አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

ደም መለገስ ለሰጪውም ለተቀባዩም ጥቅም ነው !

17 Feb 2017
4164 times

ወ/ሚካኤል ገ/መድህን(ኢዜአ)

 ደም በስውነታችን ውስጥ የሚዘዋወር ፍሳሽ ነው፣ዋና ጥቅሙ ምግብና ኦክሰጅንን ለተለያዩ የሰውነታችን ህዋሳት ማቀበልና ከህዋሳት ውስጥ የሚወጣውን ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ(co2) እና ሌሎች ቆሻሻዎች ማስወገድ ነው።

አንድ ጤናማ የሆነ ሰው ከ5 እሰከ 6 ሊትር የሚሆን ደም በሰውነቱ ውስጥ እንዳለ መረጃዎች ይጠቁማሉ ።

የደም አይነቶች አራት ናቸው ኤ፣ቢ፣ኤቢና ኦ ናቸው።ይህ ማለት በደም ልገሳ ጊዜ የሚለገሰው ደም ከበሽተኛው ወይም ከደም ተቀባዩ አንድ አይነት መሆን አለበት።

በዚህ መሰረት ኤ አይነት ደም ያለው ሰው ኤ ወይም ኤቢ አይነት ደም ላላቸው ሰዎች መለገስ ይችላል፣ሲቀበል ግን ኤ ወይም ኦ ካላቸው ሰዎች ብቻ ነው።

ቢ አይነት ደም ያለው ሰው ቢ እና ኤቢ የደም አይነት ላላቸው ሰዎች መለገስ ይችላል፣ቢ ወይም ኦ የደም አይነት ካላቸው ሰዎች ደሞ ይቀበላል።

ኤቢ አይነት ደም ያለው ሰው ከሁሉም የደም አይነት መቀበል ይችላል ። ሲለግስ ግን ኤቢ የደም አይነት  ላለው ሰው ብቻ ነው።የዚህ አይነት ደም ያለው ሰው ሁለገብ ተቀባይ(universal recipient)ይባላል።

ኦ የደም አይነት ያለው ሰው ለሁሉም የደም አይነት ላለው ሰው ሊሰጥ ወይም ሊለግስ ይችላል ። ስለዚህ ኦ የደም አይነት ያለው ሰው ሁለገብ ለጋሽ(universal donor) ይባላል ።መስጠት እንጂ መቀበል አይችልም ። ከኦ የደም አይነት  ያለው ሰው ብቻ ይቀበላል ማለት ነው።

ስለ ደም እና የደም አይነቶች ይህን ያህል ካልኩኝ ደም በመለገስ የሚገኙ ጠቀሜታዎችን፣ደም ልገሳ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች እነማን እንደሆኑና አንድ ሰው ደም ለመለገስ የሚያስፈልጉትን ቅድመ ሁኔታዎች በተመለከተ ከመቐለ ደም ባንክ አገልግሎት ያገኘሁት መረጃ መሰረት አድረጌ ትንሽ ላካፍላችሁ ።

ደም መለገስ በፈቃደኝነት የሚደረግ በጎ ተግባር ነው፣ደም መለገስ ለለጋሹ የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው ።ከሁሉም ቀዳሚ የሰው ህይወት በመታደግ የሚያገኘው የመንፈስ እርካታ ወይም የህሊና እርፍት የላቀ ነው ።ከመለገሱ በፊት እንደ ኤች አይቪ፣የደም ግፊት፣የስኳር ፣ የጉበትና ከሌሎች በሽታዎች ነፃ መሆኑን  ምርመራ ያደርጋል ።ይህ ማለት እግረ መንገዱ የጤናው ሁኔታ ያውቃል ማለት ነው።

በጥናት እንደተረጋገጠው ደም የሚለግስ ሰው የልብ ህመሙ በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል ። ደም የሚለግስ ሰው የደም አይነቱ  ምን እንደሆነ እንዲያውቅ ይረዳል ። ደም መለገስ ህብረተሰብን የማገልገል ፍላጎትና ተነሳሽነት ያጎለብታል።

ሰውነታችን በየቀኑ አዳዲስ የደም ህዋስ ያዘጋጃል ። የደም ህዋሳት ደም ተለገሰም አልተለገሰም በየሶስት ወሩ ራሳቸው ስለሚሞቱ ደም መለገሱ በሰውነት የሚኖሩ ህዋሳት እንዲታደሱ ያደርጋል። ስለዚህ አሁን ያለንን ደም ከሶስት ወር በኋላ አይጠቅመንም ። በአዲስ ደም ስለሚተካ  ከሚባክን በመለገስ ህይወት በማዳን የራሳችንንና  የሌሎችን ህይወት እናድናለን ማለት ነው።

ደም ለመለገስ  ቅድመ ሁኔታዎች ያስፈልጉታል ።   ፈቃደኛ መሆን፣እድሜ ከ18 እስከ 65 ዓመት ፣ ከ45 ኪሎ ግራም  በላይ ክብደት፣ጤናማና ደም ከለገሰ 3 ወር የሞላበት መሆንን ይጠይቃል ።

ከለጋሾች የሚገኘውን ደም በወሊድ ምክንያት ደም ሊሚፈስባቸው እናቶች ፣ በአደጋ  ብዙ ደም ለሚፈስባቸው ሰዎች፣ከባድ የቀዶ ጥገና ህክምና ለሚያስፈልጋቸው ፣በተለያየ የጤና ችግር ምክንያት የደም ማነስ ችግር ላለባቸው፣ እንደተወለዱ ወዲያውኑ ደም ለሚያስፈልጋቸው ህጻናት፣በዘር የሚመጣ ደም ያለመርጋት በሽታ ወይም ሂሞፊሊያ ለሚያጋጥማቸው ሰዎች አገልግሎት ይውላል ።

በዚህ ምክንያት ብዙ ደም እንደሚያስፈልግና በሃገሪቱ የሚስተዋለውን የደም ፍላጎትና አቅርቦት ለማጣጣም የብሄራዊ ደም ባንክ ኃላፊነት ወስዶ እየሰራ እንደሆነ ይታወቃል።

በመላው አገሪቱ 25 የደም ባንኮች የተሟላ አገልገሎት እንዲሰጡ መደረጉንና ተጨማሪ 12 የደም ባንኮችን በመገንባት ቁጥራቸው ወደ 37 ለማሳደግ እየተሰራ እንደሆነም ከብሔራዊ ደም ባንክ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በትግራይ ከልል ሁለት የደም ባንኮች አሉ፣የመቐለና የአክሱም ደም ባንኮች ። በክልሉ ሶስት ዞኖች ማለት ማእከላዊ፣ምዕራብ እና ሴሜናዊ ምዕራብ ዘኖች ለማገልገል የተቋቋመው የአክሱም ባንክ አንዱ ነው።

በእነዚሀ ሶስት ዘኖች በደም እጥረት ችግር ምክንያት የሚሞት ሰው በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን  ነዉ  ከአክሱም ደም ባንክ አገልገሎት የተገኘ መረጃ የሚያሳየው ።

አቶ ሳምሶን የማነ የአክሱም ደም ባንክ አገልገሎተ ዋና ዳይሬክተር ናቸው ። እስከ አሁን ድረስ በተካሄዱ   የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች የህብረተሰቡ ደም የመለገስ ባህል አያደገ መጥቷል ። ደም መለገስ ህይወትን ማዳን ነው ብሎ ያመነው የአካባቢው ህብረተሰብ ተሳትፎው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ነው ።

ባላፉት 6 ወራት ከደም ለጋሾች  2 ሺህ 750 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ ነበር ። 1 ሺህ 818 ዩኒት ደም ተሰብስቦ  በሶስቱ ዞኖች  ለሚገኙ 16  ሆሰፒታሎች 1 ሺህ 165 ዩኒት  ደም መሰራጨቱን አቶ ሳምሶን ያስረዳሉ።

በወሊድ ምክንያትና በአደጋ ከፍተኛ የደም መፍሰስ ችግር የነበረባቸው ዜጎች በቂ ደም አግኝተው ድነው እንደተመለሱና በአሁኑ ጊዜ በደም እጥረት ምክንያት የሚሞት ዜጋ እንደሌለ ከሆሰፒታሎች የመጣላቸው ሪፖርት ዋቢ አድርገው ይጠቅሳሉ ።

ደም ባንኩ የደም ፍላጎት እየጨመረ መሆኑን በመገንዘብ ይህን ፍላጎት ለሟሟላት ከህብረተሰቡና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በቅስቀሳ፣ግንዛቤ በማስፋትና በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ስራ እያከናወነ መሆኑን አስረድተዋል ።

በሚቀጥሉት ወራት በሑመራ የደም መሰብሰቢያ ማእከል ይከፈታልም ብለዋል ።

የአክሱም ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ገብረሚካኤል ወልደገብርኤል  ያለፉት 6 ወራት ሪፖርት ጠቅሰው እንደተናገሩት  በደም እጥረት ምክንያት ከፍተኛ ችግር ላይ የነበሩ 289 እናቶችና አደጋ የደረሰባቸው አካላት በጊዜው ተጠቃሚ ሆነው ድነው ወደየቤታቸው  ተመልሰዋል ።

በአክሱም ቅድስት ማርያም ሆሰፒታል ሲታከሙ ያገኘናቸውና ከአክሱም ደም ባንክ ያገኙትን  ጥቅም የገለጽሉን ደግሞ ወይዘሮ አለም ብዙአየነ ይባላሉ ።

 ከሰሜናዊ ምዕራብ ዞን አስገደ ጽንብላ ወረዳ ራህዋ ቀበሌ አንደመጡ የተናገሩት ወይዘሮዋ ነፍሰ ጡር ናቸው። ወይዘሮ አለም የሚኖሩበት አካባቢ ሙቀታማ በመሆኑ በእርግዝና ወቅት  ለደም እጥረት አንደተጋለጡ ያስረዳሉ።

በደም እጥረት ምክንያት እሳቸውና ሆዳቸው ውስጥ ያለው ህጻን አደጋ ላይ መሆኑን በምርመራ እንደተረጋገጠና ወደ ሽሬ ስሑል አጠቃላይ ሆስፒታሉ ሪፈር አንደተባሉ በመግለጽ የእሳቸው አይነት ደም እንደሌለ ተነግሯቸው ወደ አክሱም ቅድስተ ማርያም ሆስፒታል እንዲሄዱ መታዘዛቸው ያስረዳሉ።

የነፍሰ ጡርዋ የደም አይነት ኦ ነው። ኦ የደም አይነት ያለው ሰው  ለሁሉም የደም አይነት መስጠት ሲችል መቀበል የሚችለው ግን ከኦ የደም አይነት ያለው ሰው ብቻ ነው።

 ወይዘሮ አለም  በአክሱም ቅድስት ማረያም ሆስፒታል የሚፈልጉትን የደም አይነት እንዳገኙና ሁለት ዩኒት ደም ተሰጥቶአቸው  አሁን በደህና ሁኔታ እንደሚገኙ  ተናግረዋል ።

ይህን ደም ባላገኝ በህይወት የመኖር እድሌ አስጊ ነበር ያሉት ወይዘሮዋ ደም መለገስ ከስጦታዎች ሁሉ የላቀ መሆኑን በመገንዘባቸው ደም ለጋሾችን አመስግነዋል ። ግንባር ቀደም ደም ለጋሽ ለመሆን መዘጋጀታቸው በመግለፅ መላው ህብረተሰብ ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል ።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን