አርዕስተ ዜና

የማህበረሰብ ብዝኃ ሕይወት ባንክ - በደጋማው ጌዴኦ

14 Feb 2017
2847 times

ሃብታሙ መኮንን -ከዲላ ኢዜአ

በጌዴኦ ዞን ከሚገኙ ደጋማ አካባቢዎች የምትመደበው የቡሌ ወረዳ ከሰብል ዝርያዎች ገብስ ፣ ስንዴ ፣ አተር ፤ ባቄላ ፣ ተልባ ፣ጠመዥ ፣ አጃ ፣ ሰነፍ ገብስና   መሰል ዝርያዎች ፤ ከስራስር ተክሎች ደግሞ እንሰትና ድንች በብዛት ይመረትባታል ፡፡

አርሶ አደሮቿም እነዚህን ሀገር በቀል ሰብሎችና ተክሎች ለዘመናት በማምረት ፣ ለምግብና ለመድኃኒት ፍጆታ በማዋል ፣ ከተረፈም ለገበያ በማቅረብ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲያሸጋግራቸው ቆይቷል ፡፡

ዘመን ሲለወጥ ነባራዊ ሁኔታዎች መለወጣቸው አይቀሬ ነውና  ቀንቶት ያመረተው ምርት የእለት ጉርሱን ከቻለለት ፣ ቤተሰቡን አጥግቦ ካሳደረለት ተመስገን ብሎ ካልሆነለትና ማሳው ምርት ከነፈገው ደግሞ ለተመፅዋችነት ሲዳረግ የከረመውን አርሶ አደር ሕይወት ለመቀየር ብሎም ካንጠፈጠፈው ወዙ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ የዘልማዳዊው አመራረት ዘዴ ማሻሻል ግድ ሆነ ፡፡

እናም ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝቧ በግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ውስጥ የታቀፈው ሀገራችን ኢትዮጵያ የገጠር ልማት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ነድፋ የአርሶ አደሩን የአመራረት ሂደት ማዘመኑን ተያያዘቸው ፡፡

እነዚህ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተግባራዊ በሆኑባቸው ጥቂት አመታት ውስጥ  በየጊዜው በምርምር የሚገኙና የተሻሻሉ ዝርያዎች እንዲሁም አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለአርሶ አደሩ በመዳረሳቸው በርካቶች ከነበሩበት የጠባቂነት እሽክርክሪት ተላቀው ባለሀብት መሆን ጀምረዋል ፡፡

ይሁን እንጂ የእነዚህ የተሻሻሉ ዝርያዎች መበራከት ለዘመናት ከአየር ጸባይና ከመሬት ተፈጥሯዊ ይዘት ጋር ተላምደው የኖሩ ፤ ከምግብነት ባለፈ የመድኃኒትነት ይዘት ያላቸው ፤ የአየረ ንብረት ለውጥ ቢከሰት ምርታማነታቸው ቢቀንስ እንጂ ፈጽመው የማይከስሙ ሀገር በቀል ዝርያዎች ከአርሶ አደሩ እጅ ቀስ በቀስ እንዲወጡና እንዲረሱ ምክንያት ሆኗል ፡፡

ይህ ሁኔታ በእጅጉ ያሳሰባቸው የቡሌ ወረዳ አንደኛ አኮሎ ቀበሌ አርሶ አደሮች በጉዳዩ ዙሪያ ተሰባስበው መከሩ ፤ እናም እየጠፉ ያሉ የብዝኃ ሕይወት ሀብቶቻችንን መታደግ አለብን ብለው ተነሱ ፡፡

በ2005 ዓ.ም የክልሉና የዞኑ አካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ቢሮዎች ጽሕፈት ቤት እገዛ ታክሎበት በስሩ 15 ሴቶችና 35 ወንዶችን አቅፎ "ሆርሲንሶ" የነባር ሰብል ጥበቃና አምራች መሰረታዊ ሕብረት ስራ ማህበር በሚል ስያሜ የማህበረሰብ የዘር ባንክ ተቋቋመ ፡፡

የዘር ባንኩ በአሁኑ ወቅት 96 ወንድና 22 ሴት በድምሩ 118 አባላትን ይዞ እየተመናመኑ ያሉ ቦርሼ፣ መሎ፣ ጣመዴ፣ ሰነፍ ገብስ፣ ኮቲቻ የተሰኙ የገብስ ዝርያዎች ቀይና ጥቁር ስንዴ፣ ጎላሎ ወይም ነጭ አተር ባቄላና ተልባ፣ አጃ ጠመዥ የመሳሰሉ ሰብሎችና ለስብራት እንዲሁም ለወላድ ወገብ ጠጋኝ መድሃኒትነት ያላቸው እንሰትና የዕፅዋት  ዝርያዎችን በማምረትና በመንከባከብ ላይ ይገኛል፡፡

አባል አርሶ አደሮቹ ፤ እየጠፉ ያሉ ሃገር በቀል የሰብል ዝርያዎችን በማሳቸው በማባዛት የዘር አማራጫቸውን ከማስፋት ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ መቻላቸውን ነው የገለፁት ፡፡

ከባንኩ የሚወስዱትን የዘር ሰብል በምርት መሰብሰቢያ ወቅት በውላቸው መሰረት 20 በመቶ ወለድ በማከል እንደሚመልሱ ፤ በዚህም የዘር ዋስትናቸው ሊረጋገጥ መቻሉን ጠቅሰዋል ፡፡

አርሶ አደር ከበደ አዶላ በየጊዜው ከማህበራቸው በመውሰድ ሀገር በቀል የአተር ፣ ገብስና  የስንዴ ዝርያዎችን በማሳቸው ዘርተው ባገኙት ገቢ የመኖሪያ ቤታቸውን በቆርቆሮ  ለመለወጥና ኑሮአቸውን ለማሻሻል ፤ ልጆቻቸውንም ምንም ሳይጓደልባቸው ለማስተማር እንደቻሉ ተናግረዋል ፡፡

ሌላኛው አርሶ አደር አለሙ አዶላ ማህበሩ በቅርበት የዘር እጥረት እንዳያጋጥማቸው የዘር ብድር በማመቻቸት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸውና ዝርያዎቹ የአካባቢውን አየር  የተለማመዱ  በመሆናቸው  ያለምንም ስጋት እያመረቱ  ከቤት ፍጆታ ባለፈ ለገበያ  እንደሚያቀርቡ  ገልፀዋል ፡፡

በተደጋጋሚ ከማህበሩ በኪሎ ግራም የሚወስዱት የዘር ብድር 4እና 5 ኩንታል ምርት በማግኘት ማህበሩ የበለጠ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን የገለጹት አርሶ አደር ቦጋለ ጃርሶ ናቸው፡፡

ዘንድሮ በብድር ከወሰዱት 6 ሲኒ ተልባ ከ5 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቁ አስረድተዋል ፡፡

ነባር የባቄላ ዝርያ በማሳቸው በመዝራት ተጠቃሚ የሆኑት ሴት አርሶ አደር ሙሉነሽ ዱማሮ በበኩላቸው በማህበሩ ውስጥ የሚገኙ  ሴት አርሶ አደሮችን በማስተባበር የላቀ ተጠቃሚ ለመሆን እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል ፡፡

በጌዴኦ ዞን አካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ጽ/ቤት የብዝሃ ሕይወት ጥበቃና አጠቃቀም ዋና ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሞገስ ተሰማ በቡሌ ወረዳ አንደኛ ኦኮሉ ቀበሌበ2005 ዓ.ም የተቋቋመው ሆርሲንሶ የነባር ሰብል ጥበቃና አምራች መሰረታዊ ሕብረት ስራ ማህበር በማህበረሰብ የዘር ባንክ አገልግሎት መልካም እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሆነ ተናግረዋል ፡፡

ከኢትዮዽያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስትቲዩት ፣ ከኢትዮ ኦርጋኒክ ሲድ አክሺንና  ከደቡብ ክልል  እርሻና  ተፈጥሮ ሃብት አካባቢ ጥበቃ ድጋፍ የሚደረግለት  የዘር  ባንኩ በእስካሁን  እንቅስቃሴው  በ264 አርሶ አደሮች ተሳትፎ 116.64 ሄክታር  መሬት ላይ  24.99  ኩንታል  የብርዕ ሰብሎችን በመዝራት 155.18 ኩንታል በማግኘትሊጠፉ የተቃረቡ ዝርያዎችን ለማበራከት መቻሉን አቶ ሞገስ ተሰማ ተናግረዋል ፡፡

ለግብርና፣ ለኢንደስትሪ ፣ ለጤና ዘርፎችና ለሌሎች የልማት ተግባራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክተው የብዝሃሕይወት ሃብት በሚገባ  በመሰብሰብ ጠብቆ በዘላቂነት የማቆየትና ተመራምሮ ጥቅም ላይ ለማዋል ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ይገኛል  ያሉት በክልሉ አካባቢ ጥበቃናደን ልማት ቢሮ የብዝሃ ህይወት ስራ ሂደት ባለቤት አቶ ደበበ ጋሻውበዛ ናቸው ፡፡

ለአብነትም በክልሉ ሲዳማ፣ ጉራጌ፣ ወላይታ፣ ዳውሮ፣ ሃዲያ፣ ከንባታ ጠንባሮና የሰገን አካባቢ ሕቦች ዞን የማህበረሰብ የዘር ባንክ በማቋቋም በተለያዩ ምክንያቶች ከአካባቢው  የጠፉ  የሰብል አይነቶችና ዝርያዎች መልሶ የማልማት ለአርሶ አደሩ የዘር አማራጭ ማስፋትና የዘር እጥረት የሚያጋጥማቸውን አርሶ አደሮች በመታደግ በመሬታቸው ዘርተው  እንዲጠቀሙ  የዘር ብድር በመስጠት እገዛ እየተደረገ እንደሚገኝም አቶ ደበበ አብራርተዋል ፡፡

ይህ አደረጃጀት ከተፈጠረባቸው ጌዴኦ ዞን ቡሌ ወረዳ የሆርሲንሶ የነባር ሰብል ጥበቃና አምራች መሰረታዊ ሕብረት ስራ ማህበር የብርዕና ሥራ ሥር ዝርያዎችን በመንከባከብ ሊጠፉ  የተቃረቡ  ዝርያዎችን ለማበራከት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል  እንደሚገባና  የሥራ ሂደታቸው የገበያ ትስስሮችን በመፍጠር አርሶአደሮቹ ከሚያመርቱት ምርት የላቀ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ እያመቻቸ መሆኑን አቶ ደበበ አክለው ገልፀዋል ፡፡

ሀገራችን በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ለማሳካት ከነደፈቻቸው የገጠር ልማት ፖለሲዎችና ስትራቴጂዎቸ ጋር እኩል የሚያራምዱን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችና አዳዲስ የተሻሻሉ ዝርያዎችን መጠቀሙ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም  እየተመናመኑ ያሉ ነገር ግን የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም  ከምግብነት አልፎ ለመድኃኒትነት በመዋል አስተዋፅኦአቸው እጅግ የጎላ የብዝኀ ሕይወት ሀብቶቻችንን ተንከባክቦና ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍና በምርምር በመደገፍ ቀጣይነት ባለው መልኩ ጥቅም ላይ ማዋሉ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባ የትኩረት አቅጣጫ በመሆኑ እንደ "ሆርሲንሶ" ያሉ ማህበራት በላቀ ደረጃ ቢበረታቱ አንላለን ፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን