አርዕስተ ዜና

“ባሌ” ን - እናድነው !

17 Mar 2017
3306 times

ገብረህይወት ካህሳይ (ኢዜአ)

የድሬ ሼክ ሁሴን አገር ፣ የሶፍ ዑመር ዋሻ ባለቤት ፣ የስንዴና ገብስ አውድማ ፣ የባሌ ተራሮች  ብሄራዊ ፓርክ ባለቤትና የጥቅጥቅ ደን እምብርት  - ባሌ ። ስፍራው በበርካታ የተፈጥሮ ፀጋዎች የታደለና ብርቅና ድንቅ ሀብቶች አቅፎ የያዘ   ነው ።

ከባሌ ሀብቶች መካከል የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን  ይዘት መመልከት ዞኑ ምን ያክል ትኩረት የሚስብ አካባቢ እንደሆነ  መገንዘብ ይቻላል ። ፓርኩ በቀጥታ የ15 ሚሊየን ሰዎች የህይወት መሰረት ነው ።

ከሰንሰለታማ የፓርኩ ተራሮች 40 ወንዞች ቁልቁል ወርደው ሸበሌን ጨምሮ ወደ አምስት ትላልቅ ወንዞች ይገባሉ ። ወንዞቹ እስከ ታችኛው የኢትዮ ሱማሊያና ኬኒያ ምድር ይዘልቃሉ ። በሶማሊያ የሚካሔደው ሰፋፊ የሙዝ እርሻ ጭምር ከባሌ ፀጋዎች የተገኘ ትሩፋት ነው ።

በአገራችን ብቻ የሚገኘው ቀይ ቀበሮ ማእከሉ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ነው  ማለት ይቻላል።  እየተመናመነ የመጣው አገራዊ የቀይ ቀበሮዎች ቁጥር 450 ብቻ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ ። ከዚህ ቁጥር ውስጥ 300 የሚሆኑት በባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ውስጥ የሚገኙ ናቸው ።

ቀሪዎቹ በአርሲ ተራሮችና በሰሜን ተራራ ብሄራዊ ፓርክ ይገኛሉ ። ዋናው የቀይ ቀበሮ ምድር ባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ግን አስከፊ አደጋ ተደቅኖበታል ። ቀይ ቀበሮዎቹ ጨርሰው እንዳይጠፉ ያሰጋል ። ባለፈው ዓመት በአካባቢው በተነሱ ሁለት ዓይነት የውሻ በሽታዎች ምክንያት 100 ቀይ ቀበሮዎች ሞተዋል ።

የባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ሃላፊ አቶ ሻሚል ከዲር እንዳሉት  በፓርኩ ውስጥ 1ሺህ 600  ለመድሃኒት ጭምር የሚያገለግሉ እፅዋቶች አሉ ። 160 እፅዋቶች በፓርኩ ብቻ የሚገኙ ናቸው ። እነዚህ ግን ከፊት ለፊታቸው አደጋ እያንዣበበ ነው ።

ፓርኩ የ78 አጥቢ እንስሳት ባለቤት ሲሆን 20ዎቹ  የአገራችንና የፓርኩ ብቸኛ ሀብቶች ናቸው ። ከ310 ብርቅና ድንቅ አእዋፋት መካከል ደግሞ 6ቱ መገለጫዎቹ እንደሆኑ ሃላፊው ይናገራሉ ። አደጋው ካልተቀለበሰ እነዚህም ለአደጋ ተጋልጠዋል ።

ከቀይ ቀበሮ በተጨማሪ የደጋ አጋዘን ፣ የሚኒሊክ ድኩላ ፣ የባሌ ጦጣና ትልቁ ፍልፈል የመሳሰሉ ድንቅ የዱር እንስሳት በውስጡ የያዘው የባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በአገራችን ከኢሉ አባቦራ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠውና በጫካ ቡናውና በመድሃኒት እፅዋት ጭምር የሚታወቀው የሀረና ጥቅጥቅ ደን ባለቤት ነው ። ጫካውም ቢሆን አሳሳቢ አደጋ አላጣውም ።

በእያንዳንዱ የፓርኩ ተፈጥሮ ሀብት የተደቀነው አደጋ መንስኤው ህገ ወጥ ሰፈራ ፣ ልቅ የእንስሳት ግጦሽ ፣ ሰደድ እሳትና የእብድ ውሻ በሽታዎች  መሆናቸውን ሃላፊው አቶ ሻሚል ከዲር ተናግረዋል ።

በፓርኩ ይዞታ ውስጥ ሪራ ፣ ጨፌ ደራና ገራምባ ጎራ የሚባሉ የሰፈራ ቀበሌዎች ተፈጥረዋል ።  ቀበሌዎቹ በመንግስት በጀት ጭምር ውሃ ፣ ትምህርት ቤት ፣ የጤና ተቋማት ፣ መንገድ የመሳሰሉት የመሰረተ ልማት እንዲሟላላቸው ተደርጓል ። ነዋሪዎቹን ከፓርኩ ክልል ለማስወጣትም ሆነ ባሉበት እንዲቀጥሉ ለማድረግ የግድ ህብረተሰብን ያሳተፈ የመንግስት ውሳኔ ያስፈልገዋል ።

ሌላው አሳሳቢ ችግር ከብት አርቢዎች 800 ሺህ የሚጠጉ የቤት እንስሳት ይዘው ወደ ፓርኩ መግባታቸው ነው ። እንስሳቱ በሀሬና ደንና በሰናቴ ከፍተኛ ቦታዎች በልቅ ግጦሽ ተሰማርተው በአእዋፋት ፣ በእፅዋትና በአጥቢ እንስሳት አኗኗር ላይ አሉታዊ ተፅእኖ በማሳደር ላይ ይገኛሉ ።

የአካባቢው ነዋሪዎች ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ጋር ተያይዞ በየሶስት ዓመቱ የሚለኩሱት ሰደድ እሳት ደግሞ በደንና የዱር እንስሳትን ሰላም በማናጋት ጉዳት እያደረሰ ነው ። ከእንስሳት ጤንነትና ምርታማነት ጋር ተያይዞ ጠቃሚ ነው ተብሎ የሚታመንበት የተወሰነ ተክል በእሳት የማቃጠል ልማድ የሰው ህይወት ጭምር እየቀጠፈ መሆኑን ሃላፊው አስረድተዋል ።

በ1962 ዓ.ም የተቋቋመው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ህጋዊ ሰውነት አግኝቶ የራሱ የሆነ የባለቤትነት መብት ያረጋገጠው በቅርቡ መሆኑ ደግሞ ችግሮቹ እየተበራከቱ እንዲመጡ አንዱ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል ።

ለ15 ሚሊዮን ህዝብ ስነ ምህዳራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ የሚሰጠው ይሄው ፓርክ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2008 በተባበሩት መንግስታት የትምህርት ፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ ) በጊዜአዊ ቅርስነት ተመዝግቦ ነበር ። እስከ አሁን ድረስ በቋሚ ቅርስነት አለመመዝገቡ ደግሞ በባሌ ህዝብ እንደ አጠቃላይ በኦሮሞ ህዝብ ቅሬታ ማሳደሩን በየመድረኩ እየተገለፀ ነው ። እንደ አንድ የመልካም አስተዳደር ችግር ተደርጎም እየተነሳ ነው ።

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳውድ ሙሜ ፓርኩ በቋሚ ቅርስነት አለመመዝገቡ የሚነሳው ቅሬታ ተገቢ ነው ብለው ያምናሉ ። ለማስመዝገብ ደግሞ ከመንግስት ሶስት ዋና ዋና ቅድመ ተግባራት አሉ ባይ ናቸው ።

ቀዳሚው የብሔራዊ ፓርኩን ወሰን በህዝብ ተሳትፎ በማካለል የህዝብንና በተዋረድ የሚገኙ አካላት ይሁንታ ካገኘ በኋላ የህግ ማእቀፍ በማዘጋጀትና በማጽደቅ ህጋዊ ሰውነት እንዲያገኝ ማድረግ ነው ። ይህ አሁን በአግባቡ ተከናውኗል ።

ሁለተኛው የብሔራዊ ፓርኩን አጠቃላይ ፊዚካልና ስነ ህይወታዊ ይዘቶችን ትንተና (Nomination File ) ማዘጋጀት ሲሆን ስራው ተጀምሮ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል ብለዋል ።

ሶስተኛው ደግሞ የብሄራዊ ፓርኩ ስርዓተ አያያዝ እቅድ ( Management  Plan) ማዘጋጀትና ማፀደቅ ሲሆን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ። እናም የህዝቡ ቅሬታ በቅርቡ እልባት የሚያገኝ ይሆናል ።

በስነ ምህዳራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታው ከኢትየጵያ ብቻ ሳይሆን ከአፍሪካም ጭምር ቀዳሚ የሆነው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከተደቀኑበት አደጋዎች ነፃ ለማድረግ ዘላቂ መፍትሄ እንደተዘጋጀለትም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል ።

የተዘጋጀው የ10 ዓመት አጠቃላይ የፓርኩ አስተዳደር እቅድ አምስት ፕሮግራሞችን አቅፎ የያዘ ነው ። በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ችግር መፍታት ፣ ልቅ ግጦሽና ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ፣የቱሪዝም ልማት ፣ የማህበረሰብ ልማትና የስነ ምህዳር ጥናት ፕሮግራሞችን ያካተተ ነው ።

እቅዱን አፀድቆ ወደ ተግባር ለመግባት በመጨረሻ ምእራፍ ላይ እንደሚገኝ  የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ እጅ ለእጅ ተያይዘን ፓርኩን ማልማትና መጠበቅ ከቻልን ሀገራዊ ፋይዳው የላቀና በቱሪዝም ኢንዱስትሪ እድገታችን ገንቢ ሚና የሚጫወት ይሆናል ብለዋል ።

ከወዲሁም አምስት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተግባራዊ ምላሽ መስጠት ጀምረዋል ።

ተቋማቱ በባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በጋራ ተባብረው ለመስራት ሼር ፕሮጀክት የሚል የጋራ ስያሜ ፈጥረው ወደ ተግባር ገብተዋል ። የሼር ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አሳዬ አስናቀ እንደገለፁት  የ40 ወራት እቅድ ነድፈውና 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ በጀት መድበው እየሰሩ ነው ።

ተቋማቱ በፓርኩ ላይ ከሚሰሯቸው ተግባራት መካከል የአቅም ግንባታ ፣ የጥናትና ምርምር ፣ የማህበረሰብ ተጠቃሚነት ፣ የቴክኒክ፣ የሎጂስቲክና የፋይናንስ እገዛ ያከተተ ሲሆን 873 ሺህ ሰዎች በቀጥተኛ ከ12 እስከ 15 ሚሊዮን ለሚደርሱ ሰዎች ደግሞ በተዘዋዋሪ መንገድ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል ።

መንግስት ሃላፊነቱን ለመዋጣት ደፋ ቀና እያለ ነው ። ማህበረሰቡም የፓርኩን ልማት አጥብቆ ይፈልገዋል ። ባለድርሻ አካላት ደግሞ የድርሻቸውን ለማበርከት ወደ ተግባር ገብተዋል ። ሁሉንም የየራሱ ሃላፊነት ከተወጣ ፓርኩ ከስጋትና ከአደጋ ማዳንና መጠበቅ ይቻላል ።

የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አገራዊ ጠቀሜታው ለዘላቂ ልማት ስትራተጂያችን አጋርና የቱሪዝም ዋና መዳረሻ እንደሚሆን አያጠራጥርምና ልንጠብቀውና ልናለማው ይገባል ።

       

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን