አርዕስተ ዜና

“ዕጽ የሀዩ፤ ዕጽ ይቀትል”

ከእንግዳ መላኩ /ኢዜአ/

የምንኖርባት ዓለማችን ባሏት ዕጽዋት አረንጓዴዋ ፕላኔት የሚል መጠሪያ ተሰጥቷታል፡፡ ዕጽዋት ቀዳሚዎቹ የምድራችን ህይወት ያላቸው አካላት እንደሆኑም ይነገራል፡፡ ዕጽዋት በሌሉበት የሰው ልጅ ህልውና አይታሰብም፡፡ ለዚህስ ሳይሆን ይቀራል ዕጽዋት ከፍጥረታት ቀዳሚዎቹ የሆኑት?

ዕጽዋት ንጹሕ አየር ለማግኘት፣ ለምግብነትና ለውሃ ምንጭነት ያገለግላሉ፡፡ ለዓለማችን ኢኮኖሚ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦም ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ አብዛኞቹ ፈዋሽ መድሃኒቶች የሚሰሩት ከዕጽዋት መሆኑን ማውሳትም የእጽዋትን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያጎላዋል፡፡

ፈዋሽ መድሃኒቶች ልክ እንደዛሬው በዘመን አፈራሽ መሳሪያዎች በታገዘ ጥናትና ምርምር መመረት ከመጀመራቸው በፊትም ቢሆን ሰዎች የተለያዩ እጽዋትን እየቀመሙ የተለያዩ በሽታዎችን ያድኑ እንደነበር  የታሪክ ማስረጃዎች ያወሳሉ፡፡ መሰል መድሃኒቶችን በባህላዊ መንገድ እየቀመሙ በልዩ ልዩ በሽታዎች የሚሰቃዩ ህሙማንን ለመፈወስ የሚደረጉ ሙከራዎች ዛሬም ድረስ በመላ ዓለማችን ይተገበራሉ፡፡

የሰው ልጅ ቀድመውት የተፈጠሩትን እጽዋት በየፈርጃቸው በመለየት ለተለያዩ አገልግሎቶች ለማዋል ዛሬም ድረስ በቴክኖሎጂ የታገዘ ጥናትና ምርምር ከማድረግ ወደ ኋላ አላለም፡፡

ለምሳሌ ያህል ቲዮፊሊን የተሰኘው የአስም ማስታገሻ መድሃኒት የሚዘጋጀው ከሻይ ቅጠልና ከቡና ነው፡፡ ካንሰርን ለማከም ጥቅም ላይ የሚውለው ቪንክረስቲን የተሰኘ መድሃኒትም እንዲሁ ከቪንካ ሮዚያ  ዕጽ ነው የሚዘጋጀው፡፡ ማይግሬይን የሚባለውን የራስ ምታት ለማስታገስ ጥቅም ላይ የሚውለውና ኤርጎታ በመባል የሚታወቀው መድሃኒትም ከአጃ እንደ ሚዘጋጅ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በዘርፉ በተደረጉ ጥናትና ምርምሮችም ለጤና ተስማሚና ጎጂ /አደገኛ/ የሚባሉት እጽዋት ተለይተዋል፡፡ አንዳንዶቹ እጽዋት ደግሞ እንዳይመረቱና እንዳይዘዋወሩም ጭምር ዓለም ዓቀፍ ክልከላ ተደርጎባቸዋል፡፡

እኤአ የ1991ዱ የተባበሩት መንግሥታት የአደንዛዥ ዕጽዋት ስምምነት ለህክምናና መሰል የምርምር ተግባራት ካልሆነ በስተቀር አደንዛዥ ዕጾችንና በሰው ልጅ ጤና ላይ መሰል ተጽዕኖ የሚያስከትሉ መድሃኒቶችን ምርትና አቅርቦት ለመገደብ የተፈረመ ዓለም ዓቀፋዊ ስምምነት ነው፡፡

ይህ ስምምነት ካናቢስን ጨምሮ ሌሎች መሰል ተጽዕኖ የሚያስከትሉ ዕጾችን በማካተቱ ተጠቀሰ እንጂ ከዚያ በፊትም ኮካና ኦፒየም የተሰኙ አደንዛዥ እጾችን ብቻ ለመከልከል የተፈረመ ስምምነት እንደነበር መገንዘብ ያሻል፡፡

ካናቢስ ከባለ አበባ እጽዋት የሚመደብ ሲሆን በውስጡም ሶስት ያህል ዝርያዎችን ያቅፋል፡፡ ሰዎች ይህን ዕጽ ለመድሃኒት፣ ለማነቃቂያና መሰል ተግባራት ጥቅም ላይ ያውሉታል፡፡

ለዚህና መሰል ህጋዊ ተግባራት እኤአ በ2013 በዓለም ዓቀፍ ደረጃ 60 ሺህ 400 ኪሎ ግራም ካናቢስ በህጋዊ መንገድ ተመርቷል፡፡ በ2014 የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት 185.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ካናቢስ የተሰኘውን ዕጽ ይጠቀማሉ፡፡

እስከ 2015 ዓ.ም 185 አባል ሃገራት ጸረ አበረታች ዕጽ ስምምነቱን ፈርመዋል፡፡ ኢትዮጵያም ከነዚህ ሀገራት አንዷ እንደመሆኗ መጠን የካናቢስና መሰል አደንዛዥ እጽዋትን ዝውውርና ምርት በህግ ከልክላለች፡፡

ምንም እንኳን ሀገሪቱ አደንዛዥ ዕጽዋትን በብዛት በማምረት ረገድ ስሟ ባይጠቀስም ከደቡብ አፍሪካ ኤዥያ በሚካሄደው የዕጽ ዝውውር መስመር ላይ መገኘቷ ግን ዓለም ዓቀፍ ትኩረት እንድታገኝ አድርጓታል፡፡

የአደንዛዥ እጾች መግቢያም ሆነ መውጫ በር በሆነው ቦሌ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ በተለይ እንደ ባንኮክ፣ ካራቺና ሞምባይ ከመሳሰሉ የስጋት ቀጠና ሀገራት በሚደረጉ በረራዎች ላይ የሀገሪቱ ፖሊስ በአነፍናፊ ውሾች የታገዘ ጠንካራ ቁጥጥርና ክትትል ያደርጋል፡፡

በሀገር ውስጥ ከሚካሄዱ የቁጥጥርና ክትትል ስራዎች ጎን ለጎን ኢትዮጵያ የአደንዛዥ ዕጽዋትን ዝውውር ለመግታት  ከጎረቤት ሀገራትና ከዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ጋርም ተቀናጅታ ትሰራለች፡፡፡

ኢትዮጵያም ሆነች ጎረቤት ሀገራት ከካናቢስ ንግድ የሚገኘው ትርፍ በዋናነት አክራሪ የእስልምና ቡድኖችን ለማጠናከር ይውላል የሚል እምነት አላቸው፡፡

በኢትዮጵያ ካናቢስ የተሰኘውን ዕጽ ይዞ መገኘት አዲስ ነገር ባይሆንም ዕጹን ያለ ህጋዊ ፈቃድ ይዞ መገኘት ግን በገንዘብም በእስራትም ያስቀጣል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚሁ ዕጽ ዝውውር ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ከዋሉ ግንባር ቀደም ተዋናዮች መካከል የታንዛንያ፣ ኡጋንዳ፣ ኢትዮጵያ፣ደቡብ አፍሪካ አልፎ አልፎ ደግሞ የቤልጂየምና የእንግሊዝ ዜጎች ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነውን ድርሻ እንደሚይዙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ኢትዮጵያ በተለይ ከ1980ዎቹ ወዲህ በዚህ ዕጽ ምርትና ዝውውር ላይ ጠንከር ያሉ እርምጃዎችን ወስዳለች፡፡ ለአብነት ያህልም በ1988 ዓ.ም 320 ሄክታር ማሳ ላይ የበቀለ ካናቢስ እንዲወድም ተደርጓል፡፡ እንዲሁም በ1999 ዓ.ም 194 ኪሎ ግራም ካናቢስ፣ በ2001 ዓ.ም ደግሞ 423 ኪሎ ግራም ካናቢስ ተወርሷል፡፡

በሀገሪቱ በተለይም በከተሞች አካባቢ የሚኖሩ ወጣቶችና ስራ አጦች ዕጹን ለመዝናኛነት እንደሚጠቀሙበት ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

ችግሩን ለመቀነስ መንግሥትና መገናኛ ብዙኃን ከማስተማር ባለፈ የቅድመ መከላከልና ህክምና ፕሮግራሞችንም በማስተዋወቅ ላይ ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ በሀገሪቱ የዚህ ዕጽ ተጠቃሚዎች ቁጥር አሁንም ድረስ አምብዛም እንዳልቀነሰ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚቀርቡት ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችም ይህንኑ ነው የሚያረጋግጡት፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለፈደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከቀረቡለትና ውሳኔ ከሰጠባቸው ጉዳዮች ውስጥ ለማሳያነት አንዱን እናንሳ፡፡

እነ ወይዘሮ ኢማን እስማኤል እናታቸው በሞት ተለይተዋቸው ሀዘን ተቀምጠዋል፡፡ ወዳጅ ዘመዶቻቸውም ከሩቅም ከቅርብም ሊያጽናኗቸው ካጠጋበቸው አልራቁም፡፡

በዚህ መካከል መሃመድ አስማኤል የተባለ ወንድማቸው አብሯቸው ሀዘኑን በመፍጀት ፋንታ በወጣ በገባ ቁጥር ሰላም ነሳቸው፡፡ የእነሱ አልበቃ ብሎት ህጻናት ልጆቻቸውንም ሳይቀር ማስፈራራት ጀመረ፡፡

እነ ወይዘሮ ኢማን መክረው አስመክረውት አልሰማ ቢላቸው በአካባቢያቸው ወደ ሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ሄደው ጉዳዩን አስረዱ፡፡ ፖሊስም ወንድማቸው ድጋሚ ተመልሶ መጥቶ መሰል ድርጊት የሚፈጽም ከሆነ በስልክ እንዲያሳውቁ ስልክ ቁጥር ሰጥቶ ወደ ቤታቸው ይመልሳቸዋል፡፡

መሀመድ እንደ ለመደው በማን አለብኝ ባይነት ሀዘን ላይ የተቀመጡ ቤተሰቦቹን ቁም ቅምጣቸውን ሲያሳጣቸው ሁኔታውን በስልክ ለፖሊስ አሳወቁ፡፡

ወዲያውኑ በአካባቢው ግዳጅ ላይ የነበሩ የአካባቢው ፖሊስ አባላት በቦታው ሲገኙ አቤቱታ የቀረበበትን ግለሰብ ያገኙታል፡፡ አባላቱ መሃመድን ሲፈትሹ በቀኝ ኪሱ ውስጥ በወረቀት የተጠቀለለ ነገር ያገኛሉ፡፡

የፖሊስ አባላቱ ይህን በወረቀት የተጠቀለለ ነገር እንደ ዋዛ አላለፉትም፡፡ በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የፎሪንሲክ ምርመራ ዳይሬክቶሬት ተልኮ አስፈላጊው ምርመራ ተደረገበት፡፡ ዳይሬክቶሬቱም በተላከለት ናሙና ላይ አካላዊና ኬሚካላዊ ፍተሻ አድርጎ ካናቢስ የተሰኘ ዕጽ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

ይኅ ዕጽ ደግሞ ሰዎችን ለሱስ በመዳረግ ለተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች መንስዔ እንዲሆኑ ስለሚገፋፋ እንዳይመረት፣ እንዳይዘዋወርና ጥቅም ላይ እንዳይውል የታገደ እጽ በመሆኑ ፖሊስ መረጃዎቹን አጠናቅሮ ጉዳዩን ወደ ፈደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መራው፡፡

ጉዳዩን የተመለከተው የፈደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አግባብ ካላቸው የህግ አንቀጾች ጋር አገናዝቦ በተከሳሹ ላይ የሁለት ዓመት ከስድስት ወር ጽኑ እስራት ወስኖበታል፡፡

ዕጽዋት ለአካባቢ ስነ ምህዳር ያላቸው ጠቀሜታ ባያጠያይቅም ለሰው ልጅ ምግብና ጤንነት በሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ግን ሁሉም ጠቃሚዎች አይደሉም፡፡ የሰው ልጅን ጤንነት ለመጠበቅና ወደ ሞት ከሚያንደረድሩ በሽታዎች ለመፈወስ ጥቅም ላይ የሚውሉ እጽዋት የመኖራቸውን ያህል ለሰው ልጅ ጤና አደገኛ የሆኑ እጽዋት እንዳሉም በጥናት ተረጋግጧል፡፡

በዘርፉ ጥናትና ምርምር ያደረጉ የሀገራችን ቀደምት ልሂቃንም ቀለም በጥብጠው ብራና ፍቀው “ዕጽ የሀዩ፣ ዕጽ ይቀትል::”የሚለውን ዓረፍተ ነገር ከትበው በቀደመው ቋንቋችን  የዕጽዋትን አዳኝነትና ገዳይነት አስነብበውናል፡፡

ዕጽዋት አዳኝም ገዳይም መሆናቸውን ከተገነዘብን ደግሞ ህጉ አየኝ አላየኝ በማለት በስውር እነዚህን ዕጽዋት ለመጠቀም ከመሽቀዳደም ይልቅ ራሳችን ወደ ሞትና ወደ አልተፈለገ ድርጊት ሊገፋፉን ከሚችሉ ዕጽዋት ራሳችንን ማራቅ ብልህነትም አዋቂነትም ይመስለኛል፤ ቸር ይግጠመን፡፡

ማስታወሻ፡- “ዕጽ የሀዩ፤ ዕጽ ይቀትል፡፡” የሚለው የግዕዝ ዓረፍተ ነገር ወደ አማርኛ ሲመለስ “ዕጽ ያድናል፤ይገድላልም” እንደማለት ነው፡፡

Last modified on Monday, 13 February 2017 18:26
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን