አርዕስተ ዜና

የዩኒቨርሲቲዎችና ኢንዳስትሪዎች ትስስር ለህዳሴው ጉዞ ስኬታማነት

12 Feb 2017
3519 times

ሃብታሙ ገዜ /ኢዜአ/

የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ከኢንዳስትሪዎች ጋር ተቀናጅተው በመስራት የሀገሪቱን የህዳሴ ጉዞ ለማሳካት እንደሚሰሩ ተናገሩ።በምርምር የተገኙ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጥቅም ላይ መዋል እንዳለባቸውም ተጠቁሟል።

በድሬዳዋና በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ለሁለት ተከታታይ ቀናት የተካሄደው አራተኛው የዩኒቨርሲቲና ኢንዳስትሪ ትስስር አውደ ጥናት ተጠናቋል።

በአውደ ጥናቱ የተሳተፉት የ34ቱ ዩኒቨርሲቲዎችና የኢንዱስትሪ ተወካዮች የሁለቱን ትስስር በሚያጸኑ ጉዳይዎችና አቅጣጫዎች ላይ የጋራ መግባባት ፈጥረዋል።

በተለይ ሁለቱን ዘርፎች ይበልጥ አቀራርቦ የተሻለና ተወዳዳሪ የቴክኖሎጂ ምርቶችንና አገልግሎቶችን በማምረትና በመስጠት ሀገሪቱ የተያያዘችውን እድገትና ልማት ዘላቂ ለማድረግ በሚችሉባቸው ጉዳይዎች ላይ መግባባት ተደርሷል።

ዩኒቨርሲቲዎች በኢንዳስትሪው ዘርፍ የሚታየውን የሰው ሃይል እጥረት በመፍታት፣ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ዘላቂ ምርቶች እንዲያመርቱ ለማድረግ ከኢንዳስትሪዎች ጋር ዕለት ተዕለት ተቀናጅተው እንደሚሰሩ የየዩኒቨርሲቲ ተወካዮች ተናግረዋል።

ኢንዳስትሪዎችም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተቀራርበውና ተቀናጅተው በመስራት ረገድ ያሉባቸውን ክፍተቶችና የተሳሳቱ አመለካከቶች በመፍታት በቀጣይ ለምርታማነታቸውና ለአገልግሎታቸው ጥራት በምርምር፣ በሰው ሃይል ግንባታና በቴክኖሎጂ ለመታገዝ እንደሚተጉ የዘርፉ ተወካዮች ገልጸዋል።

በአራተኛው አገር አቀፍ ውይይት ላይ የዘንድሮ የቴክኖሎጂ ተመራቂ ተማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን የ5ኛ ዓመት የመካኒካል ኢንጅነሪንግ ተማሪ ገዲዮን ግርማ አንዱ ነው። ተማሪ ገዲዩን ባስተላለፈው መልዕክት ዩኒቨርሲቲዎች የተጀመረውን ትስስር ከማጠናከር ጎን ለጎን በየኢንዱስትሪው ለተግባር ትምህርት የሚመደቡ ተማሪዎች የመከታተልና የመደገፍ ስራ ቢሰሩ ተማሪዎች ችግር ፈቺ ምርምሮችን ለማድረግ ይነቃቃሉ።

በአውደ ጥናቱ ላይ የቴክኖሎጂ መምህራንና ተማሪዎች የቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤቶቻቸውንም አቅርበዋል።ከቀረቡ የፈጠራ ውጤቶች መካከልም በኤሌትሪክ ሀይል የሚሰራ የአነስተኛ መኪና ዲዛይን፣ የጸሀይ ብርሃንን ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል በመለወጥ ሞባይል፣ ላብቶፕና መሰል መገልገያዎችን በቀላሉ ኃይልን መሙላት የሚያስችሉ መጠቀሚያዎች፣ የአበሻ አረቄ በቀላሉ ማምረት የሚያስችሉ መሳሪያዎች፣ ከወዳደቁ ቅጠላ ቅጠሎችና ተረፈ ምርቶች የጡብ ከሰል በማምረት የተፈጥሮ ሀብትን ማዳን የሚያስችሉ የፈጠራ ስራዎች ይጠቀሳሉ።

ተማሪ አባስ ሲራጅ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የ5ኛ ዓመት የኬሚካል ኢንጅነሪንግ ተማሪ ሲሆን ጥቅም ላይ የዋሉ የናፍጣና የዘይት ተረፈ ምርቶች መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል የባዮ ጋዝ ማምረቻ በምርምር ማግኘቱን ተናግሯል፡፡ በአውደ ጥናቱ ላይ የቀረቡ የፈጠራ ውጤቶች ጥቅም ላይ ውለው አገርና ህዝቡን እንዲጠቅሙ ዩኒቨርሲቲዎችና ኢንዱስትሪዎች በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብሏል።

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶክተር ደሳለኝ ወጋሶ በበኩላቸው አውደ ጥናቱ የሁለቱን ዘርፎች ትስስር በማጠናከር በሰው ሃይል ልማትና በኢንዳስትሪ ልማት የተሻሉ ስራዎችን ለመስራት መደላደል የተፈጠረበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተሰሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ስራ ላይ ለማዋል ዩኒቨርሲቲዎች ኢንዲስትሪዎችና የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸውና ቅንጅቱን ወደ ተግባር ለማሸጋገር ድሬዳዋ የተካሄደው 4ኛው አውደ ጥናቱ አቅጣጫ አስቀምጧል ብለዋል።

በአውደ ጥናቱ የተሳተፉት የኤም ኤም ሜታል ክራፍት ድርጅት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ፅጋቡ ደምበሳይ አውደ ጥናቱ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተሳስሮ መስራት የተሻለ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል መሰረታዊ ግንዛቤ የተጨበጠበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"በቀጣይ ከዩኒቨርሲቲዎች የሚመጡ ተማሪዎችን በአግባቡ በመቀበል በምርምር የተደገፈ ስራ እንሰራለን" ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲ ከአገሪቱ ቴክኖሎጂ ልማት ፖሊሲ አኳያ የተጣጣመ ስራ ይበልጥ መሰራት እንዳለባቸው የተናገሩት ደግሞ የኢፌዴሪ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል መሪ ተመራማሪ ዶክተር አማረ ማተቡ ናቸው።

"ኢንዳስትሪዎች አዳዲስ ቴክኖሊጂዎችን ለመቀበል በራቸውን ዝግ በመሆኑ እዚህ ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል" ብለዋል።

የአርሲ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ሽመልስ ረጋሳ በበኩላቸው አውደ ጥናቱ የሁለቱን ትስስር በማጠናከር በሀገሪቱ ህዳሴ ጉዞ ላይ ያለባቸውን ታሪካዊ ኃላፊነት በጋራ ለመወጣት ምቹ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች የአርሶ አደሩን መሰረታዊ ችግር በሚፈቱና የግብርናውን ስራ ወደ መካናይዝ አስተራረስ የሚያሳድጉ ፈጠራዎች ላይ አትኩረው በመስራት  ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ጉዞ ማፋጠን ይገባል ብለዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጨመዳ ፊኒንሳ የሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድና የህዳሴውን ጉዞ ለማሳካት ዩኒቨርሲቲዎችና ኢንዳስትሪዎች ተቀራርበውና ተቀናጅተው ለመስራት የሚያደርጉት ጅምር ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስታውቀዋል።

እንደ ፕሮፌሰር ጨመዳ ገለጻ የተሰሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች  ጥቅም ላይ እንዲውሉ የዩኒቨርሲቲዎችን የፈጠራ ስራ ኢንዳስትሪዎች እንዲያውቋቸው የማድረግ ስራ ተጀምሯል። ኢንዱስትሪዎችም ግኝቶቹን አባዝተው ለህብረተሰቡ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ የምርምር ስራዎች ለሚሰሩ ተማሪዎች በገንዘብና በቁሳቁስ ከመደገፍ በዘለለ ግኝቶቹን ህብረተሰቡና ኢንዳስትሪዎች እንዲያውቋቸው አውደ ርዕይ በማዘጋጀት ግንዛቤ እየፈጠረ ነው።

በአጠቃላይ የሁለቱ ዘርፎች ተቀራርቦ የመስራት ጅምር ነገ እየተጠናከረ ሲመጣ በእርግጥም ሀገሪቱን ወደ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍም ሆነ የምጣኔ ሐብት መሰረቱ በኢንዲስትሪ ትከሻ ላይ እንዲያርፍ በማድረግ ረገድ ዓይነተኛ ድርሻ ይኖረዋል።

የዩኒቨርሲቲ- ኢንዳስትሪ ትስስር አውደ ጥናቱ በመቀሌ፣ ሃዋሳ፣ ባህርዳርና ዘንድሮ በድሬዳዋ የተካሄደ ሲሆን አምስተኛው በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት በመጪው ዓመት ይካሄዳል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን