣ ዳዬ ፣ቡሌና ሸበዲኖ ወረዳዎች የሚገነቡ ሲሆን የዲላ ዙሪያው በዚህ ዓመት ግንባታው ይጀመራል፡፡ 

ምርቱ ባለባቸው የተለዩ አካባቢዎች ደግሞ  በየቀበሌው ጥራቱን በጠበቀ ደረጃ ዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያ ትላልቅ መጋዝኖች ያላቸው ማዕከላት ይገነባሉ፡፡

እነዚህ ማዕከላት የአርሶአደሩን ምርቶች በቀጥታ የሚሰበስቡና ለገጠር ትራንስፎርሜሽን ማዕከላት የሚመግቡ ናቸው፡፡

ፓርኩ ከእንስሳት ተዋጽኦ ስጋና ወተት፣ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎች፣ ቡናና ማር ከአርሶአደሩ ተቀብሎ እሴት ጨምሮ በማቀነባበር ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለአለም ገበያ በማቅረብ የሃገሪቱን የውጭ ምንዛሪ የማሳደግ አቅሙ ከፍተኛ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

በቦታው የደረሱት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ለይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንድስትሪ ፓርክ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከማኖራቸው አስቀድሞ በአርሶደሩ ጥረትና ልፋት የተገኘ ውጤት ነው ሲሉ ለአርሶአደሮቹ እውቅና ሰጥተዋል፡፡

ከ25 ዓመት በፊት የመጀመሪያው የግብርና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ሲጀመር ከቤቱ ፍጆታ የማይበልጥ ምርት ያመርት የነበረው አርሶአደር ዛሬ ትርፍ አምርቶ የግብርና ምርቶችን በማቀነባበር እሴት ጨምሮ ለአለም ገበያ ለመላክ የሚያስችል አቅም በአገሪቱ እንዲፈጠር ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

በደቡብ ምስራቃዊ ክፍል የሚገኙ አርሶአደሮች በአለም በጣዕሙ የተለየውን ቡና በማምረት የሚታወቁ በመሆናቸው ቡናቸው በጥሬው ለሌሎች ሲሳይ መሆኑ ቀርቶ በጓሮዋቸው ተቀነባብሮ እሴት ሊጨመርበት በመሆኑ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋቸዋል፡፡

በአካባቢው ከቡና በተጨማሪ የአናናስ፣ የእንሰትና የስጋ ሃብት ያለ በመሆኑ ምርታማነቱን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ ለፓርኩ ጥሬ እቃ ማቅረብ ያስፈልጋል ሲሉም አሳስበዋል፡፡

በፓርኩ 80 ከመቶ የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች የሚገቡበት ሲሆን የእውቀት ሽግግሩን ለመቅሰም እንዲያስችል 20 ከመቶ ለውጭ ባላሀብቶች እድል ይሰጣል፡፡

መንግስት የሃገር ውስጥ ባለሃብቶችን ለማበረታታት 80 ከመቶ ብድር ከልማት ባንክ ያመቻቻል ። እስከ 10 ዓመት የሚቆይ የታክስ እፎይታና ከውጭ የሚመጡ ባለሙያዎችን እስከመቅጠር ዝግጅት አድርጓል ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

የፌደራል ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር መብራህቱ መለስ እንደተናገሩት ደግሞ ፓርኩ ኢንዱስትሪ ተኮር፣ ማህበራዊና አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማቶች የተሟላለትና የአንድ መስኮት አገልግሎት የሚሰጥበት ነው፡፡

ግንባታው ተጠናቆ  ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር  በየዓመቱ ከ233ሺ ቶን በላይ የተለያዩ ምርቶችን በማምረት ከ 6 ነጥብ 2 ቢሊየን  ብር በላይ ገቢ ያስገኛል ብለዋል፡፡

1ሺ ሄክታር የሚሸፍነው የፓርኩ ይዞታ በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ይለማል ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው ቀድሞ በሚለማው ሁለት መቶ አስራ አምስት ሄክታር 400 ሺህ የሚደርሱ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ይፈጠርላቸዋል፡፡

ፓርኩ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ኢኮኖሚያዊ ሽግግር የሚያፋጥን ሲሆን የይርጋለሙን ጨምሮ በሀገሪቱ 17 የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የቀጣይ ዓመታት እቅዶች ናቸው፡፡

በአማራና በትግራይ ክልል ባለፉት ወራት የመሰረት ድንጋይ የተጣለላቸው ተመሳሳይ ፓርኮችም ወደ ግንባታ ስራ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡

ፓርኩ የሚገነባበት ቦታ በአለም ደረጃ ታዋቂ የሆነው የሲዳማ፣ ጌዲኦና ይርጋጨፌ ቡና የሚመረትበት መሆኑን ያስታወሱት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ  ለዘመናት በጥሬ የሚላከው ቡና እሴት ተጨምሮበት የሃገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ አቅም መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡

የግብርናውን ዘርፍ መዋቅራዊ ሽግግር ለማረጋገጥና ዘላቂነት ያለው ለውጥ ለማምጣት ለአምራች ኢንዱስትሪው በግብዓትነት የሚያገለግሉ ምርቶችን መጠን፣ጥራትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በዚህም የዘርፉ ተዋናይ የሆኑ የክልሉ ባለሃብቶችም ሆነ ወደ ባለሃብትነት ለተሸጋገሩ ሞዴል አርሶ አደሮች ምቹና የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የምስራቹን ከሰሙ ጊዜ ጀምሮ መመካከር የጀመሩትን አርሶአደር ማሞን ጨምሮ የሲዳማና ጌዲኦ ዞን አርሶ አደሮች በክልሉ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ባላሃብቶች እድለኞች መሆናቸውን ተናገሩ፡፡

የወንዶ ገነት ነዋሪውና በ2000 ዓ.ም በሞዴልነት የተሸለሙት አርሶአደር ማቲዎስ ሊጋሞ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ ከብት የማርባት ልምድ ቢኖራቸውም አሁን አሁን ግን የተዳቀሉ ዝርያዎችን መጠቀም በመጀመራቸው ምርታማነታቸው እያደገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እሳቸውን ጨምረው በዚሁ ዘርፍ ከተሰማሩ 28 ጓደኞቻቸው ጋር ተደራጅተው በቀን እስከ 500 ሊትር የሚደርስ ወተት ለገበያ ማቅረብ የጀመሩ ሲሆን ተቀባይ ሲጠፋ የሚበላሸው ምርታቸው ዋጋ የሚያገኝበት ጊዜ በመቃረቡና በአካባቢያቸው በመፈጠሩ እድለኞች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የአማ የወረቀትና ወረቀት ማምረቻ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለቤት አቶ አንድነት ጌታቸው ወረቀት የሚያመርቱበት የፐልፕ ምርት ከውጭ ለማስገባት በየዓመቱ ከ20 እስከ 30 ሚሊየን ዶላር ከመንግስት ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚያመጡ ተናግረዋል፡፡

የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ኢንዱስትሪ ፓርክ በሃገር ውስጥ ማምረት ሲጀምር ቢያንስ ከ30 ከመቶ በላይ ቅናሽ ሊኖረው እንደሚችልና ምርቱን ለማምጣት ቻይናና ኢንዶኔዥያ ድረስ በመሄድ የሚባክነውን ጊዜም ይቀንሳል ብለዋል፡፡

በቀጣይ የማቀነባበር ስራው ሲጠናከር ከውጭ የሚገባውን ከማስቀረት ባለፈ መላክ የሚያስችል አቅም ይፈጥራል ባይ ናቸው፡፡ 

የአማሮ ጋዮ ቡና ላኪ ድርጅት ስራ አስኪያጅና ባለቤት ወ/ሮ አስናቀች ቶማስ ከዚህ ቀደም በጥሬ የሚልኩት ቡና እሴት ተጨምሮበት የሚላክበት እድል የሚፈጥር በመሆኑ ምርታቸው ተገቢውን ዋጋ እንደሚያገኝ በማመናቸው ደስተኛ ሆነዋል፡፡

ምርቱ ከአርሶአደር ማሳ የሚሰበሰብ በመሆኑ በጥራት ለማምረት ባለሃብቱ ከአርሶአደሩ ጋር በቅንጅት በመስራት የሃገሪቱን ኢኮኖሚ በማሳደግ ተጠቃሚ መሆን አለበት ብለዋል፡፡

ቡና እየነገዱ ባደጉበት የትውልድ ቀያቸው የፓርኩ መገንባት ያስደሰታቸው ቡና አቅራቢና ላኪ ድርጅት ባለቤት አቶ ዘላለም ወልደአማኑኤል ድርጅታቸው ከዚህ ቀደም በጥሬ ለሃገር ውስጥና ለአለም ገበያ የሚልካቸው ምርቶች በፓርኩ እሴት ተጨምሮበት መላኩ ሃገሪቱ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ ያሳድጋል፡፡

የሃብቱ ባለቤት የሆነው አምራች አርሶአደር ተገቢውን ጥቅም አግኝቶ የአካባቢውን ስያሜ የያዘ ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እድል የሚፈጥር ፓርክ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፓርኩ የሚገነባበት የሲዳማ ዞን ብቻ ከ141ሺህ ሄክታር በላይ መሬቱ በቡና የተሸፈነ ነው፡፡ ከ29 ሺ ሄክታር በላዩ ደግሞ በተለያዩ አትክልቶችና ፍራፍሬዎች ፡፡

ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኘው ቡናን በዓመት ከ100 ሺህ ቶን በላይ ማቅረብ የሚያስችል አቅም እንዳለውም በጥናት ተለይቷል፡፡

እስከ አሁን እየቀረበ ያለው ግን ከፍተኛው 40 ሺህ ቶን ብቻ በመሆኑ በሞዴል አርሶአደሮች ጓሮ በሄክታር እስከ 31 ኩንታል የሚለማውን ቡና በሌሎቹ አርሶአደሮች በማስፋት ኢንድስትሪው የሚፈልገውን ምርት የማምረት ስራ ማጠናከር ይጠይቃል፡፡

ለዚህ የንቅናቄ ስራ መጀመራቸውን የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና እርሻና ተፈጥሮ ሃብት መምሪያ ሃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ ነግረውናል፡፡

ቀደምት ከሆኑ የሃገሪቱ ከተሞች ተርታ የምትነሳው ይርጋለም የጥንቱን የእውቀትና የስልጣኔ ማዕከልነት ዳግም የምታድስበት የመሸጋገሪያ ጎዳና ላይ ትገኛለች፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን