አርዕስተ ዜና

የጤፍ ነገር -የተዘነጋው የቤት ስራ፡፡

6229 times

የምድረ ቀደምቷ አገር ህዝቦች ግብርና ስራቸው ሺ ዘመናት ወደኋላ ይርቃል። ኑባሬያቸውን ከብዝሀ ሕይወት ያዋደዱት ከጥንት ነው። እናም የአያሌ የእንስሳትና ዕጽዋት ብዝሐ ሕይወት ባለቤት የሆኑት ኢትዮጵያዊን ህይወታቸውን በግብርና ገፍተዋል፤ እየገፉም ነው። ከግብርና ተግባራቸው ትልቁን ድርሻ የተጎናጸፈው እርሻም በዓለም ላይ ኢትዮጵያዊያን ያላመዳቸውና ለምግብነት ያስተዋወቋቸው በርካታ የዕጽዋት ዘሮች ወይም የምግብ ሰብሎችን አስተዋውቀዋል፤ የግኝት ባለቤቶች ሆነዋል።

ከነዚህ ሰብሎች መካከል ለብዙኋኑ ዕለታዊ ምግብ ለሆነው 'እንጀራ' አቢይ ግብዓት ከመሆን አልፎ ዛሬ ላይ ዝናው በዓለም ገበያ እየተዋወቀ ያለው ጤፍ በጉልህ ይጠቀሳል። ኢትዮጵያዊያን ከጥንት አያቶቻቸው በወረሱት በብርቅዬው የጤፍ አዝመራ የባለቤትነት መብትና ዕውቅና አግኝተዋል ወይ የሚለው ግን ጥያቄ ውስጥ ይመስላል።

ለዚህ ጤፍ የመመገብ ልማድ ያላቸው አርሶ አደሮች ብቻ ሳይሆኑ ለዘመናት ሰብሉን የማብቀል ባህል ያለው ማሳቸው ምስክር ይመስላል። በባዶ እግራቸው በየዓመቱ ሰርክ ከቁር እስከ ጠራራ ማሳቸውን እያለሰለሱ፣ ጎልጉለው፣ ወቅተው የተጣራ ጤፍ ምርት በገበያው ለተለጠጠው ሰፊ ፍላጎት የሚያቀርቡ አርሶ አደሮች የጤፍ ህጋዊ ወራሾች እኛ እንጂ ማንም አይደለም ይላሉ። 

የኢትዮጵያዊያን ቀዳሚ የምግብ ምርጫ የሆነው ጤፍ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ጠቃሚ የምግብ ዓይነት ሆኖ ዝናው እየናኘ መጥቷል። የአርሶ አደሮችም ሆነ የባለሙያዎች የጤፍ ነገር... ስጋታቸው የኢትዮጵያ አንጡራ ሃብትና የጤና ምንጩ ኃብታችንን ቀድመን ባለማስተዋወቃችን ባለቤታችንን ሊወርስ የሚሞክር አካል ብቅ ማለቱን ተከትሎ ነው። ሙከራው አስገራሚና ኢትዮጵያዊያንን የሚያበሳጭ ተግባር እንደሆነ ይናገራሉ።

በርግጥ የኢትዮጵያ ግብርና የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት የሆነው ጤፍ በየዓመቱ ከሶስት ሚሊዬን ሄክታር በላይ መሬት የሚመረት ሲሆን ከጠቅላላው የግብርና ምርትም 37 በመቶ ድርሻ ይይዛል። በአማራ ክልል ብቻ በየዓመቱ ሰብል ከሚመረትበት 4 ነጥብ 46 ሚሊዬን ሄክታር መሬት 25 በመቶው በጤፍ እንደሚሸፈን የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያመለክታል። በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ የሚያሳትማት ነጋሪ ጋዜጣ  በአንደኛ ዓመት ቁጥር ሶስት ዕትሟ "የልዕለ ጥራጥሬው ምላሽ ያጣ ፈተና" በሚል ርዕስ ሰፊ ማብራሪያ ይዛ ወጥታለች።

ጤፍ አምራች አርሶ አደሮች የጤፍ ምርት ከአያት ቅድመ አያቶቻቸው የተረከቡትና ህይወታቸውን የሚመሩበት ብቻቸው ሀብት በመሆኑ ጤፍ የኢትዮጵያዊያን ሀብት ብቻ ነው ይላሉ። የጤፍ ማማ በሆኑ በአማራ ክልል የምሥራቅ ጎጃም ዞን በሚገኙ ወረዳዎች ነዋሪ አርሶ አደሮችም የጤፍ ወራሾች፣ አምራችና ተመጋቢዎች እንደሆኑ ያረጋግጣሉ። አርሶ አደሮቹ የጤፍ ምርት ከአያት ቅድመ አያቶቻቸው የተረከቡትና ህይወታቸውን የሚመሩበት ብቻቸው ሀብት በመሆኑን ጤፍ የኢትዮጵያዊያን ሀብት ብቻ ነው ይላሉ። የዘርፉ ባለሙያዎች ጤፍ በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኝ መንግስት ጥረት ማድረግ አለበትም ባይ ናቸው። 

ስጋታቸው የመነጨው ወዲህ ነው። የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት እና የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በጤፍ 'ጀነቲክ ሀብት' የአርክቦትና ጥቅም ተጋሪነት ጉዳይ ላይ ከሆላንዱ 'ሄልዝ ኤንድ ፐርፎርማንስ ፉድ ኢንተርናሽናል ቢቪ' ካምፓኒ ጋር እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2005 ስምምነት ተፈራርሞ ነበር። ስምምነቱም ኢትዮጵያ በጤፍ ላይ የምታደርገውን ምርምር ለመደገፍ፣ ለግብርና ሙያዎች ነፃ የትምህርት እድል ለመስጠት፣ ጤፍ በአውሮፓ ምድር ሲዘራ በሄክታር 10 ዩሮ ለመክፈልና ካምፓኒው ከተጣራ ትርፉ በዓመት 5 በመቶ ማለትም ከ20 ሺህ ዩሮ ያላነሰ ገንዘብ ለመስጠት ነው።

ይሁንና ካንፓኒው ስምምነቱን ወደ ጎን በመተው በድብቅ የፈጠራ ባለቤትነት መብት ጥያቄ ሲያቀርብ ቆይቶ በጤፍ ዱቄት አዘገጃጀት ፓተንት እና 'አዲና'፣ 'አያና' እንዲሁም 'ተስፋዬ' በተባሉ ሶስት የጤፍ ዝርያዎች ላይ እ.ኤ.አ በ2003 ከአውሮፓ ፓተንት ጽህፈት ቤት የአዳቃይነት መብት አግኝቷል።

በዚህም ኢትዮጵያ ለዘመናት እየተገለገለችበት ያለውን የጤፍ አዘገጃጀት በስሟ ወደ አለም ገበያ ይዛ እንዳትገባ በማገድ የሚገባትን ጥቅም እንዳታገኝ አድርጓታል።ለዚህም ነው አርሶ አደሮች ጤፍ ከቅድመ አያቶቻቸው የወረሱት የኢትዮጵያ ብቻ ሃብትና መለያው በሆነው የጤፍ ነገር እንዳሳሰባቸው የሚገልጹት።

የደጀን ወረዳ ነዋሪው የ76 ዓመቱ አዛውንት አርሶ አደር ሰውነት ጌቴ ለኢዜአ እንዳሉት ጤፍ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣ የኢትዮጵያውያን ህይወት ነው ይላሉ፡፡

መሬቱን ደጋግመው በማረስ የሚዘሩት፣ በማንኛውም የአየር ንብረት ላይ የሚበቅል፣ ለምግብነት ተስማሚና በገበያውም ተፈላጊ የሆነ የተዘወተረ ምርታቸው አንደሆነም በአጽንኦት ይናገራሉ።

በዞኑ የአነደድ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ዘላለም ደሴ ከአያት ቅድመ አያቶቻቸው የወረሱት ልዩ ምልክታቸውና የብቻ ሃብታቸው እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡

በእነማይ ወረዳ የግብርና ባለሙያው ወጣት ፍሬው ሙሉዓለም ኢትዮጵያ የጤፍ ዱቄት አዘገጃጀትና አዳቃይነት መብት የተነጠቀችው በመንግስት ቸልተኝነት ነው ብሏል፡፡

የእናርጅ እናውጋ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የሰበል ልማት ባለሙያ አቶ መኳንንት አበበ መንግስት አስፈላጊውን መረጃ በማሰባሰብ ኢትዮጵያ የጤፍ መገኛ እንደሆነች ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቅ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተማራማሪ ዶክተር ሙላቱ ካሳዬ የሆላንዱ ካምፓኒ የባለቤትነት መብት ያገኘባቸው የጤፍ ዝርያዎች በተለያየ መንገድ የተስፋፉ ናቸው፤ ነገር ግን ትክክለኛዋ የጤፍ መገኛ ኢትዮጵያ መሆኗ አያጠራጥርም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ እንደ በቆሎ ስንዴና ኑግ ሁሉ የጤፍም መገኛ መሆኗ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ አማካሪና የአለም  አቀፍ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ሀገራዊ አስተባባሪ አቶ አብዱልረዛቅ ጀጁ በበኩላቸው "ካምፓኒው ከስሬያለሁ በማለት ራሱን ከህጋዊ ሰውነት በማሸሽ የፈጸመው የረቀቀ ዝርፊያ ፓተንቱን በፍጥነት ፈራሽ እንዳናደርግ እንቅፋት ሆኖብን ቆይቷል" ብለዋል።

መንግስት የካምፓኒውን የፈጠራ መብት ማሰረዝ የሚችልበትን የቴክኒክ ስራና የተሻሉ መንገዶች ለመለየት ረጀም ጊዜ ቢወስድበትም በአሁኑ ወቅት አማራጮችን ለይቶ በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በአገሪቱ ጤፍን ከስምንት ሚሊዮን በላይ ዜጎች በማምረት ሂደቱ የሚሳተፉ ሲሆን ከ50 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን የተዘወተረ ምግብ እንደሆነም መረጃዎች ያመለክታሉ።

Last modified on Friday, 02 February 2018 00:28
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን