አርዕስተ ዜና

የአፍሪካ ትስስር ጅማሮ

10 Feb 2017
3389 times

ከሰለሞን ተሰራ /ኢዜአ/

ከጅቡቲ መዲና የተነሳው ባቡር በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያሉትን ታላላቅ ሰዎች አትኩሮት መሳቡ የተነገረው ባለፈው ወር አካባቢ ነበር፡፡በጅቡቲ የባህል ድምፃውያን የታጀበውና የአፍሪካና የአውሮፓ ዲፕሎማቶች የተካፈሉበት የምረቃ ስነስርአት ደማቅ እንደነበረ የዘገበው ቻናል አይ አር ኦንላይን ድረ ገፅ ነው፡፡

 “ለአገራችን ህዝብና መንግስት ኩራት ሲሆን ታሪካዊነቱ ደግሞ የማያጠያይቅ ነው“ በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለማርያም ደሳለኝ በወቅቱ መናገራቸውን አስታውሷል፡፡በአፍሪካ በኤሌክትሪክ ሐይል የሚሰራ ባቡር የመጀመሪያ  ጉዞውን የሚያደርገው ወደ አዲስ አበባ ነው፡፡“ ይህ መስመር የሁለቱን አገራት የማህበራዊና የኢኮኖሚ ነባራዊ ሁኔታ የሚለውጥ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በዚህ እለት ዋነኛዋ ተዋናይ ሆና የቀረበችው ደግሞ ቻይና ናት፡፡ቻይና የባቡሩን አሰራር በመዘርጋት፣ባቡሮቹን በማቅረብ እና ባለፉት ስድስት አመታት በሺ የሚቆጠሩ ኢንጅነሮችን በማስመጣት የመስመሩን ግንባታ እውን አድርጋለች፡፡ አራት ቢሊዮን የሚጠጋውን ወጪ በአብዛኛው የሸፈነችው ቻይና ናት፡፡

በአለም ውዱና ዘመናዊውን የባቡር መስመር በአገሯ  የገነባችው ቻይና ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎቿን ወደ ውጭ አገራት በመላክ አጋርነቷን እያስመሰከረች ነው፡፡በቻይና የተመረቱ የምድር ውስጥ ባቡሮች በቅርቡ በአሜሪካኖቹ ቦስተንና ቺካጎ እንደሚታዩ ዘገባው አስነብቧል፡፡ቤጂንግ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ፈጣን የባቡር መስመር ኢንዶኔዢያ ላይ እየገነባች ነው፡፡ከዚህ ባለፈ በቤጂንግና በለንደን መካከል የባቡር የጭነት አገልግሎት ጅማሮ እውን ሊሆን ተቃርቧል፡፡ሌላው አስደማሚ ግንባታ ደግሞ 2 ሺ 400 ማይል የሚረዝመው የፓን ኤሽያ የባቡር መስመር ትስስር ሲሆን ቻይናን፣ላኦስን፣ታይላንድንና ሲንጋፖርን ያገናኛል፡፡

እንደ አፍሪካ ያሉ የተወሰኑ አካባቢዎች ደግሞ የቻይናን ድጋፍ በላቀ ሁኔታ እያገኙ ነው፡፡አህጉሪቱ ያላት የባቡር መስመር በጣም አነስተኛ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

ከሰሐራ በታች ያሉት አገራት ተከታታይና ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገቡ ቢሆንም አሁንም የመሰረተ ልማት እጥረት አለባቸው፡፡ የአፍሪካ ልማት ባንክ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው ከአህጉሪቱ መንገዶች መካከል ግማሹ ብቻ አስፋልት የተነጠፈለት ሲሆን 600 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝቧ የኤሌክትሪክ ሐይል አቅርቦት አያገኝም፡፡

 በጆብ ሆፕኪንስ የአለም አቀፍ ጥናት አድቫንስድ ክፍል የቻይና አፍሪካ የምርምር ኢኒሼቲቭ በቻይና መንግስት እገዛ የሚንቀሳቀሱት ኩባንያዎች በአመት  50 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ በመመደብ በአህጉሪቱ አዳዲስ ወደቦችን፣የቀለበት መንገዶችንና የአውሮፕላን ማረፊያዎችን እየገነቡ መሆኑን በጥናት ተመርኩዞ አቅርቧል፡፡

ብዙዎቹ ፕሮጀክቶች የቤጂንግ አዲሱ የሲልክ ሮድ ኢኒሼቲቭ አካል ሲሆኑ ቻይና 1 ትሪሊዮን ዶላር በመመደብ በማደግ ላይ ካሉ አገራት ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት ለማሳደግ የምትጠቀምበት ነው፡፡

ከዚህ ውስጥ አብዛኛው ገንዘብ ለባቡር መስመር ዝርጋታ የሚውል ሲሆን ግንባታው የአፍሪካውያንን የጉዞ እንግልት በመቀነስና ከተቀረው አለም ጋር ያላቸውን የንግድ ልውውጥ ለማሳደግ እንደሚያግዛቸው ታምኖበታል፡፡

በቻይና መንግስት የገንዘብና የግንባታ ባለሙያዎች እገዛ ከተሰሩት ፕሮጀክቶች መካከል በኢትዮጵያ የሚገኘውና ሁለት አመት የፈጀው የቀላል ባቡር መስመር ዝርጋታ፣13 ቢሊዮን ዶላር የሚፈጀውና የኬንያዋን ዋና ከተማ ናይሮቢን ከወደብ ከተማዋ ሞምባሳ ጋር የሚያገናኘው የባቡር መስመር እንዲሁም በናይጀሪያ እየተከናወነ ያለው ዘመናዊ የባቡር መስመር ግንባታ ይጠቀሳሉ፡፡

“ ለረጅም አመታት በአፍሪካ ያለው የመንገድ አገልግሎት እየፈራረሰና እየቀነሰ መጥቷል ነገር ግን በቻይና እገዛ ይህ እውነታ እየተቀየረ መምጣቱን ” በሬል ዌይ የባቡር መስመር ጋዜጣ የዜና ኤዲተር የሆነው አንድሪው ግራንትሀም ተናግሯል፡፡

ቻይና በአፍሪካ በቁርጠኛነት እያከናወነች ያለችው የባቡር መስመር፣የትምህርት ቤትና የስታዲየም ግንባታ ከአሜሪካ አንፃር ሲታይ ለየቅል የቆመ ነው፡፡.አሜሪካ በአፍሪካ የሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የመደገፍ ፍላጎቷ ፍፁም የወረደ መሆኑን ፀሐፊው ጠቅሷል፡፡

በባራክ ኦባማ የአመራር ዘመን በ2013 ይፋ የተደረገውና 9 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር በጀት የተያዘለት የፓወር አፍሪካ ኢኒሸቲቭ በአምስት አመታት ውስጥ 20 ሚሊዮን አፍሪካውያንን የኤሌክትሪክ ሐይል  ተጠቃሚ ለማድረግ ቢያልምም ፈቅ ሳይል ቀርቷል፡፡

ንግድን በተመለከተ ደግሞ ቻይና በ2009 አሜሪካን በመቅደም የአፍሪካ ዋነኛዋ የንግድ አጋር ሆናለች፡፡ይህ ሒሳብ በዶናልድ ትራምፕ ዘመን እንዴት ሊቀለበስ እንደሚችል የሚያሳይ ምንም ፍንጭ አለመኖሩን ዘጋቢው አስነብቧል፡፡ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቀረጥ ነጻ የንግድ እድል ተጠቃሚነት ወይም አጎዋን ጥያቄ ውስጥ ከትተውታል፡፡ከወራት በፊት ያዋቀሩት የሽግግር ቡድን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በላከው መጠይቅ በአፍሪካ ያለውን የእድገት መፍጨርጨርና የውጭ እርዳታ አጠራጣሪ አድርጎ አሳይቶበታል፡፡

ይህ ደግሞ አንዳንድ የአፍሪካ ከፍተኛ ባለስልጣኖችንና ኤክስፐርቶችን ስጋት ውስጥ ከቷቸዋል፡፡የአሜሪካ ተፅእኖ የጎላ መሆኑ የማይካድ ሲሆን የመሰረተ ልማት ፍላጎታቸውን ለማሟላት የሚውተረተሩ አገራት ስጋት ቢገባቸው አያስደንቅም፡፡

.በብሮኪንግ ኢንስቲቲዩት የአጎዋ ዳይሬክተር የሆኑት አማዱ ሳይ አሜሪካ ታማኝ ደንበኞችን ለማፍራት ያገኘችውን አጋጣሚ እያጣች ነው ብለዋል፡፡

”አዲስ ገበያ የምትፈልግ ከሆነ ቦታው አፍሪካ ነው፡፡ ነገር ግን አሜሪካ የአፍሪካን እምቅ አቅም እየተጠቀመችበት አይደለም፡፡በንፅፅር ቻይናውያን እዛ ናቸው ማንኛውንም አደጋ ለመጋፈጥ ተዘጋጅተዋል ”ሲሉ ሙያዊ ምልከታቸውን አንጸባርቀዋል፡፡

ቻይና ድህነትንና ስራ አጥነትን ለማስወገድ እየተጋች ባለችው ጅቡቲ ብቻ 14 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ በመመደብ እየተንቀሳቀሰች ነው፡፡ከያዘቻቸው ፕሮጀክቶች መካከል የሶስት ወደቦች፣የሁለት አውሮፕላን ማረፊያ  ይጠቀሳሉ፡፡ከዚህ በተጨማሪ በአገሪቱ የከሰል ሐይል ማመንጫ ለመገንባት እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች፡፡

የኢትዮጵያ 90 በመቶ የወጪ ንግድ በጅቡቲ በኩል የሚወጣ በመሆኑ የአገራቱ ትስስር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡

የጅቡቲ ወደብ ሊቀመንበር የሆኑት አቡበከር ኦማር ሀዲ ሁለቱን አገራት የሚያገናኘው አዲሱ የባቡር መስመር ከህንድ ውቅያኖስ ወደ አትላንቲክ ውቅያኖስ ለሚዘረጋውና የረጅም ጊዜ ህልም ለነበረው የአፍሪካ የጉዞ ትስስር ቀለበት መንደርደሪያ ነው ብለዋል፡፡

”ባቡሩ በአሁኑ ሰአት ጨዋታ ቀያሪ ሆኗል በማለት ቀደም ባለው ጊዜ አራት ቀን አካባቢ ይፈጅ የነበረውን የመኪና ጎዞ ወደ 12 ሰአት ማሳጠሩን ማሳያ በማድረግ ሐሳባቸውን ለዘጋቢው አካፍለውታል፡፡”

ቻይና ለአገራቸው እያደረገች ያለውን የገንዘብ ድጋፍም አድንቀዋል፡፡

”አሜሪካኖችን ብንቀርባቸውም ራዕይ የላቸውም,፡፡30 አመት ወደፊት ቀድመው ማሰብ አይችሉም፡፡ የእነሱ ራዕይ አፍሪካ አሁንም በእርስ በእርስ ጦርነትና በርሐብ ውስጥ እንዳለች አድርጎ ማሰብ ነው፡፡ ቻይናውያን ግን ራዕይ አላቸው፡፡” ማለታቸውን ዘግቧል፡፡

ሁሉም በቻይና ራዕይ ደስተኛ ላይሆን ይችላል፡፡አገራት በብድር ባህር እንዳይሰጥሙ የሚሰጉ አሉ፡፡ የጅቡቲ ብድር ከፍ ያለ ቢሆን የመክፈል አቅም እንዳላት የአገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር ኢሊስ ሙሳ ዳውላህ ተናግረዋል፡፡ ሚኒስትሩ ጅቡቲ በማስመዝገብ ላይ ያለችው 6 ነጥብ 7 በመቶ አገራዊ እድገት ብድሯን ለመክፈል ያስችላታል ማለታቸውን ዘገባው በማሳያነት አስቀምጦታል፡፡

” አደጋውን ተጋፍጠን መሰረተ ልማታችን ካላስፋፋን በድህነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቀን እንቀራለን፡፡ከጥቂት አመታት በኋላ ስትመለሱ ጅቡቲን የአህጉሪቱ የሎጀሰቲክ መናኽሪያ ሆና ታገኟታላችሁ ብለዋል፡፡ ”

 የባቡር መስመር ዝርጋታው ከግንባታው ይልቅ ጥገናው አሳሳቢ በመሆኑ ሊታሰብበት እንደሚገባ ቀደም ያሉ ማሳያዎችን በመጥቀስ የአፍሪካ ፍሪደም ሬል ዌይ መፅሐፍ ፀሐፊዋ ጄሚ ሞንሶን ትናገራለች፡፡

” አስተማማኝ የሆነ ጥገና ከሌለ ችግር መፈጠሩ አይቀርም፡፡ይህ ደግሞ በአህጉሪቱ ኢኮኖሚና መደበኛ ነዋሪ ላይ ከባድ ተፅእኖ ያሳርፋል ብላለች፡፡”

ለአሁኑ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት በኢትዮ ጅቡቲ ዘመናዊ  የባቡር መስመር ግንባታ መጠናቀቅ ደስተኛ ሆነዋል፡፡ቻይናውያን የቴክኒኩንና የኢንጅነሪንግ ስራውን ሲከዉኑት ኢትዮጵያውያንና ጅቡቲያውያን ሰራተኞች ደግሞ በጉልበትና በቀላል የቴክኒክ ስራዎች ላይ በመሳተፍ አዲስ እውቀት ለመቅሰም በቅተዋል፡፡

አጠቃላይ አሰራሩ ለአምስት አመታት በቻይናውያን እጅ ውስጥ ከቆየ በኋላ በቻይና በሰለጠኑትና በመሰልጠን ላይ ለሚገኙት ለአገራቱ ዜጎች ይተላለፋል፡፡

ለጅቡቲ መንግስት የሚሰራው የቴክኖለጂ ስፔሻሊስት ዳሀ አህመድ ኦስማን አዲሱ የባቡር መስመር ከጅቡቲና ከኢትዮጵያ ባለፈ አህጉሪቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግራት እምነት እንዳለው ለፀሐፊው ነግሮታል፡፡በዚህ ስራቸው ቻይናውያንን ማመስገን አለብን፡፡ ምክንያቱም ገንዘባቸውንና እውቀታቸውን ከእኛ ጋር ተካፍለዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ልናመሰግናቸው የሚገባው በእኛ ላይ እምነት በማሳደራቸው  ነው ማለቱን ጠቅሶ ድረ ገፁ ዘገባውን አጠናቋል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን