አርዕስተ ዜና

የደም ግብር ታዛቢ መልክዓ ምድሮች

891 times

የደም ግብር ታዛቢ መልክዓ ምድሮች

አየለ ያረጋል /ኢዜአ/

በነጫጭ ቀለማት ያሸበረቁ ካቦች ይስተዋላሉ፤ ከዙሪያ ገባ ጎራማይሌ ተራሮች ግርጌ። ዕልቆ ቢስ ትዕይንቶች በዘመናት ጅረት ፈሰዋል፤ ሠርቀው ሰርገዋል። እነኚህ ግዑዛን የአይን ዕማኝ ኮረብታዎች ግን ጥንትም እንደነበሩ አሉ፤ የትዕይንቱን ዑደቱ እየታዘቡ። ባሳለፍነው አንድ ምዓተ ዓመት እንኳን ስንቱን ተመለከቱ! ብቻ አጀብ ነው! ይሄው ከ122 ዓመታት በፊት በዙሪያቸው ተዳፋታማና ሜዳማ ስፍራዎች የደም ግብር ሲበላ አስተዋሉ። ከሰሞኑ ደግሞ እንደኔ በርካታ ካቦች በነጫጭ ቀለማት ሲቀልሙ ተመለከቱ። ቁጥቋጦዎች ሲራቆቱ ምድረ በዳዎች ሲጎፍሩ አይተዋል። የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ንጋት  ጀምሮ በፆመ ሁዳዴ የደም ግብር ሲበላ ነበሩ፤ ዛሬም ግብሩ የተበላባቸውን ስፍራዎች(መካነ መቃብሮች) እያዩ ነው። የአድዋ ተራሮችን ያክል ሕያው የታሪክ ምስክር ማን አለ! ዘመን አይሽሬ መልክዓ ምድሮችን ያክል!

ይሄው ከሰሞኑ 122ኛውን የአድዋ ጦርነት ድላችንን ዘከርን። በዚያች ተዓምረኛ ዕለት በአድዋ ተራሮች መንደር መድፎች አጓርተዋል፣ መትረየሶች አሽካክተዋል፣ እሳት ወርዷል፤ ጥይት ዘንቧል፣ ጎራዴ ተመዟል፣ ጦር ተሰብቋል! ምን አለፋን በጥቅሉ የክቡር ሰብዓ ዘሮች ደም ተገብሯል። የአድዋን ድል ህያውነት፣ እንቆቅልሽነት፣ አድማስ ዘለል ታሪክነት፣ የዓለም ነጸብራቅነት፣ አፍሪቃዊነት፣ ኢትዮጵያዊነት አልዘረዝርም። /“አሁንም አሁንም ለበላይ---” እንዳለው ዘፋኙ ስለ አድዋ(በቂ ነው ባይባልም) ብዙ ተብሏል አሁንም አሁንም ቢባልለት ግን አይጋነንም።/

ከዚያ ይልቅ የደራሲና ጋዜጠኛ ነብይ መኮነን ስንኞች(ስውር ስፌት) ልዋስ!

“አድዋ የደም ግብር ነው፤አበው የለኮሱት ቀንዲል

አድዋ የአፍሪካ ዱካ ነው፤ አበሽ የከተበው ፊደል

ላጥፋህ ቢሉት መች ይጠፋል፤ ጠላት በልቶ ያፈራ ተክል

ለዛሬም ታሪክ ነው፣ ‘ነገም ሌላ ቀን ነው’ ለሚል----”

አድዋን ጂጂና ቴዲ አፍሮ በዘፈኖቻቸው፣ እነ ፕሮፌሰር ሃይሌ ገሪማ በፊልማቸው፣ እነ ግራዝማች ግርማቸው ተክለ ሐዋርያት በተውኔታቸው፣ ጸጋዬ ገብረ መድህንና መሰሎቹ በቅኔያቸው፣ ሌሎች የኪነ ጥበብ ሰዎች በየመክሊቶቻቸው፣ የታሪክ ሊቃውንትም በጥናታቸው አውስተውታል፤ በዘመኑ አሳሾችም ሆነ በአሜሪካና አውሮፓ ጋዜጦች ተነግሮለታል። ለመሆኑ እኛ (ባለታሪኮች) ድፍን 122 ዓመታት ያስቆጠረውን አኩሪ ድላችንና የአብሮነት አርማችን ተግባብተንበታል! በተገቢው ሁኔታ ዘክረነዋል! ቋሚ መዘከርስ እስካሁን ለምን አልቆመለትም! የጽሁፌ መንደርደሪያና መድረሻም ‘ዝክረ አድዋ’ ነው!

ዝክረ አድዋ

“ጥቁር ሕዝቦች ከነጮች ጋር ያደረጓቸው ጦርነቶች ብዛት የትየሌለ ነው” ይላሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ኤምሬትስ ፕሮፌሰሩ ባህሩ ዘውዴ። (ፕሮፌሰሩ በዘንድሮው ክብረ በዓል በአድዋ ተገኝተው ነበር፣ ስለ ዝክረ አድዋ አስፈላጊነትና ታሪካዊ ፋይዳ በጽሁፋቸው አንስተዋል፤ በተለይም ለኢዜአ በጉዳዩ ላይ ሀሳብ ሰንዝረዋል)። “አንድም ጦርነት ግን በነጮች ላይ ድል አልተጎናጸፈም፤ ከወርቃማው የአድዋ ድል በስተቀር”። አድዋ አዲስ የታሪክ ምዕራፉ ሲከፍት በአንጻሩ ነባር አስተሳስብ ሰብሯል፤ የጥቁሮች የበታችነት ስሜትና የነጮች የበላይነት አስተሳስብ ለመጀመሪያ ጊዜ በአድዋ ተራሮች ግርጌ ተሽሯል።

ፕሮፌሰሩ ‘ኢትዮጵያዊያን ለምን አሸነፉ’ ለሚለው አራት መልሶች አሏቸው። የመጀመሪያው ከቅድመ አድዋ ጦርነቶች ያልታዬ ህብረት በአድዋ ጦርነት ወቅት መጥቷል። ከዳር እስከ ዳር ሁሉም አካባቢ ህዝብ ምንም አይነት ልዩነት ሳይገድበው ወደ አድዋ ተምሟል። በኤርትራና በትግሬ የነበሩ ለጠላት አድረው የነበሩ እንደነ ደጃዝማች ባሕታ ሐጎስና ራስ ስብሐት መሰል መሳፍንት ከዳግማዊ አጼ ምኒልክ ጐን ተሰልፈዋል።

በአጼ ምኒልክ የግዛት ማስፋፋት ዘመን የተገኘው ወታደራዊ ልምድን ደግሞ ለጦርነቱ በድል መወጣት በሁለተኛ ምክንያትነት ይጠቅሱታል። ሶስተኛው የአጼ ምኒልክ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ውጤት ነው። በየጊዜው በርካታ የወቅቱ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ገብተዋል። (በነገራችን ላይ በአድዋ ጦርነት በኢትዮጵያና በፋሽስት ጣሊያን መካከል የነበረው የጦር መሳሪያ ልዩነት እምብዛም ነው፤ ‘ኢትዮጵያን በኋላቀር የጦር መሳሪያ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀውን የኢጣሊያ ጦር አሸነፉ’ በሚባለው ተረክ ፕሮፌሰር ባህሩን ጨምሮ በርካታ የታሪክ ምሁራን አይስማሙበትም፤ ንጉሱ በርካታ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ወደ ኢትዮጵያ ቀድመው ገብተው ስለነበር። በእርግጥ ከ40 ዓመታት በኋላ በ5 ዓመቱ ጦርነት ፋሸስት ኢጣሊያ አውሮፕላን ይዛ ስትመጣ ኢትዮጵያ ግን ጦርና ጎራዴ ይዛ ጠብቃለች)                     

አራተኛው ምክንያት ደግሞ “የኢትዮጵያዊያን ታክቲካዊ የበላይነት ነው” ይላሉ። ዳግማዊ ምኒልክ በጦርነቱ ወቅት የተጠቀሙበት ስልት(ለምሳሌ የባሻ አውዓሎምን ስለላ ልብ ይሏል) ጠላትን በተሳሳተ ስሌት የመራና ጠላት በቀላሉ በወገን ጦር እንዲከበብ ያደረገ ነበር  ነው የሚሉት። በኢጣሊያ ወገን ከዘመቱ አራት ጀነራሎች መካከል አንደኛው ከመሸሹ ውጭ ሁለቱ በጦርነቱ ተገድለዋል፣ አንደኛውም ተማርኳል።

የአድዋ ድል ዘመናዊነት እንዲስፋፋ፣ የባቡር፣ ስልክ፣ ትምህርት፣ ፖስታ፣ ቴሌ፣ መንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶች እንዲዘረጉ፤ ኢትዮጵያ የትኛውም አፍሪካዊ አገር ያላገኘውን የራሷን የፖለቲካ ኢኮኖሚ እንድትመራ ያስቻላት ድል ነው። ቀድሞውኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ይዘት ቢኖረውም በኋላ ግን የአፍሪካዊያን የነጻነት እንቅስቃሴ ምልክት ሆኗል፤ የ‘ኢትዮጵያዊነት’ ጽንሠ ሃሳብ። እናም አድዋ ለ’ኢትዮጵያዊነት’ እና ለ’ፓን አፍሪካዊነት’ ጉዞ መሰረት ሆኗል፤ ቅኝ ግዛት እጣፈንታ አለመሆኑን አብስሯል፣ በርካታ የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት ቀንበር ሲላቀቁ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማትን ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ተሻምተዋል። ኃያላኑ የምዕራብ አገራት ኤምባሲዎቻቸውን በአዲስ አበባ ከፍተው ለኢትዮጵያ ነጻና ሉዓላዊነት ‘አሜን’ ብለው ዕውቅና ሰጥተዋል።

ሌላም አለ፤ ከአድዋ ድል በኋላ ኢትዮጵያዊያን የጀግንነት፣ የአገር ፍቅር፣ የአገር ሉዓላዊነት የማይበገር ወኔና ስነ ልቦና እሴቶችን አዳብሯል። ለአብነትም በአምስት ዓመቱ የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ፣ በደርግ ዘመን በነበረው የሶማሊያ ወረራ እንዲሁም በባድመ የነበረው የኢትዮጵያዊያን ኅብረት ከአድዋ የተገኘ የአብሮነትና አይበገሬነት እሴት መሆኑን የታሪክ ምሁሩ ያብራራሉ። በርግጥ ኢትዮጵያዊያን በአድዋ ጦርነት ርህራሄንና ሰብዓዊነትን ለነጭ ፋሽስት አስተምረዋል።

“አድዋ በአብሮነት የአሸናፊነት ተምሳሌት” እንዲል የዘንድሮው መፈክር የኢትዮጵያ ሕዝቦች ኅብረትና አንድነት ጥግ ድረስ የታዬበት ይህ ድል በተገቢው ሁኔታ አልተዘከረም። አድዋ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረው በ1923 ዓ.ም በድሉ ሰባተኛ ዓመት የዳግማዊ ምኒልክ ሐውልት ምረቃ ዕለትና የአጼ ኃይለሥላሴ ንግስና ዋዜማ ዕለት ነው። ከ1934 ዓ.ም ወዲህ ደግሞ በነጋሪት ጋዜጣ ታውጆ ብሔራዊ በዓል ተደርጎ በየዓመቱ መታሰብ ጀመረ። 100ኛ እና 103ኛ ክብረ በዓሉ በድምቀት መከበሩን ይገልጻሉ። ‘እንኳን እንደ አድዋ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ድል ቀርቶ በርካታ ትናንሽ ጦርነቶች እንኳን መታሰቢያ የጦር ሙዚዬም ገንብተዋል’ የሚሉት ፕሮፈሰር ባህሩ፤ ለዚህ “ኢትዮጵያዊያን አንዱ ይህን ታሪካዊ ታላቅ ድል እስካሁን ቋሚ መታሰቢያ መገንባት አለመቻላችን ሊያሳፍረን ይገባል”ይላሉ።

ፕሮፌሰሩ ስለ ጦርነቱ ተዋናዮች እንዲህ ይላሉ። “ከዳር እስከ ዳር ነው የተነሳው። ያኮረፈም ሳይቀር ገብቷል። ያኮረፈም ቢሆን በምንም መልኩ አያገባኝም ያለ የኢትዮጵያ ክፍል አልነበረም። ከወለጋ እስከ ሀረር፣ ከኤርትራ እስከ ሲዳሞ። ኤርትራ ውስጥ በኢጣሊያን ቅኝ ግዛት የነበረችው ኤርትራ እንኳን በደጃች ባሕታ ሐጎስ የሚመራ አመጽ ማካሄድ ችላለች። ያ ኢትዮጵያዊ ስሜት ነው። በቅኝ ግዛት ስር የነበሩት እንኳን። እና ዋናው የአድዋ እሴት ይሄ ነው።”

ወጣቱ ትውልድ ከአድዋ እሴቶች ‘አንድነትን’ ሊወርስ ይገባል ባይ ናቸው። “አንድነት ባይኖር፤ ያ! ሁሉ ኢትዮጵያዊ ባይተባበር ኖሮ ይህን አይነት ድል ሊገኝ አይችልም። የዚያ ውጤት ነው” ይላሉ። አያቶች በክንዳቸው መከዳነት፣ በአጥንታቸው ምሰሶነትና በደማቸው ቡኬት በኅብረት በማገራትና አስከብረው ባቆዩዋት አገር የልጅ ልጆች በአድዋ ታሪካቸው እንኳን የጋራ መግባባት ፈጥረዋል? ለሚለው መጠይቅ ፕሮፌሰር ባህሩ ‘መግባባት ቢኖርም በቂ አይደለም! ይበልጥ ይሰራበት” የሚል አስተያየት አላቸው።

“የጋራ መግባባት አለ፤ ይቀረዋል፣ የበለጠ መሰራት አለበት። ግን አሁን ጅማሬው ጥሩ ነው ፣ የጋራ መግባባት አለ፤ እስካሁን ድረስ ይሄ መግባባት አልነበርም ማለት ይቻላል”።

የዝክረ አድዋ ተስፋችን

ባለፈው ዓመት ከተከበረው 121ኛው የድሉ መታሰቢያ ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ነበር። በዓሉ የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ታቦ ምቤኪን ጨምሮ የአገሪቷ ርዕሰ ብሔርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በተገኙበት ነበር በአድዋ ከተማ በድምቀት የተከበረው። የአድዋ ድል ሕያውነት ባሳለፍነው ዓመት ተነስቷል፣ ብዙ ተብሏል። የፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ጽንሰ ሃሳብም ተነስቷል። ዘንድሮስ? 122ኛው መታሰቢያ ቀን ባሳለፍነው ሳምንት ሲከበር በተመሳሳይ  ርዕሰ ብሔሩ ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ተገኝተዋል። የአድዋ ድል ሕያውነት አስተጋብተዋል። “የድሉን መልካም እሴቶች ለወቅታዊ የሰላምና መረጋጋት ፍላጎታችን መጠቀም ይገባል” ብለዋል።

ሁለቱንም ክብረ በዓላት በቦታው ተገኝቼ እንደታዘብኩት የአከባበር ሂደቱ መሻሻል የታየበት ይመስላል። ለአብነትም ባሳለፍነው ዓመት የአድዋን ድል እንዲገኝ በመሪነት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት የዳግማዊ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱን ስም ማውሳት ነውር ይመስል ነበር። በወቅቱ የአውሮፓና የአሜሪካ ጋዜጦች ሳይቀር ያወደሳቸው፣ ጣሊያኖች በሮም አደባባይ “አበጀህ ምኒሊክ! አበጀሽ ጣይቱ!” እያሉ ሰልፍ የወጡላቸው የዳግማዊ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ስምም በንግግር አድራጊዎችና ድራማዊ ተውኔቶች ተነስተዋል። (በርግጥ ከባለፈው አመት አኳያ አልኩኝ እንጂ በንግግር አድራጊዎች ንጉሱና ንግስቲቱ የሚለው ሚዛን ይደፋል፤ በበዓሉ ዋዜማ በተከፈተው የፎቶ ዓውደ ርዕይም የበርካታ አርበኞች ፎቶ ለዕይታ ቢቀርብም የንጉሠ ነገሥቱና የእቴጌጣይቱ ምስል አልነበረም)።

የክልሎች መገናኛ ብዙሃንም በአንድ ታሪክ ላይ የተለያዩ ይዘቶችን ከማስተጋባት ባለፈ  ለታሪካዊ ለድሉ ተገቢውን ሽፋን ያልሰጡ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት እንደነበሩ ሲወራ እንደነበር አይዘነጋም። በዚህ ዓመት አከባበሩ ግን በርካታ መገናኛ ብዙሃን በስፍራው ተገኝተው ሽፋን ሰጥተዋል። ለዝክረ አድዋ መነሳሳት የፈጠረው ጉዞ አድዋም በባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ በአደባባይ  ተመስግኗል። በዘንድሮው የአምስተኛው ዙር የአድዋ ተጓዦች (አንዲት ታሪካዊ ውሻን ጨምሮ) በስፍራው ተገኝተው “ኢትዮጵያዊነት ይለምልም” ብለዋል። እና ምናልባት በጋራ ታሪካችን ላይ እየተግባባን ይሆን ያሰኛል!

(በነገራችን ላይ ለአድዋ ድል በዓል መታሰብ በአዲስ ንቅናቄ የፈጠሩት የ’ጉዞ አድዋ’ ዘንድሮ ለ5ኛ ጊዜ ሲካሄድ አንድ አስገራሚ ክስተትም ተመዝግቧል። ተጓዦቹ የ45 ቀናት በእግር ጉዟቸውን ከአዲስ አበባ ጀመሩ። ጉዞው ከአድዋ ታሪክ ጋር ቁርኝት ያላቸውን ሰፍራዎች በመጎብኘት ዳግማዊ ምኒልክና የፊታውራሪ ገበየሁ ገቦ የትውልድ ስፍራ(አንጎለላ) ደረሱ። ታሪካዊቷ ውሻም በፈቃዷ ወጣቶችን ተከትላ አድዋ ተራሮችን ጎበኘች። የበዓሉ ዕለትም ተጓዦችን ተከትላ ስትቦርቅ ተስተዋለች። አድዋንም ተሳልማ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰች። ‘እንኳን ሰው ውሻም…’ ብለን እንተርት እንዴ?) 

ሌላው የዘንድሮ መታሰቢያ ክብረ በዓል የድሉ ቋሚ መታሰቢያነት በአድዋ የሚገነቡ ሶስት ፕሮጀክቶች እንቅስቃሴ ላይ እያሉ መከበሩ ነው። የመጀመሪያው ባሳለፍነው ዓመት በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ላይ የነበረው የአድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል፤ ለፕሮጀክቱ በመንግስት 200 ሚሊዮን ብር መመደቡን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ማስታወቃቸው አይዘነጋም። የዲዛይን ስራውና ሌሎች ተግባራት መጠናቀቃቸው ተነግሯል።

ሌላው ደግሞ  ‘የአድዋ ድል መታሰቢያ ዓለም አቀፍ ሙዚዬም’ ግንባታ ፕሮጀክት ነው። የመሰረት ደንጋይ ከመቀመጥ አልፎ የመሬት ክለላ ስራዎች ተከናውነዋል። የዲዛይን ስራው በኢትዮጵያ አርክቴክቸሮች ማኅበር እየተሰራ ነው። ፕሮፖዛሉ በመሰራት ላይ ሲሆን፤ ቀጣይ ገንዘብ ማሰባሰብ ስራ እንደሚከናወን ተገልጿል። ይህ ሙዚዬም የፋሽስት ጣሊያን አሰብ መግባት ጀምሮ ከቅደመ አድዋ የነበሩ ጦርነቶችና ታሪካዊ ሁነቶችን የሚይዝ ተቋም እንደሚሆን ተገልጿል። ፕሮጀክቱን በዋናነት የሚያስተባብረው የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚን ወክለው በስፍራው የተገኙት ፕሮፌሰር ባሕሩ ለዚህ ድል “የቋሚ መዘክር አስፈላጊነቱ ጥርጥር የለውም” ይላሉ።

ከባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ለወራት መሰራቱን አደረጃጀቱና ይዘቱን በተመለከተ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ ተወስዶ “የአድዋን ታሪካዊ ግዝፈት በሚመጥን ሁኔታ እንዲገነባ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው” ብለዋል። ውጫዊና ውስጣዊ ገጽታዎች የሚኖሩት ይህ ቤተ መዘክር ‘ምንድብድብ’ በተሰኘው የእጅ በጅ ውጊያ በተካሄደበት ስፍራ ይገነባል። (ውስጣዊ ስዕላዊና ቁሳቁሶችን ሲይዝ ውጫዊ ገጽታው የፍልሚያ ቦታዎችን የሚይዝ ነው)

ሶስተኛው ደግሞ በክልሉ መንግስት መሪነት ‘የአድዋ ተራሮችና የአድዋ ድል ቱሪዝም ፕሮጀክት’ በይፋ መመረቁ ነው። ወደ 258 ሚሊዮን ወጭ የተገመተለት ይህ ፕሮክት በውስጡ አስር የተለያዩ ተግባራትን አካቷል። ለምሳሌ በአድዋ ከተማ ጣሊያኖች በቆንስላነት ሲጠቀሙበት የነበረውን ሕንጻ ቤተ መዘክር ይደረጋል፣ የባሻ አውዓሎም ሃረጎት ሐውልት ይገነባል፣ የራስ አሉላ አባነጋ መቃብር ሐውልት ይታደሳል፤ የብዝሐ ሕይወት ፓርክ ይከለላል፣ በተራራ ላይ ተንሳፋፊ ጋሪዎች፣ ባሎኖች፣ የቱሪስት ማረፊያዎች፣ የእግርና ፈረስ ጉብኝት አገልግሎቶች፣ የመካነ መቃብር ስፍራዎች ልማት ጥቂቶቹ ናቸው። ከሁለት ወራት በፊት የተጀመረው የዚህ ፕሮጀክት እንቅስቃሴም እስካሁን በርካታ መካነ መቃብሮች ተለይተው ታጥረዋል። (ቀደም ሲል ነጫጭ ቀለማት ያልኳቸው ካቦች ከጠላትም ከወገንም መቃብሮች ናቸው)።  ከነዚህም መካከል

“አድዋ ስላሴን ጠላት አረከሰው

ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው…”

የተባለለት የአድዋው ጀግና የፊታውራሪ ገበየሁ ገቦ(ጎራው ገበየሁ) የተሰዋበት ስፍራ ላይ ጊዜያዊ መታሰቢያ ሐውልት ይገኛል። በጠላት ወገን ደግሞ የጀኔራል ዳቦር ሜዳ ሐውልት ለመገንባት መቃብሩ በጊዜያዊነት ታጥሯል። የአድዋን ተራሮች የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በማልማትና ብዝሃ ሕይወቱን በመጠበቅ ታሪካዊ ሥፍራውን በዓለም አቀፉ የሳይንስ፣ የትምህርትና የባህል ድርጅት (ዩኔሰኮ) ዓለም አቀፍ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ ማቀዱን የተለያዩ የክልሉ የስራ ኃላፊዎች ገልጸዋል።

የሆነው ሆኖ በሚገነቡ ሶስት ፕሮጀክቶች (በተለይ ቤተ መዘክሩ ዓለም አቀፋዊ ነውና) በግንባታና በሚይዛቸው ነገሮች ዙሪያ የተለያዩ ወገኖችን አስተያየት ማስተናገዱ አልቀረም።

የመጀመሪያዊ የግንባታዎች ‘ኢትዮጵያዊነት’ ወይም አገራዊ ባህል አንጸባራቂነታቸው ነው። የኢትዮጵያ ፊልም ሰሪዎች ማህበርን በመወከል በስፍራው የተገኘው አርቲስት ደሳለኝ ስዩም የቤተ መዘክሩ አርክቴክቸራል ዲዛይን ሊታሰብበት ይገባል ባይ ነው። ምንም እንኳን ቅኝ ባንገዛም ኪነ ሕንጻው የውጭ ባህል ካንጸባረቀ ሌላ ‘የባህል ቅኝ ግዛት’ በመሆኑ ግንባታው አገራዊ ለዛ ሊላበስ እንደሚገባ ነው ያብራራው። የታሪኩ ባለቤቶች ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነውና ሁሉንም ህዝቦች ተሳትፎ፣ ባህልና ማንነት ወካይ መሆን እንዳለበትም እንዲሁ። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ከአክሱም እስከ ጎንደር ዘመነ መንግስት የኪነ ሕንጻ ጥበባት የተገለጠባቸው ድንቅ ቅርሶች ባለቤት አገር ናት ይላል።

በሌላ በኩል የአድዋ ተራሮች ሲለሙ፣ ቤተ መዘከር ሲገነባ የተወሰኑ የጦር ተዋናዮች መታሰቢያ እንደሚኖራቸው ቢገለጽም ‘የእነ እገሌስ’ የሚሉም አልጠፉ። ለአብነትም ደራሲት የምወድሽ በቀለ ተከታዩን ትላለች። “እቴጌ ጣይቱ ልጅ የላትም፤ ግን ትልቅ ስራ የሰራች ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ጸሀይ ናት። ለእሷስ ከሚሰራው ነገር ምስሏ ያለበት መሰራት የለበትም?”።

ዓለም አቀፍ ሙዚዬሙ ከአጼ ካሌብ የሰላም ማስከበር ዘመቻ ጀምሮ እስከ ባድመ ጦርነት ያለውን የጦርነት ታሪካችንን የሸከፈ የጦር ሙዚዬም መሆን አለበት የሚል ሃሳብ የሚያነሱም አሉ።

ለአድዋ ድል መንስኤ የሆነው የውጫሌ ውል የተፈረመበት ይሥማ ንጉስ፣ የእቴጌ ጣይቱ ብልሀትና የጦር ስትራቴጂ የታየበት እንዳየሱስ፣ ከአድዋ ጦርነት ቀደም ብሎ ፊታውራሪ ገበየሁ ታላቅ ጀብዱ የሰሩበት የአምባላጌ ጦር ሜዳና መሰል ታሪካዊ ሥፍራዎች ከአድዋ ጋር ተሳሰረው መልማት እንዳለባቸው ያነሱም አልጠፉ። በዚህ ረገድ ፕሮፌሰር ባህሩ “ በእንዳየሱስ ጣሊያኖች የሰሩትን ያህል ኢትዮጵያን አልሰሩም። ጣሊያን ለራሳቸው መታሰቢያ ወደኋላ አይሉም። እኛ ግን በገዛ አገራችን አልሰራንም። የውጫሌ ውል ጣጠኛ ውል ቢሆንም ቢያንስ ታሪካችን ስለሆነ ልንዘክረው ይገባል” ነው ያሉት።

ዞሮ ዞሮ ሁሉንም ፍላጎት ማሳካት ባይቻልም ቢያንስ እንደመንደርደሪያ ጀግኖቻችንን ከዘከርን፣ ታሪካችንን ካወሳን፣ ወደፊትም ተግባቦታችን ተጠናክሮ፣ ኢትዮጵያዊነት ለምልሞ ብሩህ ዘመን ይመጣ ይሆናል።

ምናልባት እነዚህና መሰል ተግባራት ሲከናወኑ ቋሚ መዘከር በማቆም ከታሪክ ተወቃሽነት ያድናል። ሉላዊ ድላችንን መዘከሩ በታሪካችን መኩራት ነው! ሰማዕታትን ማክበር ነው! የአብሮነት እሴቶችን መንገር ነው!!

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን