አርዕስተ ዜና

የጫካ ውሎ

10 Feb 2017
2665 times

በአማኑኤል ካሣ/ኢዜአ/

እውነት እላችሃለሁ በዚህ ሰአት በአይኔ የማየውን ነገር ሁሉም ሰው ተራ በተራ ቢያየው ደስታየን አልችለውም ። ሆኖም በዚህ ቅፅበት በስፍራው የምንገኘው እኔና ሁለት አስጎብኝዎቼ ብቻ ነን።ቢሆንም ግን የማየውን ነገር ልነግራችሁ ወደድኩ።

ከቆምኩበት 1ሺህ 8 መቶ ሜትር ከፍታ ከባህር ጠለል በላይ ወደታች አስደናቂ መልከአ ምድር አቀማመጥ ያለው ቦታ ይታየኛል። አብዛኛው ገደላማ ቦታዎቹ በእጣን ዛፍና በሳቫና የሳር ምድር የተሸፈነ ሲሆን ሜዳማ ቦታው ደግሞ በግራር ዝርያ  አሸብርቋል።

አከባቢው ሙቀታማ ቦታ ሲሆን የአየር ሁኔታው ከ28 እስከ 40 ዲግሪ ሴንትግሬድ ይደርሳል ። በምስል ማቅረቢያ/binocular/ተጠቅሜ አከባቢውን መቃኘት ስጀምር ለአይን የሚማርኩ የዱር እንስሳት በፓርኩ ውስጥ ሲቦርቁ፣ሲመገቡና ሌሎች እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ ይታዩኛል።

ከሁሉም በፊት ቀድመው አይኔ ውስጥ የገቡት በየብስ ላይ ከሚኖሩት እንስሳት ተወዳዳሪ የሌላቸው ትላልቅ የአፍሪካ ዝሆኖች ናቸው።ዝሆኖቹ በቡድን ሲሄዱ ከትልቅነታቸው የተነሳ ቢያስፈሩኝም በሩቅ ሆኜ በምስል ማቅረቢያ እያየኋቸው መሆኔን ሳስብ ግን ተፅናናሁ ። ከፍርሃቴ ይልቅ ደስታየ ጎላ።ምን ያህል ለጫካው ግርማ ሞገስ እንደሰጡት ልነግራችሁ አልችልም።

የምስል ማቅረቢያ መሳሪያው አቅጣጫ እየቀያየርኩኝ በርካታ የዱስ እንስሳት ማየት ቻልኩኝ ።ከቂጣቸው አካባቢ ሾጠጥ ብለው ወደ ትከሻቸው አካባቢ ደንደን ያሉ ጅቦች፣ቅጠላቅጠል የሚለቅሙ የሜዳ ፍየሎች፣የረዠምና ጠመዝማዛ ቀንድ ባለቤት የሆኑ አጋዘኖች፣ለመልካም መአዛ የተፈጠሩ ጥርኞች፣ልዩ ልዩ ዝርያ ያለቸው ቀበሮዎች፣በርካታ ዝርያ ያላቸው ወፎችና ሌሎች በርካታ እንስሳቶች በምስል መመልከቻው  ተመለከትኩኝ።

ከአጠገቤ የሚገኘው የፓርኩ ፅሕፈት ቤት ተወካይ አቶ አለም ወላይ ቁልቁል ወደ ተከዜ ወንዝ እንድመለከት ጠቆመኝ።በወንዙ ዳርቻ በርካታ ወፎች ይታዩኛል።እነዚህ ወፎች ብዙ አገር ተሻግረው ከአውሮፓ አገራት ለሶስት ወር ቆይታ ወደ ፓርኩ እንደሚመጡ ነገረኝ።በጣም ስለገረመኝ ለምን እንደዛ እንደሚሆኑ እስኪነግረኝ በአይኔ በሙሉ ተመስጦ ጠበቅኩት።

በአውሮፓ ከፍተኛ ቅዝቃዜ በሚፈጠርበት ወቅት ወፎቹ ለሶስት ወራት ወደ ፓርኩ መጥተው እንደሚያሳልፉና በረዶው ቀልጦ ቅዝቃዜው ሲቀንስ ደግሞ ድንበር ተሻግረው ወደ አውሮፓ እንደሚመለሱ ነገረኝ።

ይህ የምነግራችሁ ስፍራ በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ይገኛል።በሰሜን ተከዜ ወንዝን ተከትሎ ከጎረቤት አገር ኤርትራ፣በስተምስራቅ ታሕታይ አድያቦ(3 ቀበሌዎች)፣በስተደቡብ ወልቃይትና ቃፍታ ሑመራ ወረዳ(7 ቀበሌዎች)፣በስተ ምዕራብ ደግሞ ቃፍታ ሑመራ ወረዳን ያዋስኑታል።

የቃፍታ-ሑመራ ብሔራዊ ፓርክ ለፓርክነት የታጨው በ1960 ዓ/ም በራስ መንገሻ ስዩም እንደሆነ ታሪክ ይነግረናል።ሆኖም በ3ኛና 4ኛው ክፍለዘመን ማለትም በአክሱም ስልጣኔ ዘመን ይህ ስፍራ የዝሆን ጥርስ ለንግድነት ይጠቀሙበት እንደነበርና በጊዜው በአካባቢው የዝሆን ብዛት ከ5ሺህ በላይ ይደርስ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያትታሉ።

ከ40 አመታት በፊት ይህ ፓርክ የቆዳ ስፋቱ ከ5ሺህ ስኩየር ኪሎ ሜትር በላይ የነበረ ሲሆን በአካባቢው የህዝብ ብዛት እየጨመረ በመምጣቱ ስፋቱ ወደ 2ሺህ176ነጥብ34 ስኩየር ኪሎሜትር ሊቀንስ መቻሉን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የቆዳ ስፋቱ መቀነስ ብቻ ሳይሆን በአሁን ሰአት ፓርኩ በአካባቢው በሚገኙ አርሶ አደሮች ለእርሻ ስለሚጨፈጨፍ በውስጡ የሚገኙ እንስሳትና እፅዋት አደጋ ላይ ይገኛሉ።

በፓርኩ ፅሕፈት ቤት ግቢ ውስጥ በአንዱ ጥግ ላይ ትላልቅ የዝሆን ጥርስና ረዣጅም ጠመዝማዛ የዝሆን ጥርስ ተመለከትኩኝ፤እነዚህ ጥርሶችና ቀንዶች በፓርኩ ውስጥ በህገ ወጥ አደን  የተገደሉት እንስሳቶች ቅሪት መሆኑን ተነገረኝ።በዚህ መንገድ በርካታ የዱር እንስሳት እየተገደሉ እንደሆነ ለመገመት አላዳገተኝም።

የፓርኩ ፅሕፈት ቤት ተወካይ አቶ አለም ወላይ እንደነገሩኝ ከሆነ በፓርኩ ክልል ውስጥ ከ3 ሺህ 7መቶ በላይ አርሶአደሮች የሚገኙ ሲሆን አርሶ አደሮቹ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ  በሚያስፋፉት የግብርና ስራዎች ወደ ምድረ-በዳነት እየቀየሩት ይገኛሉ።

አዲ ጎሹ፣ ማይ ወይኒና ማይ ቀይሕ በተባሉ በፓርኩ ውስጥ በሚገኙ ቀበሌዎች የሚኖሩ በርካታ አርሶ አደሮች የእርሻ ማሳ ለማስፋፋት ደኑ በአሳዛኝ ሁኔታ እየጨፈጨፉት ይገኛሉ።

ይህንን ተከትሎም በህገ-ወጥ መንገድ በፓርኩ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ የቤት እንስሳት እርባታና የማደለብ ስራዎችም እየተካሄደበት ነው ።

ፓርኩ በወርቅ ሃብት የታደለ በመሆኑም ይህንን ተከትሎ በርካታ የባህላዊ ወርቅ ቆፋሪዎች በህገወጥ መንገድ እየቆፈሩ ወርቅ በማምረት ላይ እንደሚገኙ በአይኔ ማረጋገጥ ችያለሁ።

በዚህም ምክንያት የፓርኩ የዱር እንስሳት በተቆፈረው ጉድጓድ ውስጥ እየገቡ የሞት አደጋ እየደረሰባቸው እንደሆነ አቶ አለም ይናገራሉ።

ከዚህም ባሻገር ወርቅ ፈላጊዎች ለተለያየ ምክንያት በሚያቃጥሉት እሳት ከደኑ ጋር እየተያያዘ ተደጋጋሚ የእሳት ቃጠሎ እየደረሰበት ይገኛል።

‘’ፅሕፈት ቤቱ ችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንዲፈለግለት ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም ፓርኩ ለመንከባከብ የክልሉ መንግስት ያሳየው ቁርጠኝነት ግን እምብዛም ነው ’’ ይላሉ ሃላፊው።

መንግስት በቁርጠኝነት ገብቶ አርሶ አደሩ በማሳመንና ቅያሪ መሬት ሰጥቶ ከፓርኩ ክልል እንዲለቁ ቢያደርግ ከዚህ በላይ አደጋ ሳይደርስበት ፓርኩን መታደግ እንደሚቻል ነው ያረጋገጡልኝ።

በትግራይ ምዕራባዊ ዞን የቃፍታ ሑመራ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አዳነ ዓባይ የፓርኩን ደህንነት ለመጠበቅ  በአብዛኞቹ ቀበሌዎች ተለዋጭ የእርሻ መሬት መስጠት መጀመሩን ይናገራሉ።

ግን በአንዳንድ ቀበሌዎች ፓርኩን ለቀው ለሚወጡ አርሶ አደሮች የሚሰጥ ምትክ የእርሻ መሬት በሚፈለገው መጠንና ጊዜ አለመገኘቱ ፓርኩን ከሰውና ከቤት እንስሳት ንክኪ ነጻ ለማድረግ  እየተደረገ ያለውን ጥረት አስቸጋሪ አድርጎታል ባይ ናቸው ።

ፓርኩን ለቅቄ ከመሄዴ በፊት ተከዜ ወንዝ አካባቢ ወደሚለሙ የመስኖ እርሻ ስፍራዎች ጎራ አልኩኝ።በስፍራው አቶ ሐጎስ ገብረፃዲቅ የተባሉ አርሶ አደር አትክልታቸውን በመንከባከብ ላይ ነበሩ።

አቶ ሐጎስ የአካባቢው ተፈጥሮ ሃብት ለመስኖ ስራ አመቺ ቢሆንም በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ የዱር  እንስሳት ያፈሩትን ምርት እየባከነባቸው እንደሚገኝ ነገሩኝ።በተለይ በስፍራው የሚገኙት ትላልቅ ዝሆኖች ወደ መስኖ ቦታው እየገቡ አትክልቶቻቸውን እየረጋገጡ እንደሚያበላሹባቸው በምሬት ይገልፃሉ ።

መንግስት ቅያሪ መሬት ቢሰጣቸው አይናቸውን ሳያሹ ከቦታው ለመነሳት ፍቃደኛ እንደሚሆኑ መዳፌን በመምታት በመሀላ አረጋገጡልኝ።

እኔም የአከባቢው የተፈጥሮ ፀጋ እያደነቅኩኝና ከዚህ በላይ ትኩረት ቢሰጠው ለክልሉም ሆነ ለአገሪቱ ምን ያህል የቱሪስት መስህብና ለተለያዩ ዘርፎች የጥናትና ምርምር ማዕከል ሊሆን እንደሚችል እያሰብኩኝ ጉብኝቴን ጨርሼ በመጣሁበት ተመለስኩኝ።  

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን