አርዕስተ ዜና

ከህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እስከ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት

2894 times

ምህረት አንዱአለም /ኢዜአ/

ከጂቡቲ ወደ ኢትዮጵያ በበቅሎ የሚደረገውን ከ4 እስከ ስድስት ሳምንት ጉዞ ለማሳጠር ህዳር ወር 1890 ዓ.ም ጂቡቲ ላይ የባቡር መስመር ዝርጋታ መጀመሩን መረጃዎች ያሳያሉ። የአምስት ዓመት የምስረታ እድሜ ብቻ የነበራት ድሬዳዋም በ1895 ዓ.ም  የመጀመሪያውን ባቡር አስተናገደች።

ከዚህ ቀጥሎም ከአምስት አመት በኋላ  ከድሬዳዋ አዲስ አበባ የሚደርሰው የሃዲድ ስራ ተጀምሮ በ1909 ዓ.ም  በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያው ባቡር አዲስ አበባ መግባቱን የታሪክ ሰነዶች ያሳያሉ። በታሪክ የጊዜ ርዝማኔ ዛሬ ላይ የደረሰው ባቡር ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ቁርኝት ከ100 ዓመት  በላይ ሆኖታል፡፡

ሀገራት ለመልማት ቀድመው መስራት ከሚጠበቅባቸው ጉዳዮች አንዱ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን በርካቶች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው፡፡ ከትራንስፖርትም መካከል  ባቡር አንዱን የልማት ኮሪደር ከሌላው የሚያስተሳስር የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ የደም ስር መሆኑን በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ደረጄ ተፈራ ተናግረዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ በኢትዮጵያ እየተመዘገቡ ካሉ የእድገትና የልማት እንቅስቃሴዎች አኳያ የባቡር ትራንስፖርት ከሜጋ ፕሮጀክቶች አንዱ ሆኖ ቀጥሏል፡፡

ለፈጣን ማህበራዊና ኢኮኖሚዊ እድገት ፈጣንና አስተማማኝ የጭነትና የመንገደኞች መጓጓዣ አማራጭ ከሌለ፥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በኢኮኖሚ እድገትም ሆነ በማህበራዊ ትስስር ላይ አሉታዊ  ጫና ያሳድራልም ነው ያሉት አቶ ደረጃ፡፡

በኢትዮጵያም በመጀመሪያውና በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ጊዜያት ከ5 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የባቡር መሰረተ ልማቶችን ለመስራት እቅድ ተይዞ ወደ ተግባር መገባቱንም  ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ይህ የባቡር መሰረተ ልማት ሲገነባ የሰለጠነ የሰው ሃይል እና የፋይናንስ ችግር ቢኖርም የሰው ሃይሉን አቅም በመገንባትና የፋይናንስ አማራጮችን በማፈላለግ  ሀገሪቱ  ሁለት ፕሮጀክቶችን ገንብታ ወደ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ሀሳባቸውን ያካፈሉን አቶ ደረጀ አሁንም በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም  ያብራራሉ፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶችም የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በሀገሪቱ የተለያ አቅጣጫ የሚዘረጉ የባቡር መሰረተ ልማትና በተለይ ደግሞ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ኮሪደር ከሆነው ጂቡቲ ጋር የሚያገናኘው ፕሮጀክትም ይገኝበታል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገነቡ አምስት የህዝብ ማጓጓዣ ቀላል ባቡር ምዕራፎች ውስጥ 34 ኪሎ ሜትር ግንባታና ከአዲስ አበባ ተነስቶ ጂቡቲ ድንበር ድረስ 656 ኪሎ ሜትር  ርዝመት ያለው ሃዲድም ግንባታው ተጠናቆ  አገልግሎት መስጠት  ከጀመረ ውሎ ማደሩን ነው አቶ ደረጀ በአብነት ያነሱት፡፡

ከጂቡቲ ጋር የሚያገናኘው ኢትዮጵያ የገነባችው 656 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የባቡር መስመር መስከረም 25 ቀን 2009 ዓ.ም፥ ጅቡቲ የገነባችው የ104 ኪሎ ሜትር መስመር ደግሞ  ጥር 2 ቀን 2009 ተመርቆ ባለፉት ወራት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ቀጥሎ ሁለተኛው ግዙፍ ፕሮጀክት የሆነው የባቡር መስመር ግንባታው 3 ነጥብ 4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ እንደተደረገበት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ይህ ፕሮጀክት የሀገሪቱ የወጪና ገቢ ንግድ ዋነኛ መስመር ከሆነው የጂቡቲ ወደብ ጋር በቀጥታ የሚያገናኝ መሆኑን በባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የመልቲ ሞዳል ኦፕሬሽን መምሪያ ዳይሬክተር አቶ እውነቱ ታዬ  ተናግረዋል፡፡

የወጪና ገቢ ንግድ ምርቶችን በተሽከርካሪዎች ማጓጓዝ እንደማያዋጣ የሚያነሱት አቶ እውነቱ የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ከወደብ  እቃዎችን በፍጥነት እያነሳ ወደ ሀገር ውስጥ እያጓጓዘ መሆኑንም ነው የጠቀሱት። እንደ እሳቸው ገለፃ አንድ ባቡር ከጂቡቲ ወደብ በቀጥታ ወደ ሞጆ ደረቅ ወደብ 106 ኮንቴይነሮች በአንድ ጊዜ ጭኖ በየቀኑ  የማጓጓዝ አቅም አለው፡፡

ይህ የትራንስፖርት ፕሮጀክት  የባህር ትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ አገልግሎቱን እያጠናከረ መሆኑን  የተናገሩት አቶ እውነቱ  ድሮ በተሽከርካሪ እስከ ሶስት ቀን የሚወስደው የጭነት ማጓጓዝ ሂደት አሁን ከጂቡቲ ወደብ ተነስቶ ሞጆ ደረቅ ወደብ በአንድ ቀን እየደረሰ ነው  ብለዋል፡፡ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ እስካሁን 3 ሺህ 959 ኮንቴይነሮችን ከጂቡቲ ወደብ ወደ ሞጆ ማጓጓዝ መቻሉንም ነው የጠቆሙት።

በየወሩ ከሚነሳው አጠቃላይ የኮንቴይነር መጠን የባቡር አገልግሎት ድርሻ ወደ 24 በመቶ ያደገ ሲሆን  ከሞጆ ወደ ጂቡቲ ደግሞ 250 ባዶ ኮንቴይነር መውሰድ መቻሉን ነው ያነሱት። ከዚህ ቀደም በትራንስፖርት እጥረት 36 በመቶ ያህሉ የመልቲ ሞዳል ጭነት ይጓተት የነበረ ሲሆን አሁን ባቡሩ አገልግሎት  መስጠት ሲጀምር ችግሩ ሙሉ በሙሉ መቀረፉን  አቶ እውነቱ አስረድተዋል። በማጓጓዝ ሂደት ላይ  በተለያዩ ምክንያቶች በወር እስከ 17 ተሽከርካሪ አደጋ ያጋጥም የነበረ ሲሆን አሁን አደጋው እየቀነሰ መሆኑና መኪና ሊያነሳቸው የማይችሉ ወደብ ላይ ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ ከባድ ጭነቶችን በባቡር ማንሳት መቻሉ ነው የተገለፀው፡፡

ከጂቡቲ ወደብ በባቡር እቃዎችን ቶሎ ቶሎ  ማንሳት መቻሉ  በወደቡ ይከማቹ ለነበሩ እቃዎች ኢትዮጵያ በውጭ ምንዛሪ የምትከፍለውን ወጪ እንደቀነሰላትም  አቶ እውነቱ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የጉምሩክ አሰራርና ድጋፍ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሃይሌ ገብረ እግዚአብሄር  የባቡር መስመሩ አገልግሎት በመጀመሩ ኢትዮጵያ እና ጂቡቲ ፈጣን የጉምሩክ አገልግሎት ስምምነት መፈራረማቸውን ገልፀዋል።

በስምምነቱ መሰረት አገልግሎቱ  ከተጀመረ ወዲህ ጂቡቲ ወደብ ላይ የሚራገፉ  እቃዎች የጉምሩክ ስርዓቱን ጠብቀው ከስምንት ቀን በታች በሆነ ጊዜ ወደ  ሀገር እየገቡ ነው  ያሉት ዳይሬክተሩ አብዛኛዎቹ ከሶስት እስከ አራት ቀናት ባለው ጊዜ ስለሚገቡ ወደብ ለሚከማች እቃ የሚከፈለውን ገንዘብ እየቀነሰ መሆኑን  በማንሳት ከአቶ እውነቱ ሀሳብ ጋር ይስማማሉ። የባቡር ትራንስፖርቱ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ከወደብ የሚነሱ እቃዎች ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ ለሚያደርገው ቁጥጥርም አመቺ መሆኑን እንዲሁ፡፡

አሁን ላይ አንዱ ባቡር ከነተጎታቾቹ በአንድ ጊዜ የሚጭነው የኮንቴይነር መጠን 53 መኪኖች የሚይዙትን ያህል ሲሆን በርካታ ሰዎችን እያጓጓዘ ነው  ያሉት አቶ  ሃይሌ ባቡሩ ምርቶችን ወደ ውጭ ማጓጓዝ ሲጀምር መርከብ ሲያመልጣቸው ለነበሩ ባለሃብቶች መፍትሄ እንደሚሆንና ሀገሪቱ በውጭ ምርት ተወዳዳሪ እንድትሆን እንደሚያደርጋትም  አንስተዋል፡፡

በመኪና ምርቶችን የማጓጓዝ ሂደቱ ረጅም ጊዜ የሚጠይቅ በመሆኑ ያጋጥሙ የነበሩ የምርት ቅሸባና የሎጂስቲክስ ችግሮችን በመቅረፍ ሀገሪቱን ተጠቃሚ  የሚያደርጋት ሲሆን  የኢትዮ ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት ወደ አገልግሎት መግባትና ሌሎች የባቡር ፕሮጀክቶች ግንባታ ሂደት ላይ መሆን ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትን  ለመሳብ  ትልቅ እድል ይሰጣታል፡፡

ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ባቡር ዋነኛው መሰረተ ልማት መሆኑን የገለጹት  በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የፖሊሲ ጥናትና የስትራቴጂ ዳይሬክተሩ አቶ  ንጉሴ ጉሩሙ አንድ  ባለሃብት ምቹና አማራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሁም ሌሎች መሰረተ ልማቶች መሟላታቸውን ካላረጋገጠ ሃብቱን ፈሰስ አያደርግም ብለዋል።

የባቡር ትራንስፖርትን ተመራጭ የሚያደርገው ደግሞ  የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች የተለያዩ  ክብደት ያላቸውን ጥሬ እቃዎች በቀላሉ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲያስገቡ  ስለሚያስችላቸው ነው፡፡

ቀደም ሲል መኪኖችን በመጠቀም  ጥሬ እቃዎችን የማምጣት ሂደቱ የተጓተተ እንደነበር ያነሱት አቶ ንጉሴ የኢትዮ ጂቡቲ ባቡር አገልግሎት መጀመሩ ችግሩን እንደሚቀርፈውና እቃዎችን ከወደብ ወይም ከማምረቻ አካባቢ ወደሚፈለገው ቦታ በፍጥነት የሚያደርስ መሆኑ ለኢንቨስትመንት መስፋፋት አስፈላጊነቱን የሚያረጋግጥ ነው ይላሉ፡፡  

በኢትዮጵያ አገልግሎት የጀመሩና እየተገነቡ ያሉ የባቡር መስመሮች በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች  የግብርና፣ የማዕድን እና የማምረቻ ዘርፉን ለማጠናከር  የሚያስችሉ መሆኑን ነው አቶ ንጉሴ የጠቀሱት፡፡

ከአዲስ አበባ ጂቡቲ የባቡር መስመር ጋር የተገናኙ ሌሎች ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ መሆናቸውን የገለፁት አቶ ደረጄ ከእነዚህም ፕሮጀክቶች ከአፋር ክልል አዋሽ ተነስቶ ሸዋሮቢት፣ ከሚሴን፣ ኮምቦልቻን ሀይቅን፣ መርሳን እና ወልዲያን የሚያስተሳስረው የባቡር መስመር  አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከወልዲያ አቅራቢያ የምትገኘውን ሀራ ገበያን ነክቶ በአላማጣ፣ መሆኒ፣ መቀሌ የሚሄደው ደግሞ ሌላኛው ፕሮጀክት መሆኑን የጠቆሙት አቶ ደረጀ እነዚህ ፕሮጀክቶች የአማራ፣ የትግራይና የአፋር ክልሎችን ህዝብ ከመካከለኛው የሀገሪቱ ክፍል እና ምርቶችን ደግሞ ከወደብ ጋር ያገናኛሉ ነው ያሉት፡፡

በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ ከሚገነባው የአዋሽ ወልዲያ ሀራ ገበያ የባቡር መስመር ግንባታ ውስጥ ከአዋሽ ኮምቦልቻ ያለው የመጀመሪያው ምዕራፍ 95 በመቶ  የተጠናቀቀ ሲሆን  ከኮምቦልቻ-ወልዲያ (ሃራ ገበያ) ማስገንቢያ  የሚውለው ገንዘብ በወቅቱ ባለመገኘቱ ግንባታውን በታቀደለት ጊዜ ማከናወን እንዳልተቻለ ነው ነው ከምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የተገኘ መረጃ የሚጠቁመው፡፡  

ጥቅምት 2007 ዓ.ም  በ1 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር ግንባታው የተጀመረው የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ወልዲያ(ሃራ ገበያ) ባቡር ፕሮጀክት 392 ኪሎ ሜትር ርዝመትን የሚሸፍን መሆኑን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያሳያል፡፡ ከመቀሌ ደረቅ ወደብ እስከ ጂቡቲ የሚወስደውን ጊዜ ከ50 በመቶ በላይ እንደሚቀንስ የሚነገርለት የመቀሌ ሀራ ገበያ ፕሮጀክት  ግንባታው ከ50 በመቶ በላይ  ተጠናቋል።

ሁለቱ የባቡር ፕሮጀክቶች የሚገነቡበት አካባቢ የመሬት አቀማመጡ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ በርካታ ዋሻዎች እና ድልድዮች  መሰራታቸውን የጠቆሙት አቶ ደረጄ የፋይናንስ ውስንነት ለፕሮጀክቶች አፈፃፀም አሉታዊ ጫና እንዳለው  ነው የገለፁት፡፡  

በቀጣይ ከሰበታ ተነስቶ በአምቦ ጅማ፣ በደሌ፣ የሚሄድና የምዕራቡን የሀገሪቱ ክፍል ከመሃል ሀገር ጋርና ከወደብ ጋር የሚያስተሳሰር፣ ከሞጆ ሃዋሳ፣ ሞያሌ ወደ ኬንያ የሚሄድ እና ከወልዲያ በባሀርዳር ወረታ፣ ወደ ሱዳን የሚሄድ የባቡር መስመር  የሚገነባ መሆኑም የተገኘው መረጃ የሚያመለክት ሲሆን ከባህርዳር ፍኖተ ሰላም የሚሄድ መስመርም  ይገኝበታል ነው ያሉት አቶ ደረጄ፡፡ ፡፡

እነዚህ  የባቡር መስመሮች ሲገነቡ የልማት ኮሪደሮችን የማስተሳሰር፣ ከተሞችን የማነቃቃትና አማራጭ ወደቦችን ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት የማግኘት እድልን የማስፋትና ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚኖራትን ኢኮኖሚያዊ እና የህዝብ ለህዝብ ትስስር የሚያጠናክሩ የእድገትና የለውጥ ሃዲዶች  ይሆናሉ፡፡

በሀገሪቱ ሁሉንም አከባቢ በባቡር ማስተሳሰር ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነትን፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የህዝቦች መስተጋብርን  የሚያጠናክር  መሆኑና ኢትዮጵያ ለሌሎች ሀገራት መንግስታት እና ህዝቦች የልማት ተምሳሌት እንድትሆን ያግዛታል በማለት  ነው አቶ ደረጄ ሀሳባቸውን ያካፈሉን፡፡

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር መስመር እና የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት በኤሌክትሪክ ሃይል የሚሰሩ መሆናቸው ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ቀዳሚ ያደርጋታል ያሉት አቶ ደረጄ  ከብክለት የፀዳ  የአረንጓዴ ኢኮኖሚን በመገንባትም ለሌሎች ሀገራት ተምሳሌት መሆኗን ነው ያነሱት።በኤሌክትሪክ ሃይል መሥራታቸው የአረንጓዴ ኢኮኖሚን ከመገንባት ባሻገርም ሀገሪቱ ለነዳጅ የምትከፍለውን የውጭ ምንዛሪ  በማስቀረት ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል ነው ያሉት፡፡  

የውጭ ተቋራጮች የባቡር መስመሮችን ሲገነቡ ለኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በሲቪል፣ በኤሌክትሪካልና በሜካኒካል ምህንድስና የእውቅት ሽግግር እንዲፈጥሩ እየተደረገ  መሆኑን የጠቆሙት አቶ ደረጄ በሀገር ውስጥ የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራትም ከአዲስ አበባ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር እየተሰራ ነው ይላሉ፡፡ በቀጣይ ደግሞ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን እራሱን የቻለ የባቡር አካዳሚ ለማቋቋም ጥናት ተጠናቆ ወደ ስራ እየተገባ መሆኑን አቶ ደረጄ ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ከቁጥጥር ጀምሮ እስከ ካፒቴን ድረስ እየሰሩ ያሉት ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ያነሱት አቶ ደረጄ  ቻይናውያን የባቡር መስመሩን በመጠገንና የባቡር ትራንስፖርቱን በማስተዳደር ላይ እንደሚገኙም  ገልፀውልናል፡፡

ኢትዮጵያ 75 በመቶ ጂቡቲ 25 በመቶ ድርሻ የያዙበትን የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት ለ6 ዓመት እንዲያስተዳድሩ ለሁለት የቻይና ኩባንያዎች መሰጠቱ  ተገልጿል። በዚህም ሁለቱ ኩባንያዎች ኢትዮጵያውያንን እና ጂቡቲያውያንን የባቡር ተቆጣጣሪ፣ ካፒቴን እና የጥገና ባለሙያዎችን እንዲያበቁ  እንደሚደረግ ነው የተገለፀው።

ከዚህ ጎን ለጎን የባቡር መስመሮች በሚገነቡበት ወቅት የአካባቢው ህብረተሰብ ከጉልበት ስራ እስከ ምህንድስና ስራዎች ድረስ የስራ እድል ተጠቃሚ  እያደረጋቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ከመደጎም ባሻገር ለእውቀት ሽግግርም ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

በዚህም ወጣቶች ተደራጅተው በየአካባቢው የባቡር ርብራብ በማምረት ተጠቃሚ እየሆኑ ነው ያሉት አቶ ደረጄ የባቡር መስመሮች ግንባታቸው ተጠናቆ ስራ ሲጀምሩ በፌርማታዎች አካባቢ ትኬት የመቁረጥ፣ የመስተንግዶ፣ የፓርኪንግ፣ የጥበቃና ሌሎች ስራዎች ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ።

የባቡር መስመር ግንባታ ፕሮጀክት ለኢኮኖሚያዊና ህዝብ ለህዝብ ትስስር የበኩሉን ሚና የሚጫወት ከመሆኑም ባሻገር ኢንቨስትመንትን ለመሳብ አስተዋጽኦው ከፍተኛ በመሆኑ የሀገሪቷን ኢኮኖሚ አንድ እርምጃ ወደ ፊት ይወስዳታል፡፡ የዚህ ፕሮጀክት መስፋፋት ከሀገር እድገትና አቅም አኳያ ገና ተጀመረ እንጂ  ያልተጠናቀቀ በመሆኑ ቀጣይ መሰል ፕሮጀክቶች ተጠናክረሮ ይቀጥል እንላለን፡፡

 

 

Last modified on Monday, 12 March 2018 14:23
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን