አርዕስተ ዜና

በቻይና-አፍሪካ ትብብር ውስጥ የቻይና-ኢትዮዽያ ምጣኔ ሃብታዊ ተጠቃሚነት

17 Mar 2017
3349 times

በሀብታሙ አክሊሉ (ኢዜአ)

በቻይና አፍሪካ የትብብር ስምምነት በርካታ የስራ ዕድሎች በአፍሪካ ተፈጥረዋል፤ የሃገር ውስጥ አኮኖሚ እንዲተዋወቅ ረድቷል፤ የፖለቲካና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች መረጋጋትን አምጥቷል፤ በተዘበራረቀ መልኩ ይፈጠር የነበረውን የስደተኝነትና የስደተኞች ፍልሰት እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል።

ኢትዮዽያና ቻይና በፕሬዚዳንት ዢ ቺን ፒንግ የቻይና አፍሪካ ፎረም ላይ ሃሳብ በተለዋወጡበት አስር የትብብር መርሃ ግብሮች መሰረት የልማት ስትራቴጂዎቻቸውን እየፈፀሙ መሆኑን ያስነበበው ፒፕልስ ዴይሊ ሁኔታው ኢትዮዽያን ፈጣን ኢኮኖሚ እንድታስመዘግብ እንደረዳት ፅፏል። 

ያላደገ የመሰረተ ልማት ሁኔታ፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት፣ የፋይናንስ ምንጭ አለመኖር በኢትዮዽያ የልማት ስራን ለመተግበር ማነቆ የሆኑ ችግሮች መሆናቸውን ከግምት ባስገባ መልኩ የቻይና-ኢትዮዽያ ትብብር ለመሰረተ ልማቶች መሻሻል፣ ለኢንዱስትሪያል ፓርኮች ግንባታና ለሰው ሃብት ልማት ቅድሚያ የሰጠ እንቅስቃሴን በማድረግ ተከታታይ የሆኑ አመርቂ ውጤቶች እንዲመዘገቡ አድርጓል። በዚህም አዲስ አበባ-ጂቡቲ የባቡር መስመርን በቻይናውያን ቴክኖሎጂ፣ መሳሪያና ስታንዳርድ መሰረት በማጠናቀቅ ለትራፊክ ክፍት እንዲሆን ተደርጓል። የባቡር መስመሩም የኢንዱስትሪያል ፓርኮቹን አፈፃፀም የተሳለጠ ከማድረግ ባሻገር በመስመሩ የተገናኙ ሃገራትን ለብልፅግናና ለጋራ ልማት እንዲበቁ ያደርጋቸዋል። የጊቤ lll የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብን በመገንባት ወደ ስራ በማስገባት በሃገሪቱ የሃይል ማመንጨት ሂደቱ በእጥፍ እንዲያድግ አስችሏል።   

ኢትዮዽያን ስኳርን ወደ ሃገሯ ከማስገባት ራሷን ችላ ወደ ውጭ እንድትልክ በሚረዱ የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ ሂደት ላይ የቻይናውያን ድርጅቶች በስፋት እየተሳተፉ ይገኛሉ። በየዕለቱ 1 ሺ 200 ቶን የአዲስ አበባ ከተማን ቆሻሻ በመጠቀም ሃይል ለማመንጨት በግንባታ ላይ የሚገኘው በአፍሪካ የመጀመሪያ በሆነው የቆሻሻ ሀይል ማመንጫ ግንባታ ረገድም የቻይናውያን እገዛ ሊጠቀስ የሚችል ነው። በፕሮጀክቱም ቻይናውያን የኤሌክትሪክ ሃይል ከማመንጨት ባሻገር ከተማዋን ከአካባቢ ብክለት ነፃ በማድረግ የሀገሪቷን ብሎም የአህጉሪቷን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ትደግፋለች። የቻይና-ኢትዮዽያ ትብብር እገዛ ኢትዮዽያውያንን ከድህነት በማውጣቱ ሂደት የሚገለፅ ብቻም ሳይሆን የሃገሪቷን ቢዝነስና ኢንቨስትመንት በማሻሻል የውጭ ባለሃብቶች ወደ ሃገር ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ ሁኔታዎችን ያመቻቸም ነው። በቻይና አፍሪካ ትብብር ማዕቀፍ ውስጥ ያሉ ተግባራትን የሃገሪቱ የልማት አጋሮች በተገቢው እንዲተገብሩት ማድረግም ከትብብሩ ትሩፋቶች መካከል ይጠቀሳል። የኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር መስመር የዕቃ ትራንስፖርት ዋጋን በመቀነስ ህብረተሰቡን የማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ህይወት ተጠቃሚ ያደርገዋል። የትራንስፖርት ኮሪደሩም ሁለቱ ሃገራት በመሰረተ ልማት ግንባታውም ሆነ በኢንዱስትሪያል ልማቱ እያስመዘገቡ ያለውን ስኬት ያሳያል።         

በቻይናውያን ኩባንያ ግንባታ የተደረገለት የሃዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የቻይና-ዩ ኤስ አሜሪካ-ኢትዮዽያ አዲስ የሶስትዮሽ ግንኙነት ሞዴልን ያስተዋወቀ ነው። የጊቤ III የሃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ደግሞ የቻይናውያን የኤሌክትሪካልና ሜካኒካል ዕውቀትና መሳሪያ ከጣሊያናውያን የሲቪል ኢንጂነሪንግ ዕውቀትና ክህሎት ጋር ተቀናጅቶ የተፈጠረ የልማት ውጤት ነው። የአዲስ አበባው የቆሻሻ ሃይል ማመንጫም በቻይናውያን፣ በእንግሊዛውያንና ኢትዮዽያውያን ባለሙያዎች ትብብር የሚከናወን ነው። የቻይናውያን የኢኮኖሚ ትብብር የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ አዲስ አስተሳሰብ ለሌላው ዓለም ያስተዋወቀ ነው።

ያለፉት 30 አመታት የቻይናን የኢኮኖሚ ማሻሻያና ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ጉዞን በጥቅሉ ስንመለከተው ሁለት ምስጢራትን ማግኘት እንችላለን። የመጀመሪያው ራስን ችሎ መቆምና ጠንካራ ስራ ሲሆን፤ ሁለተኛው ግን ሌሎችን እንዲጠነክሩ በማገዝ በዓለም አቀፉ የኢንዱስትሪ ሰንሰለት ውስጥ የራስን ትክክለኛ ቦታ ፈልጎ ማግኘት ነው። ይህም ለኢትዮዽያ የምጣኔ ሃብት ዕድገት የራሱን መነሳሳት ፈጥሯል። በአሁኑ ወቅትም ቻይና ኢኮኖሚያዊ መዋቅሯን እንደገና በማየትና ኢንደስትሪዎቿንም ካለፈው በረቀቀ መልኩ በማሻሻል ሂደት ላይ ስትገኝ የአፍሪካ ሃገራት ደግሞ  ወደ ኢንዱስትሪያላይዜሽን እና ዘመናዊነት ለመለወጥ ጠንክረው እየሰሩ ይገኛሉ። ይህም ሁኔታ ለሁለቱም ወገኖች ከዚህ ቀደሞ ያልተመዘገበ ልዩ ልማታዊ ታሪክን ለማስመዝገብ የሚረዳቸውን ዕድል ያመጣላቸዋል።                                                           

ቻይና ሃገራትን በመሰረተ ልማት  እያስተሳሰሩ ተጠቃሚ የሚያደርግ ዋን ቤልት ዋን ሮድ የሚል ሃሳብን በማቅረብ ወደ ተግባር የመተርጎም ስራንም ጀምራለች። ይህ አዲሱ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ሀሳብ ሃገራት በጋራ መጠቃቀም ውስጥ የራሳቸውን ምጣኔ ሃብት በማሳደግ የራሳቸውንም ዕጣ ፈንታ የሚወስኑበት ነው። ሃሳቡም የአፍሪካ ሃገራትን ጨምሮ በሌሎች በርካታ  ሃገራትም ተቀባይነትን አግኝቷል። ቻይናም በዋን ቤልት ዋን ሮድ በሰሜንና በደቡበ ሃገራት መካከል ያለውን የምጣኔ ሃብት ክፍተት በማጥበብ በዓለማችን ላይ የተመጣጠነ ልማትን ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ውስጥ አስፈላጊውን ሚና እየተጫወተች ትገኛለች።

በሌላም በኩል ቻይና የአፍሪካን የመምህራን ማሰልጠኛ ተቋማትን በማጠናከር በዘርፉ ያለውን የትምህርት ጥራት ችግር ለመቅረፍ ሰፊ ሚናን እየተጫወተች እንደሆነ አንድ የመንግስታቱ ድርጅት ሃላፊ መናገራቸውን ከሰማን ቀናትም አልተቆጠሩም። በምስራቅ አፍሪካ የዩኔስኮ ዳይሬክተር የሆኑት ቴሬሴ ንዶንግ ጃታ ስለ ዕገዛው ውጤታማነት ለመመስከር ዩጋንዳን ማየቱ ብቻ በቂ ነው ብለዋል።

ቻይና በዩኔስኮ በኩል 8 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ በማድረግ ኢትዮዽያን ጨምሮ በኮትዲቯር፣ በናሚቢያ፣ በዲሞክራቲከ ኮንጎ፣ በላይቤሪያ ፣በኮንጎ፣ በታንዛኒያና ዩጋንዳ ለሚገኙ የመምህራን ማሰልጠኛዎች እገዛ ማድረግዋን መረጃውን ያወጣው ዢንዋ ዘግቧል። የመጀመሪያና ከፍተኛ ደረጃ ትምህርትን ለማሳደግ እገዛ እያደረገች የምትገኘው ቻይና በትምህርት መስክ እያደረገች የሚገኘውን ድጋፍ ማሳደግን ታላሚ ያደረገ ስብሰባ በጅቡቲ ለማካሄድ ዝግጅት ማጠናቀቋን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ቻይና በቅርቡ ባካሄደችው 19ኛው የብሄራዊ ኮንግረስ ስብሰባ ላይ በቀጣይ የኢኮኖሚ ዕድገትዋ 6.5 እና በላይ ሊቀጥል እንደሚችል ይፋ አድርጋለች። ይህም የአሃዝ ትንበያ በበርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ተቀባይነትን አግኝቶላታል። የቻይና ኢኮኖሚ ምንም እንኳ ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት ባያሳይም አሁንም ግዙፍና ጠንካራ ነው ሲል ብሉምበርግ ምስክርነቱን ሰጥቷል። ዘጋቢው ሲቀጥልም 11 ትሪሊዮን ዶላር ጠቅላላ ሃብትን ባለፈው አመት ያስመዘገበችው ሃገረ ቻይና ለዓለም አቀፍ ሃገራት ጂዲፒ ዕድገት አስተዋፅኦ በማድረግ የሚደርስባት ሃገር እንደሌለም ፅፏል።   

የያዝነው የፈረንጆች አመት 2017 ቻይና በዋን ቤልት ዋን ሮድ ጉዳይ ዙሪያ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ለብሪክስ ሃገራት ሁለት ታላላቅ ስብሰባዎችን በማዘጋጀት ስለአፈፃፀሙ የምትመክርበት ወሳኝ አመት እንደሆነ የፒፕልስ ዴይሊ ፀሃፊ አፅንኦት ሰጥቶታል። በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ መሪነት ጉዳይና በአፍሪካ ልማት ላይ ሁለቱ ስብሰባዎች መሰረታዊ ሊሆኑ የሚችሉ ሃሳቦች ይነሱባቸዋል ተብሎም ተጠብቋል። የቻይና-አፍሪካና የቻይና-ኢትዮዽያ ትብብሮች በጋራ ልማት ዙሪያ ሌላው ዓለም ሊፅፈው የሚችል ተጨማሪ አዲስ ምዕራፍ ይከፈትበታል ሲል በድረ ገፁ አስፍሯል።    

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን