አርዕስተ ዜና

ጽናት ያሸነፈው ፈተና

16 Feb 2017
2972 times

ከሰለሞን ተሰራ /ኢዜአ/

የአየር ፀባይ ለውጥ ለረሐብ አደጋ ከሚዳርጉ ጉዳዮች ቀዳሚ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት መረጃ መረብ ኢሪኒ ይጠቅሳል፡፡ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በአግባቡ ማቅረብ፣ ግጭት፣ ንግድ፣ የጉልበት ገበያ፣የህዝብ ብዛት ጫና፣ ባህላዊ ልማዶች እና ተጨማሪ ጉዳዮች ለድርቅ መከሰት ምክንያት ናቸው ብሎ ይገለፃል፡፡

ኤክስፐርቶች በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ የሚከሰተው የረሐብ አደጋ  አገሪቱ በዝናብ ላይ ጥገኛ በመሆኗ፣ በአነስተኛ እርሻ በመጠመዷ፣ በድርቅና በህዝብ ቁጥር ማደግ የመጣ ነው ብለው ይሞግታሉ፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና በአብዛኛው ከእጅ ወደ አፍ በሆነ አመራረት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ቀደም ባሉት ስርአቶች  ገበሬዎቹ ምርታቸውን ለማሳደግ የሚረዳ ድጋፍ ስለማይደረግላቸው ወይም ትርፍ ምርታቸውን የማስቀመጥ ልማድ ስለሌላቸው ዘወትር ችግር አያጣቸውም ነበር፡፡

ባለፉት 120 አመታት አገሪቱን ዘመናዊ ለማድረግ የተያዘው ጥረት እንዳለ ሆኖ አሁንም ከአገሪቱ ህዝብ 80 በመቶ የሚሆነው በግብርና ስራ ላይ የተሰማራ ነው በማለት ካልቸራል ሰርቫይቫል የተባለ ድረ ገፅ ሐሳቡን አስፍሯል፡፡

 የቤተ መንግስት ጦርና  የረሐብ አደጋ

የኢትዮጵያ የቤተ መንግስት ታሪክ ጸሐፊዎች ሐተታቸው ከረሐብና ድርቅ ተነጥሎ አያውቅም፡፡በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ ቦታ ያላቸው ሪቻርድ ፓንክረስት እንደጠቀሱት አገሪቱ ከ 15 ኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ እስከ 19 ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ በየአስር አመቱ አንድ ጊዜ ረሐብ እንደጎበኛት ጠቅሰዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ  ባደረጉት ጥናት ረሐብ የተፈጥሮ አደጋና ድርቅን ተከትሎ  ህብረተሰቡን  በምግብ እጥረት የሚያጠቃ  እና በቴክኖሎጂ አለመበልጸግ የሚከሰት ነው በማለት ይገልፁታል፡                                                                                 

በአገሪቱ  የረሐብ አደጋን ከተፈጥሮ በደል ጋር ማያያዝ የተለመደ ነው፡፡ በየጊዜው ይከናወኑ የነበሩ ውጊያዎች  እህል ከአካባቢው ሰዎች ተዘርፎ ለወታደሩ እንዲጫን ስለሚያስገድዱ ረሐብ ይከሰት ነበር በማለት ፖርቱጋላዊው የሐይማኖት አባት ቢ ቴሌዝ በ 17 ኛው ክፍለ ዘመን አገሪቱን ከጎበኘ በኋላ ባሰፈረው ጽሑፍ መግለፁ በታሪክ ድርሳናት ተከትቦ ይገኛል፡፡

የወታደሩ ብዛት ከአንበጣና ተምች  የበለጠ ሲሆን  አንበጦቹ የሚበሉት ሜዳ ላይ ያገኙትን ሲሆን ወታደሮቹ ግን ጓዳ ድረስ ዘልቀው እህል ይወስዳሉ ብሏል፡፡የኢትዮጵያ ጦር ብዛት ወንዶቹ 80 ሺ ሲጠጉ አጃቢ ሴቶቻቸው ደግሞ 30 ሺ ይደርሱ ነበር በማለት እንግሊዛዊው ኮሎኔል  በርክሌይ  የ 1860 ዓመታት ገጠመኙን ጽፏል፡፡

 

የዘውድ ስርአቱና ድርቁ

ዘ ቦርደን ፕሮጀክት የተባለ ድረ ገጽ ተለዋዋጩ የአየር ፀባይ የሰሜን ምስራቅ ወሎና የትግራይ አካባቢን በተደጋጋሚ ለድርቅ እንደሚዳርጋቸው ይገልፃል፡፡በታሪክ ከተመዘገቡት ክስተቶች አንዱ በ 1958 በትግራይ የደረሰው የረሐብ አደጋ ሲሆን 100 ሺ የሚጠጉ ሰዎችን ለምግብ እጥረት እንደዳረጋቸው ተገልጿል፡፡

የነገስታቱ ጦር ቁጥር እንዳለ ሆኖ ከ 1973-1974 በወሎ በተከሰተው ድርቅ ብቻ  300 ሺ ሰዎች መሞታቸው ይታወቃል፡፡ችግሩ የተከሰተው በምግብ እጥረት ብቻ ሳይሆን የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ባለመቻሉ መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች ይገልፃሉ፡፡ በዚህም ንጉሱ ስልጣናቸውን እንዳጡ ይናገራሉ፡፡

ንጉሱ  80ኛ አመት የልደት በአላቸውን 35 ሚሊዮን ዶላር አውጥተው ሲያከብሩ ከ 1971-1973 በተከሰተው ድርቅ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለሞትና ለችግር ተጋልጠው ነበር፡፡

 

 ደርግና የድርቁ መዘዝ

ሴፕቴምበር 12 -1982 ደርግ በርካታ ወጪ ያወጣበትን አስረኛውን የአብዮት በአል ለማክበር ሽር ጉድ ሲል ነበር፡፡ በተመሳሳይ በ1984 ደርግ ከ100 እስከ 200 ሚሊዮን ዶላር ለበአሉ ሲያወጣ  ሚሊዮኖች በድርቅ አደጋ ህይወታቸው እየተቀጠፈ ነበር፡፡

የደርግና የሐይለስላሴ አገዛዝ  የሚያመሳስሉባቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ህዝብ በረሐብ ሲያልቅ መንግስት ጦሩን ለማደራጀት ያደርገው የነበረው ሩጫ ሰብአዊነት የጎደለው መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡

ደርግ በጉልበት 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን ለማስፈር ባደረገው ሙከራ ከ 50 አሰከ 100 ሺ ሰዎች መሞታቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

 

ድርቅና የደርግ ኢኮኖሚ መንኮታኮት

በኖቨምበር 1984 የወጣ ሪፖርት ደርግ በኤርትራና ትግራይ የነበሩ  የድርቅ ተጠቂዎችን ከአካባቢያቸው በማራቅ ወደ ደቡብና አሮሚያ ክልሎች እንዳሰፈራቸው ይገልጻል፡፡ሰፈራው ከድርቁ ጋር የተያያዘ አለመሆኑ ይታመናል ሲል ካልቸራል ሰርቫይቭ በወቅቱ አስነብቦ ነበር፡፡

አገሪቱ ከ 1970 የድርቅ ገጠመኝ ሳታገግም በድጋሚ አደጋው ጎብኝቷታል፡፡በዊክ ፔዲያ የቀረበ ማሳያ ደግሞ በ1980 ዎቹ ብዛት ያላቸው የኤርትራ ፣ትግራይ፣ ወሎ ፣ ከፊል ጎንደርና ሸዋ አካባቢዎች የረሐብ አደጋው ጎብኝቷቸዋል፡፡በ 1984 የተከሰተው ድርቅ ረሐብ በማስከተል አብዛኛውን የሰሜኑን ክፍል አጥቅቷል፡፡

መንግስት እርዳታ የማድረስ አቅም እንደሌለው አሳይቶም አልፏል፡፡በአካባቢው የነበረው የምርት መበላሸትና ግጭት እርዳታ ለማድረስ አላስቻለም ነበር፡፡ በ1986 የተከሰተው ረሐብ ወደ ደቡብ በመሸጋገር 5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ህዝቦችን በእርዳታ ላይ ጥገኛ አድርጓቸው ነበር፡፡

ደርግ  የረሐብ አደጋውን ለመከላከል ያሳየው ቸልተኛነት ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ ከፍተኛ ውግዘት አስከትሎበታል፡፡ወዳጅ የተባሉ መንግስታት ሳይቀሩ እርዳታው በወቅቱ  ነፃ አውጪዎቹ ይዘዋቸው ወደነበሩት መንደር እንዳይዘልቅ መከልከሉን ክፉኛ ወቅሰውታል፡፡ችግሩ የአገሪቱን ያልጠገገ ኢኮኖሚ አንኮታኩቶታል፡፡በ 1985  እና 1986 ብቻ 600 ሺ የሚጠጉ ሰዎች ከቀዬአቸወ በግዴታ  ተፈናቅለዋል፡፡

 

አለም  አቀፍ ምልከታ

በ 1984 ቱ ድርቅ 8 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የረሐብ አደጋው  ሰለባ ሲሆኑ 1 ሚሊዮን የሚጠጉት ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡በዛው አመት ኦክቶበር 23 የቢቢሲ ዘጋቢዎች ችግሩን የዳሰሱት ሲሆን በምድር ላይ ያለ ገሐነም ሲሉ ትዕይንቱን ገልጸውታል፡፡

በሌላ በኩል በ1984 በተከሰተው የረሐብ  አደጋ 7 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሰዎች ተጠቅተው የ 600 ሺ ሰዎች ህይወት ሲቀጠፍ በ 2003 ግን 13 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሰዎች የረሐብ አደጋ ተደቅኖባቸው የሞቱት 300 ብቻ ነበሩ፡፡

የኤልኒኖ ክስተት

አገሪቱ ገጥሟት በነበረው የኤልኒኖ ክስተት  በሃገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች አስከፊ ድርቅ መከሰቱ ይታወቃል። ችግሩን ተከትሎ ዜጎች ለምግብ እጥረት ተጋልጠዋል።

መንግስት ድርቁ  ከታየበት ወቅት ጀምሮ “በምግብ እጥረት የአንድም ሰው ህይወት መጥፋት የለበትም” የሚል ቁርጠኛ አቋም  በመያዝ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ጋር የችግሩን ስፋት በማጥናትና   ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሳወቅ ድጋፍ ከመጠየቅ ጎን ለጎን ከመጠባበቂያ የእህል ክምችት በማውጣት እርዳታ አቅርቧል።

ኢትዮጵያ በድርቅ ሳቢያ የተከሰተውን የምግብ እጥረት ለመጀመሪያ ጊዜ በራስ አቅም መከላከል የምትችልበት ሁኔታ የተፈጠረው ባለፉት አስርት ዓመታት በተከታታይ ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገቧ ነው። የምግብ እጥረቱ ሲከሰት 451 ሺህ ሜትሪክ ቶን (4 ሚሊየን 451 ሺህ ኩንታል) የመጠባበቂያ እህል ክምችት ነበር፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት  የምግብ እጥረቱን ለመቋቋም ያጋጠመውን የፋይናንስ ጉድለት ለመሙላት በተደረገው ዘመቻ ላይ የኢፌዴሪ መንግስት የድርቁን ተፅዕኖ ለመቋቋም እና በዜጎች ላይ ምንም ጉዳት እንዳያደርስ የልማት ፕሮጀክቶቹን እስከማጠፍ ድረስ ሄዶ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑን ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

መንግስት አሁንም ቀዳሚ የፋይናንስ ምንጭ ሆኖ መቀጠሉን ያነሳው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መግለጫ፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የድርቁን ጉዳት ለመቋቋም የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባው አሳስቧል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ የኢትዮጵያ አስተባባሪ አሁና አይዛኮንዋ ኦኑቺ መንግስት ፋይናንስን በቀዳሚነት በማቅረብ የተለያዩ ዘርፎችን አስተባብሮ ለድርቁ ምላሽ በመስጠት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ድርቁ ያስከተለውን ሃገራዊ ጫና በመቋቋም ረገድ የኢፌዴሪ መንግስት የመሪነት ድርሻ ወስዷል። መንግስት በወቅቱ 381 ሚሊዮን ዶላር ወይም ስምንት ቢሊዮን ብር ወጪ አድርጎ ድርቁ ላስከተለው ተፅዕኖ ምላሽ ሰጥቷል።

ለምግብ እጥረት የተጋለጡት ዜጎች ቁጥር ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ከታዩት ሁሉ ከፍተኛው ቢሆንም  በምግብ እጥረት ሳቢያ የአንድም ሰው ህይወት አልጠፋም።

ድርቁ ያስከተለውን የምግብ እጥረት በራስ አቅምም ሆነ በእርዳታ ለመከላከል ከሚደረገው ርብርብ ባሻገር፣ ኢኮኖሚውን በዘላቂነት በማሳደግ ዝግጁነቱን ከፍ ማድረግ ተችሏል።

ድህረ ኤልኒኖ

ከሕዳር 7/2009 ጀምሮ በመላው ሀገሪቱ (በ246 ወረዳዎች) 23 ቡድኖችን በማሰማራት በተከናወነው የዳሰሳ ጥናት 5.6 ሚሊዮን ሕዝቦች ለድርቅ መጋለጣቸውንና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው  መለየቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ  መግለጻቸው በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ድርቅ ለመቋቋም 948 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልጋት ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

የድርቅ ተጋላጮቹ በዋናነት በአርብቶ አደር አካባቢዎች  የሚገኙ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል 36 በመቶ፣ በሶማሌ 29 በመቶ እንዲሁም በአማራ 11 በመቶ እንደሚደርስ  የዳሰሳ ምልከታው አሳይቷል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ ከተያዘው በጀት ውስጥ 198 ሚሊዮን ብር ለትምህርት ቤት ምገባ፣ እንዲሁም 118 ሚሊዮን ብር ለእንስሳትና አሳ መድሐኒትና መኖ አቅርቦት እንደሚውል ታውቆአል፡፡

 ቀደም ሲል በተደረገው የመኸር ጥናት ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑት ዜጎች ቁጥር ከ10.2 ሚሊዮን ወደ 5.6 ሚሊዮን መቀነስ መቻሉንም አቶ ምትኩ አስረድተዋል፡፡  

መንግስት 16.5 ቢሊዮን ብር በመመደብ በኤልኒኖ ድርቅ ለተጠቁ ዜጎች የምግብና ምግብ ነክ፣ ጤና፣ ትምህርትና ውሀ በማቅረብ በሰዎችና በእንስሳት ላይ ሊፈጠር የሚችለውን አደጋ ማቃለል ችሏል፡፡

ድርቁ ያስከተለውን ጉዳት ለመከላከል 255 ሺ 571 ሜትሪክ ቶን እህል፣14 ሺ 863 ሜትሪክ ቶን ጥራጥሬ ፣3 ሺ 673 ሜትሪክ ቶን አልሚ ምግብ እና 4 ሺ 117 ሜትሪክ ቶን የምግብ ዘይት ለስርጭት ዝግጁ ተደርጓል፡፡መንግስትም 141 ሺ 510 ሜትሪክ ቶን እህል ከስትራቴጂክ መጠባበቂያ ምግብ ክምችት ኤጀንሲ በብድር ለማግኘት ችሏል፡፡

በ 2009 ሁለተኛው ወሰን ትምህርት 1 ሚሊዮን 122 ሺ 555 የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች የአስቸኳይ ጊዜ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

በድርቅ በተጎዱ ክልሎች የአስቸኳይ ጊዜ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራምን ለማካሄድ ከመንግስት የተመደበውን 198 ሚሊዮን 608 ሺ 76 ብር ክልሎቹ ባላቸው ድጋፍ የሚፈልጉ ተማሪዎች ብዛት ተሰልቶ የበጀት ድልድል ተሰርቶ መላኩ ተገልጿል፡፡

የብሔራዊ ሚትዮሮሎጂ ኤጀንሲ ያወጣው የ 2009 በልግ ትንበያ የበልግ ዝናብ በአርብቶ አደር አካባቢዎች ከመደበኛ በታች ስለሚሆን ቅድመ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስቧል፡፡

የባለፈው አመት ድርቅ ተሻጋሪ አሉታዊ ተፅእኖ፣ከመስከረም አጋማሽ እስከ ህዳር ወር መዝነብ የነበረበት ዝናብ መስተጓጎል እና ቀጣይ በልግ ከመደበኛ በታች መሆን ሁኔታውን ፈታኝ ሊያደርገው እንደሚችልም መረጃው ጠቅሷል፡፡

የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ኢትዮጵያ በተለይም ባለፈው ዓመት ከዓመታት በኋላ ያጋጠማትን ድርቅ በራሷ አቅም በመመከት በሰውና በእንሰሳት ላይ ይደርስ የነበረውን ጉዳት መከላከል መቻሏ የሚወደስ ነው ብለዋል።

ዋና ጸሓፊው አንቶኒዮ ጉተሬዝና የድርጅቱ  የእርዳታ ዋና ኃላፊ ስቲፈን ኦብራይን የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ  የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሪቱ የተከሰተውን ድርቅ ለመከላከል ለሚወስደው እርምጃ ድጋፍ እንዲሠጥ ጥሪ ማድረጋቸውን ዋልታ ድረ ገፅ ጠቅሷል፡፡

ለድርቅ ተጋላጮች አፋጣኝ ምላሽ መሥጠት  አስፈላጊ  መሆኑን  የተመድ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ኃላፊ ስቴፈን  አብራይን ገልጸው የኢትዮጵያ  መንግሥት  እ.ኤ.አ በ2017  ለሰብዓዊ እርዳታ  ያስፈልገኛል ብሎ ላቀረበው ድጋፍ አለም አቀፉ ማሕበረሰብ  ምላሽ  እንዲሠጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በየትኛውም የአለም አካባቢ ለሚከሰት ድርቅ ምላሽ መስጠት በጎ ምግባር ብቻ ሳይሆን የአለምን ጥቅም የማስከበር ጉዳይ  መሆኑንም  ሰሞኑን በተካሄደው 28ኛው  የአፍሪካ  የመሪዎች ጉባኤ ላይ በስፋት ተንጸባርቋል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን