አርዕስተ ዜና

ሞዴል ተሞክሮዎችን በማስፋት ሚሊዮኖች ሚለየነሮች ይሆናሉ !

11 Mar 2017
3396 times

                       ዮናታን ዘብዴዎስ ( ሃዋሳ ኢዜአ)

የክልሉን የአርሶ አደሮች ዓመታዊ ፌስቲቫል ያስተናገደው የሲዳማ ባህል አዳራሽ ላለፉት ሁለት ቀናት ደምቆ ነበረ የሰነበተው፡፡

ከክልሉ የተለያዩ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የተውጣጡ፣ ከፊታቸው ደስታ የሚነብባቸው አርሶአደሮች ጎርደድ መለስ ብለውበታል፡፡ በአዳራሹ መግቢያ በር ላይ የፌስቲቫሉን ምንነት የሚያወሳ ባነር ከፍ ብሎ ተሰቅሏል፡፡

8ኛው የክልሉ አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች ፌስቲቫል “እርሻችንን በማዘመን የኢንዱስትሪ ልማት ሽግግር እንፋጥን” የሚል መሪ ቃል ቃል የያዘ ነው  ፡፡

የአዳራሹ  ቅጥር ግቢ በግብርና ምርት ውጤቶችና ግብርናውን ሊያዘምኑ በሚችሉና ለአግዚቪሽን በቀረቡ የቴከኖሎጂ ትሩፋቶች ተሞልቷል፡፡

ከፌደራልና ከክልል የተገኙ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች፣ ባለሙያዎች፣ አርሶ አደሮችና ተጋባዥ እንግዶች ኢግዚቪሽኑን ታድመዋል፡፡ 

በመጀመሪያው ቀን ውሎ ፓናል ውይይትን አካቶ፤ በኢግዚቪሽን ደምቆ የተከበረው ፌስቲቫሉ በ2ተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመጀመሪያው ዓመት በግብርና ዘርፍ የገጠሙ ተግዳሮቶችና መፍትሄዎቻቸውን ተመልክቶ የተዘጋጀ የዳሰሳ ጥናት ቀርቦ ምክክር ተካሄዶበታል ።

የሁለተኛው ቀን ውሎ ደግሞ የሽልማት መርሃ ግብር የተካሄደበት ነበር፡፡ ከተሸላሚ አርሶአደሮች መካከል አቶ ዳንጋሞ ዳኖሌ ቀዳሚ ነበሩ ። በሲዳማ ዞን በዳሌ ወረዳ ጎይዳ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው ።

ባለትዳር ፣ የአራት ወንዶችና የሁለት ሴቶች አባት ናቸው ።  ለሶስት ተከታታይ ዓመታት ሞዴል አርሶ አደር ተብለው ተሸልመዋል ።

ስላፈሩት ሃብት ሲተርኩልኝ ፍፁም ሐሴት ፊታቸው ላይ ይነበብባቸው ነበር ፡፡ ስማቸው አንድ ሺህ በሚጠጋ ህዝብ ፊት ሲጠራ መደሰታቸውን ሳይደብቁ ነበር የነገሩኝ፡፡

ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ሃብት በማፍራት ከሁሉም ቀድመው የተሸለሙ ሞዴል አርሶ አደር ናቸው - አርሶአደር ዳንጋሞ ዳኖሌ ፡፡

ከባለቤታቸው ጋር በመሆን በሞተር የሚሰራ የሰብል ማጨጃ ሽልማታቸውን ከክልሉ ርዕሰ መስተዳደሩ የተቀበሉት  እኚህ ሞዴል አርሶ አደር ለዚህ ያበቃቸው አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀምና ከግብርና ባለሙያ የሚሰጣቸው ድጋፍና የመንግስት ክትትል እንደሆነ ነው የገለፁት፡፡

በይርጋለም ከተማ ትልቅ ቪላ ቤት ሰርተው እንደሚኖሩበት የተናገሩት አርሶ አደሩ በሃዋሳ ከተማም መኖሪያ ቤት እንዳላቸውና በዘመናዊ የኑሮ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ለ35 ሰዎች የስራ እድል የፈጠሩት አርሶ አደር ዳንጋሞ ልጆቻቸውን በሚፈልጉበት ደረጃ መርጠው አስተምረዋል፡፡ ዶ/ር ልጃቸው ስፔሻላይዝ እንዲያደርግም ከአንድ መቶ ሺህ ብር በላይ የወጭ መጋራት ከፍለው ውጭ አገር በማስተማር ላይ እንደሚገኙ በልበ ሙሉነት ስኬታማነታቸውን ተርከውልኛል።

ግብርናው ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የሚፈልግበት ዘመን ላይ መደረሱን ያመለከቱት አርሶአደሩ ወደ ባለህብትነት ያሻገራቸውን ግብርና ዘመኑ በሚፈልገው ልክ ከሰራን የሃገሪቱን እድገት ፈጣን ማድረግ እንደሚቻል በተግባር አይተውታልና ምስክርነታቸውን ይገልፃሉ ።

ሌላኛዋ ተሸላሚ ሞዴል አርሶ አደር ገነት መንግስቱ ይባላሉ ። ሲሸለሙ የመጀመሪያቸው ነው፡፡ ዘመናዊ የግብርና ትምህርት ዘዴዎች ቀስሜ ተግባራዊ ማድረጌ ስኬታማ አድርጎኛል ባይ ናቸው ፡፡

 19 ሚሊየን ብር ሃብት በማፍራት  ከአርሶ አደርነት ወደ ባለሃብትነት ተሸጋግረዋል ።   

እንደ ክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ ገለፃ ከላይ የገለፅናቸውን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ1 ነጥብ 2 እስከ 21 ሚሊዮን ብር ሃብት ያፈሩ 387  አርሶ አደሮችና  ከፊል አርሶ አደሮች በፌስቲቫሉ ላይ ተሸልመዋል፡፡

ተሸላሚዎቹ በጥረታቸው ድህነትን  በብቃት ያሸነፉና የምግብ ዋስትናቸውን ያረጋገጡ ከመሆኑም በተጨማሪ በሚሊዮን የሚቆጠር ሃብት አፍርተዋል፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ ድጋፋቸውን ያበረከቱ የግብርና ባለሙያዎች፣ ባለሃብቶች፣ ተማራማሪዎችና መገናኛ ብዙሃንም የድርሻቸውን ስላበረከቱ እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደሴ ዳልኬ በሽልማት ስነ ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ግብርናው የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ለኢንዱስትሪ ልማትና ለኤክስፖርት ዘርፍ ዋነኛ የግብአት ምንጭ በመሆኑ የተለየ ትኩረት በመስጠት ኢኮኖሚውን መምራት ይገባል፡፡

የሃገሪቱ እድገት ምንጭ በሆነው ግብርና የክልሉ አርሶ አደሮች በአነስተኛ ማሳ ምርትና ምርታማነትን መነሻ በማድረግ ገበያ ተኮር ምርቶችን የማምረት አቅማቸውን እያሳደጉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ግብርናው እየዘመነ በመሆኑ ባለፉት አጭር ዓመታት  አርሶ አደሮች ከኃላ ቀርነት አስተራረስ  በመውጣት ለገበያ የማምረት አቅም ማጎልበታቸውን ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ከአርሶ አደርነት ወደ ባለሃብትነት ተሸጋግረው ለሽልማት የበቁ አርሶ አደሮች ማረጋገጫ መሆናቸውን ርዕሰ መስተዳደሩ ተናግረዋል፡፡

የማስፋት ስትራቴጂን ተግባራዊ በማድረግ ስኬታማና ሞዴል አርሶ አደሮች የሚጠቀሙትን አሰራሮች ለሌሎች አርሶ አደሮች በማስተላለፍ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡

የግብርና ኤክስቴንሽን ተግዳሮቶችን ለመፍታትም አርሶ አደሩንና ከፊል አርሶ አደሩን አቀናጅቶ በአደረጃጀት መምራት እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል ።

ተሸላሚ አርሶ አደሮች የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ወደ እንዱስትሪ ለማሸጋገር በሚደረገው ርብርብ ውስጥ የማይተካ ሚና እየተጫወቱ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የግብርና ልማት ስራን ለማጠናከር ወሳኝ በሆነው የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ስራ መላው አርሶ አደር የተግባሩ ባለቤት በመሆኑ ዘላቂነት ያለው ልማት ለማስመዝገብ የበኩላቸውን  እየተወጡ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

በመስኖ ልማት ዘርፍና በገጠር የተቀናጀ ልማት ከእንስሳት የሚገኘው ጥቅም በሚፈለገው ደረጃ ላይ አለመድረሱን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳደሩ የመኖ ልማትን ጨምሮ በዘርፉ የተቀናጀ ስራ እንዲሰራ አሳስበዋል፡፡

የፌስቲቫሉ አካል በሆነው የፓናል ውይይት በቀረበ ጥናታዊ ፁሁፍ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የግብርና ልማት ዘርፍ መላውን አርሶና አርብቶ አደር እንዲሁም የገጠር ወጣቶችና ሴቶችን ተጠቃሚ ያደረገ የ8 ነጥብ 7 በመቶ ዕድገት እንደተመዘገበ ተመልክቷል፡፡

በክልሉ በ2ተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመጀመሪያ ዓመት ያገጠሙ ፈተናዎችን የሚተነትነው ጹሁፉ የሰብል በሽታዎችና ተባዮች ተከስተው ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን ያስረዳል፡፡

በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የዝናብ እጥረት በመፈጠሩ ምክንያት የምርት መጠን ማነስና እንስሳት በግጦሽና መኖ እጥረት ለጉዳት እንተዳረጉም ጥናቱ ያትታል ።

በዋና ዋና ሰብሎች የስንዴ ቢጫ ዋግ በሽታ፤ የበቆሎ ገዳይ ቫይረስ፤ የዝንጅብል አጠውልግና የማንጎ ፍሬ ዝንብ አዲስ የተከሰቱ ተባዮችና በሽታዎች ናቸው ብሏል ጥናቱ፡፡

በአርሶና አርብቶ አደሮች ዘንድ ግንዛቤ የማስጨበጫ ስራዎች በመሰራታቸው አርሶ አደሮች ጸረ-ተባይ ኬሚካሎችን የቴክኖሎጂ አካል አድርገው እንዲጠቀሙ ማድረግ ተችሏል፡፡

ጥናቱን ያቀረቡት የደቡብ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር አግደው በቀለ በወቅታዊነት ተባይን አስሶና ለይቶ ተገቢውን ፈጣን እርምጃ አለመውሰድና ጸረ-ተባይ ኬሚካሎች በሚፈለገው መጠንና ጥራት ገበያ ላይ አለመገኘታቸውና ሌሎችም በሰብል ጥበቃ ወቅት የታዩ ተግዳሮቶች እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡

በእንስሳት መኖ እጥረትም በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ድርቅ ተከትሎ የተፈጠረ ችግር እንደነበረ የተመለከተ ሲሆን በመስኖ ልማትም ክልሉ ከፍተኛ  እምቅ ሀብት ቢኖረውም መልማት የቻለው መሬት 40 በመቶ ብቻ ነው ተብሏል፡፡

የኤፌዴሪ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ መንግስቱ ጹሁፉ ያለውን ችግር ያመላከተ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍታት የእቅዳችን አካል አድርገን መነቀሳቀስ እንደሚገባና ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፤ ተመራማሪዎች፤ ባለሙያዎችና አርሶ አደሮች ጋር በመቀናጀት ከፍተኛ ርብርብ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡

የግብርና ምርምር ማዕከላትን በማጎልበት ለዘርፉ ተግዳሮቶች ዘላቂ መፍትሄ በመስጠት የግብርናውን ከፍለ ኢኮኖሚ ማሳደግ እንደሚያስፈልግም ሚ/ር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡

የኤፌዲሪ መንግስት የፖሊሲ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ዶክተር ካሱ ኢላላ በበኩላቸው ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ማምረት የቻሉ አገራት ምርታቸው ከፍተኛ ሲሆን የኢትዮጵያ በአንጻሩ ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሰብል ጥበቃ ስራ የምርምር፣ የኤክስቴንሽንና የእፅዋት ማዕከላት እየተቀናጁ አዳዲስ በሚፈጠሩና በተያያዥ ጉዳዮች   ዙሪያ ተጠናክረው መስራት እንዳለባቸውና የግብርና   ቴክኖሎጂ   አለመጠቀምና ሙሉ ፓኬጅ አለመተግበርን ለምርት መጠን ዝቅተኛነት እንደምክንያት አንስተዋል፡፡

ለውጦች የተመዘገቡ ቢሆኑም ከተሰራው ይልቅ ያልፈጸምናቸው ተግባራት ይበልጣሉ ያሉት ዶ/ር ካሱ የግብርናውን ምርት በማሳደግ የጀመርነውን የኢንዱስትሪና የአግሮ ፕሮሰሲንግ ስትራቴጂያች ማፋጠን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የተቀናጀ ቴክኖሎጂ አጣምሮ በመጠቀም ማልማት እንደሚገባ የተናገሩት ዶ/ሩ የመኖን ጠቀሜታ ተገንዝበን በአርሶና አርብቶ አደሮች ማሳ ላይ ማምረት እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል፡፡

ለፓናል ውይይት በቀረበው ጽሁፍ  ውይይት ተደርጎ የተለያዩ ጥያቄዎችና የመፍትሄ ሀሳቦች የተነሱ ሲሆን ፈተናዎችን ፈትቶ ሌሎች በርካታ ሞዴል አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮችን ለማፍራትና ወደ ባለሃብተነት ለማሸጋገር መስራት እንደሚገባም ተገልጧል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዋነኛነት የተመሰረተው በግብርና ላይ ሲሆን ከአጠቃላይ ገቢ 38 በመቶ ከውጭ ምንዛሪ ግኝት አንፃር ደግሞ 80 በመቶ እንደሚሸፍን ከእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን