አርዕስተ ዜና

መነሻው አህያ - መድረሻው የዓለም ገበያ

14 Mar 2017
3459 times

ገብረህይወት ካህሳይ (ኢዜአ)

የዛሬ 24 ዓመት ገና የ18 ዓመት ወጣት ነበር ። ዛሬ የ42 ዓመት ጎልማሳ ነው ። ያኔ ግብርናውን  አሃዱ ብሎ የጀመረው አህያ ጠምዶ በማረስ ነበር ። ዛሬ 16 ትራክተሮችና ሌሎች ዘመናዊ መሳሪያዎች ተጠቅሞ ያርሳል ። ለዓመት ቀለብ ብሎ የጀመረው ግብርና ዛሬ የ160 ሚሊዮን ብር ባለሃብት አድርጎታል - የቤንሻንጉል ጉሙዙ ወርቅነህ ህሩይ ጎላ  ።

አዳማ ከተማ ላይ በ8ኛው የሞዴል አርሶ አደሮች ፌስቲቫል ነበር የተገናኘነው ። ተሸላሚ ነው ። ነገር ግን  ሞዴል አርሶ አደር ሆኖ አልነበረም  የተሸለመው - ግብርናው የወለደው ባለሃብት ተብሎ እንጂ ።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ እጅ የተቀበለው የዋንጫ ሽልማት በክብር እቅፍ አድርጎ ይዞታል ። ለቃለ ምልልስ ስጠይቀው ፈቃደኝነቱን አረጋገጠልኝ ። ቆይታችን በፈገግታ የታጀበና በስኬት ትረካዎች የተሞላ ነበር ።

የትናንቱ ወጣት የዛሬ ጎልማሳ ባለሃብት ነውና ለክብሩ አንቱታ ጨመርኩበት ። አርሶ አደር ወርቅነህ ህሩይ ጎላ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ጉባ ወረዳ የተገኙ የግብርና ጀግና ናቸው ። ጉባ - ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ እየተካሄደ ያለበት ታሪካዊ ስፍራ ።

“ ግብርና የጀመርኩት በ18 ዓመቴ ነው ። በመስኩ 24 ዓመታትን አሳልፌያለሁ ። ወላጆቼ በሰጡኝ ቁራሽ መሬት አህያ ጠምጄ በማረስ ጀመርኩኝ ። በባለሙያዎች ምክር እየታገዝኩኝ ምርጥ ዘር ፣ ማዳበሪያና ሌሎች ግብአቶች የመጠቀም አቅሜ እየጎለበተ ፣የስራ ፍቅሬ እየጨመረና  በማገኘው ገቢ ደስተኛ እየሆንኩኝ መጣሁ “ በማለት አነሳሳቸውን ይተርኩታል ።

“ ቁጠባን ለተሻለ እድገት መንደርደሪያ በማድረግ ሰፊ መሬት አግኝቶ የማልማት ፍላጎቴ ጨመረ ። የቆጠብኩትን መጠነኛ ገንዘብ ከባንክ ብድር ጋር በማዋሃድ በኢንቨስትመንት ለግብርና ልማት የሚውል 3ሺህ 341 ሔክታር መሬት ወሰድኩኝ “ ይላሉ ።

መሬቱን በአግባቡ ማልማት በመቻላቸው ተጨማሪ የእርሻ መሬት ጠይቀው አሁን በአጠቃላይ የሚያለሙት መሬት 4 ሺህ 470 ሔክታር መሬት ደርሷል ። ታዲያ ! መሬቱን ከ24 ዓመት በፊት እንደጀመሩት በአህያ የሚያርሱት እንዳይመስላችሁ ። 16 ዘመናዊ ትራክተሮችና ዘመናዊ የአጭዶ መውቂያ መሳሪያዎች ባለቤት ሆነዋል ።

 አቶ ወርቅነህ በዓመት በአማካይ ከ7 ሺህ እስከ 10 ሺህ የጉልበት ሰራተኞች ቀጥረው ያሰራሉ ። ለእንዱስትሪ ግብአት ጥጥ ፣ ለዓለም ገበያ ሰሊጥ ለቀለብ ደግሞ ማሽላ ያመርታሉ ።

ዘንድሮ ለሽልማት ከመምጣታቸው በፊት እንኳን 7ሺህ ኩንታል ሰሊጥ ፣ 22ሺህ ኩንታል ጥጥ ለሰራተኞች ቀለብ የሚሆን ደግሞ 18 ሺህ ኩንታል ማሽላ ማምረታቸውን በመግለፅ ስኬታቸውን በኩራት ይተርኩታል ።

አቶ ወርቅነህ የራሳቸውን 7 ልጆችን ጨምረው በጠቅላላ 11 የቤተዘመድ ልጆች በማስተማር ላይ እንደሚገኙ   ይተርካሉ ። የመጀመሪያ ልጃቸው በሲቪል ኢንጅነሪንግ የማስተርስ ዲግሪ አግኝታለች ። ሶስቱ ልጆቻቸው ደግሞ የመጀመሪያ ዲግሪ ይዘዋል ። 4 ልጆችም በዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ናቸው ።

“ የካፒታል መጠኔ ከ160 እስከ 180 ሚሊዮን ብር ይጠጋል ። ብዙ ህልሞች አሉኝ ። ዘመኑ ለስራ የተመቸ ነው ። ከሰራህ የመንግስት ድጋፍ አይለይህም ። እናም ህልሞቼን ለማሳካት ትላልቅ ፕሮጀክቶች ጀምሬያለሁ “ ይላሉ ።

በየዓመቱ እያመረትኩኝ ለኢንዱስትሪ ግብአትነት በማቀርበው ጥጥ ላይ እሴት ለመጨመር ትልቅ የመዳመጫ ፋብሪካ ለመገንባት በእንቅስቃሴ ላይ ነኝ የሚሉት አቶ ወርቅነህ ዘንድሮ ግንባታው ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ በመቀጥለው ዓመት ጥጥ መዳመጥ ይጀምራል የሚል ተስፋ መሰነቃቸውን ያብራራሉ ።

በሚኖሩበት ጉባ ወረዳ ለወደፊቱ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚገበኙ   ቱሪስቶች ቁጥር እየጨመረ እንደሚሄድ የተገነዘቡት አርሶ አደር ወርቅነህ በአካባቢው ባለ 4 ኮኮብ ደረጃ የሚያሟላ ሆቴል ለመገንባት መሬት ወስደው የቅድመ ግንባታ ስራዎች ማጠናቀቃቸው ይናገራሉ ።

አህያ ጠምደው የጀመሩትን እርሻ አሁን በዘመናዊ ትራክተሮች እየታገዙ ለዓለም ገበያ የሚቀርብ ጥራቱን የጠበቀ የሰሊጥ ምርት በማቅረብ ለአገራቸው የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ጀምረዋል ። ከአህያ ወደ ዓለም ገበያ ይሉታል ይኸው ነው ።

ግብርናችን  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወርቅነህ  ህሩይ ዓይነት አርሶአደሮች ማፍራት የሚችልበት ምእራፍ ላይ መድረሱን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የገለፁትም ለዚህ ነው ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለ8ኛው ዙር ሜዴል አርሶ አደሮች ሽልማት ከሰጡ በሃላ ባስተላለፉት መልእክት “ በግብርናና በተፈጥሮ ሀብት ልማት በአነስተኛ የአርሶ አደር ማሳ ላይ የተመሰረተ የእድገት አቅጣጫ በመከተላችንና ለሩብ ምዕተ ዓመት የሰራናቸው ስራዎች አገራችን በመጀመሪያ የካፒታል ክምችት ምእራፍ ላይ እንድትደርስ አስችሏል “ ነበር ያሉት ።

ምእራፉ በአንድ በኩል ለኢንዱስትሪ ልማት ተፈላጊ የሆነውን መጠነ ሰፊ ካፒታል የማከማቸት ብቃት የሚገነባበት  በሌላ በኩል ደግሞ ለኢንዱስትሪ ግብአትና ለኤክስፖርት ጥቅም የሚውሉ ምርቶችን የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶት የሚሰራበት ወሳኝ ምእራፍ ነው “ ብለውታል ።

ይሄው ምእራፍ የገጠር የግብርና የስራ መስክ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር በሚደረገው   ርብርብ መጠነ ሰፊ የተዘጋጀ የሰራተኛ ሀይል ማቅረብ የሚቻልበት ጭምር ነው ብለውታል ።

በግብርናው ዘርፍ ከተሰማሩ 14 ሚሊዮን አርሶ አደሮች መካከል በእስከ አሁኑ ጥረት 22 በመቶ የሚሆኑትን ሞዴል አርሶ አደሮች ማድረግ እንደተቻለ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያንዳንዱ ሞዴል አርሶ አደር  ያካበተውን እውቀት ፣ ክህሎትና ልምድ ተጠቅሞ ከአንድ እስከ ሶስት የሚደርሱ ሌሎች ሞዴል አርሶ አደሮች በማፍራት በሁለትና በሶስት እጥፍ እንዲያሳድጉት ትልቅ ሃላፊነት ከታሪካዊ አደራ ጋር እንደተሰጣቸው ተናግረዋል ።

የወጣቶች ዘመናዊ የግብርና ልማት ተሳትፎ በአግባቡ ከተመራ የግብርናው ዘርፍ በማዘመን   ታሪካዊ ተልእኮ የሚፈፅም ይሆናል ሲሉም አስምረውበታል ።

በጥረታቸው ፣ በግብርና ባለሙያዎች እገዛና በተመራማሪዎች ድጋፍ  ሚሊየነሮች የሆኑት ሞዴል አርሶ አደሮች  በተናጠልና በህብረት ስራ ማህበሮቻቸው አማካኝነት ወደ ኢንዱስትሪ በሚደረገው እንቅስቃሴ በኢንቨስትመንት በመሳተፍ  ለብዙ ወገኖቻቸው የስራ እድል የመፍጠር ታሪካዊ ሃላፊነት እንደለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል ።

የሽልማቱ አካል የነበሩት ወጣት ሞዴል አርሶ አደሮች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ታሪካዊ ጥሪ ታሪካዊ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ነን ብለዋል ።

ወጣት ዘውዱ ዓለሙ በ8ኛው አገር አቀፍ የሞዴል አርሶአደሮች ፌስቲቫል ከጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ እጅ የሜዳሊያ ሽልማት ከተቀበሉ ሚሊዮነር ወጣት አርሶ አደሮች መካከል አንዱ ነው ።

እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ ተምሮ ውጤት ስላልመጣለት ወደ ግብርና ስራ መሰማራቱን የሚገልፀው ወጣት ዘውዱ በአንድ በኩል የግብርና ስራውን ጎን ለጎን ደግሞ የእንስሳት እርባታውን አቀናጅቶ በማከናወን በአጭር ጊዜ ውስጥ  9 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ሀብት ማፍራት እንደቻለ ይናገራል ።

ከሰሜን ሸዋ ዞን ቅንብቢት ወረዳ በስኬቱ ለአገር አቀፍ ሽልማት የበቃው ወጣት ዘውዱ 50 ለሚጠጉ ወገኖቹ የስራ እድል ፈጥሯል ።

አሁን ያከበተውን ሀብት  ይበልጥ በማሳደግ ወደ ኢንቨስትመንት  በመሸጋገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ   ያስተላለፉትን መልእክት ተግባራዊ በማድረግ እራሱን ፣ አገሩንና ወገኑን ለመጥቀም ዝግጁ ነኝ ይላል ።

የአገራቸን ውጣቶች ሀብት አፍርተው እሱ የደረሰበት ደረጃ ደርሰው የማየት ፍላጎት እንዳለው ወጣቱ ገልፆ ስራ በመፍጠርና ጠንክሮ በመስራት ሀብት ማፍራት እንደሚቻል በተግባር አይቼዋለሁ በማለት የእድሜ እኩዮቹን በፅናት ለስራ ቆርጠው እንዲነሱ ምክሩን ለግሷል ።

ከባሌ ዞን ጊኒር ወረዳ 7 ሚሊዮን ብር ሀብት በማፍራቱ ተመልምሎ ለሽልማት የበቃው ወጣት አርሶ አደር ሰለሞን ደገፋ በበኩሉ በመስመር መዝራትን ጨምሮ የግብርና ቴክኖሎጂ ግብአቶችን በአግባቡ በመጠቀም ለስኬት መብቃቱን ተናግሯል ።

ከእርሻው ስራ በተጓዳኝ በከተማ የመኖሪያ ቤትና ሁለት መጋዘኖች ገንብቶ ወደ ንግድ መግባቱን ገልፆ ወጣቶች መንግስት የሚፈጥርላቸውን የስራ እድል በአግባቡ ከተጠቀሙበት ስኬታማ መሆን እንደሚቻል ከእኛ ማረጋገጥ ይችላሉ ብሏል ።

የወጣት ሞዴል አርሶ አደሮች ስኬት ማስፋት ከተቻለ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ወጣት ስራ ፈጣሪዎች ሲሸለሙ ማየት እንደምንችል እርግጠኛ ነኝ የሚል ሃሳብ የሰጠው ወደ ባለሃብትነት ለመሸጋገር ጠንክሮ እንደሚሰራ በእርግጠኝነት ተናግሯል ።

ከምስራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ወረዳ ተመልምሎ የሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነው ወጣት አርሶ አደር ሹሚ ዱቤ  በግብርና ስራ የ8 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ባለሃብት መሆን ችሏል ።

የስራ እድል የፈጠረላቸው 20 የሚሆኑ ወጣቶች የስኬቴ ሚስጢር ናቸው በማለት ይገልፃቸዋል ።

ተምረው ቤት የተቀመጡ በርካታ ወጣቶች የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ተአምር እንደሚሰሩ የሚገልፀው  ወጣት ሹሚ በአንድ በኩል መንግስት እድሉን ሊፈጥርላቸው በሌላ በኩል ደግሞ ወጣቶቹ እድሉን በአግባቡ ተጠቅመው ከልብ መስራት እንዳለባቸው ይመክራል ።

በተለይ የከርሰ ምድር ውሃን የሚጠቀሙና የመስኖ ልማትን የሚመርጡ ወጣቶች ጠንክረው ከሰሩ ስኬታማ እንደሚያደርጋቸው  ተሞክሮውን አጋርቷል ።

የሞዴል አርሶ አደሮች ሽልማት ስኬታማ የሆኑትን  የበለጠ እንዲነሳሱ ወደ ኋላ የቀሩት ደግሞ መነቃቃት እንዲፈጥሩ በማድረጉ ሂደት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ውጤቱ ጎምርቶ መታየት ጀምሯል ።

በ8ኛው የሞዴል አርሶ አደሮች ፌስቲቫል 550 የልማት ጀግኖች የተሸለሙ ሲሆን ከሞዴል አርሶ አደሮች በተጨማሪ ለግብርና ምርትና ምርታማነት እድገት ልዩ ሚና የተጫወቱ የልማት ጣቢያ ሰራተኞች ፣ የወረዳ ግብርና ፅህፈት ቤቶች ፣  ሞዴል የወረዳና የቀበሌ አመራር አካላት ፣ የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች ፣ የብድርና ቁጠባ ተቋማት ፣ ተመራማሪዎች ፣ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶችና ድጋፍ ሰጪ አካላት ተቋዳሽ ሆነዋል ።

በባህርዳር ከተማ በ1999 ዓ.ም የተጀመረው የሞዴል አርሶአደሮች ፌስቲቫል በሀዋሳ ፣አዳማ ፣ መቀሌ ፣ ድሬዳዋ ፣ ዳግም በባህርዳር እስከ 6ኛ ዙር ድረስ በየዓመቱ ሲካሄድ ቆይቶ ነበር ።ከስድስተኛ ዙር በኋላ ግን በየሁለት ዓመቱ እንዲከበር  ተደርጓል ። በዚሁ መሰረት ሀዋሳ  በ2007 ዓ.ም አዳማ ደግሞ ዘንድሮ ፌስቲቫሉን በደጋሚ የማዘጋጀት እድል አግኝተዋል ።

ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ያወጣው የሞዴል አርሶ አደሮች መመልመያ መስፈርት አጠቃላይ የካፒታል መጠናቸው ከ1ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ፣እሴት  ወደ ሚጨምሩ የተለያዩ የልማት ፣ የኢንቨስትመንትና ንግድ ስራዎች የተሻገሩና ለወጣቶችና ለሴቶች የስራ እድል የፈጠሩ ፣ ባፈሩት ካፒታል ቴክኖሎጂዎችንና አዳደስ አሰራሮችን በመጠቀም የግብርና ምርታማነት ያሳደጉ  የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው ።

አዳማ በሚሊየነር አርሶ አደሮች ስኬት ሀብት ሀብት እየሸተተች እንግዶቿን በሰላም አስተናግዳ ሸኝታለች ። ጠንክሮ ከተሰራ የሚሊየነርነት ሚስጢር ቅርብ እንደሆነም በተግባር አሳይተውናል ። ለተሻለ ሀብት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ታሪካዊ የአደራ ጥሪ ተቀብሎ መተግበር ደግሞ ለበለጠ ውጤት ይጠቅማልና ይታሰብበት ።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን