አርዕስተ ዜና

የጥጥ ልማትና ተግዳሮት- በአፋር….‼

07 Feb 2017
4013 times

ወንድማገኝ ሲሳይ (ኢዜአ)

የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በአፋር ክልል ለሚገኙ ጥጥ አልሚዎች ጥራትን መሰረት ያደረገና አመራረት ላይ ያተኮረ ሥልጠና ሰሞኑን በአሚባራ ከተማ ሰጥቷል።

በስልጠናው ላይ ከአሚባራ፣ገዋኔና ዱለቻ ወረዳ የተውጣጡና በጥጥ ልማት የተሰማሩ ከፊል አርብቶ አደሮችና ባለሀብቶች ተሳትፈዋል።

በኢንስቲትዩት የጥጥ ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መሰለ መኩሪያ በዚህ ወቅት እንዳስታወቁት “በሀገሪቱ ለጥጥ ልማት አመቺ ከሆነው 3 ሚሊዮን ሄክታር ሰፊ መሬት ውስጥ እስካሁን ጥቅም ላይ የዋለው ሰባት በመቶ ብቻ ነው”።

ሀገሪቱ ገና ያልተነካውን ይህን እምቅ ሀብት ታዲያ በአግባቡ ጥቅም ላይ ልታውለው ይገባል።

በአሁኑ ወቅት ከውጭ አገር በርካታ የካበተ ልምድ ያላቸው የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሀገር ውሰጥ እየገቡ መሆናቸውን ተከትሎ ከፍተኛ የግብዓት አቅርቦት ይፈለጋል።

ለጥጥ ልማት አመቺ የሆነውን ሰፊ መሬት ጥቅም ላይ በማዋል የኢንዱስትሪዎችን የጥሬ እቃ ፍላጎት ሟሟላትና ማርካት ከሀገሪቱ የሚጠበቅ ነው።

በዚህ ረገድ ኢንሲቲትዩቱ ከአምራቾች፣ከግብዓት አቅራቢዎች ፣ ከክልሎች ጋር በመሆን በጋራ ለመስራት እየተንቀሳቀሰ  መሆኑን ነው አቶ መሰለ የሚገልጹት።

ጥጥ በተፈጥሮው የሚውለው ለጨርቃ ጨርቅ ምርት ብቻ ስለሆነ ጥራቱን ጠብቆ  ሊመረት ይገባል ይላሉ።

የጥጥ ጥራትን ለማስጠበቅ በአንድ ቦታ ብቻ ተገድቦ የሚቆም ሳይሆን ከምርት አሰባሰብ አንስቶ ጨርቁ ተመርቶ እስኪወጣ ድረስ ያለው ሂደት ከፍተኛ ጥንቃቄ ይጠይቃል።

ኢንስቲትዩቱ በዚህ በኩል ያለውን የግንዛቤ ክፍተት ለመሙላት የጥጥ ጥራትን መሰረት ያደረገ ስልጠና ለአምራቾች በመስጠት የበኩሉን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

በአፋር ክልል ለሚገኙ ከፊል አርብቶ አደሮችና ልማታዊ ባለሀብቶች  የተሰጠው ስልጠና የዚሁ እንቅሰቃሴ አካል መሆኑን በመጠቆም።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ለጥጥ ጥራት መጓደል በዋናነት ከዝርያ ፣ከአየር ንብረት፣ከአመራረት፣ከምርት አሰባሰብ፣ማከማቻ ቦታና ከማጓጓዧ ጋር በጥብቅ ይቆራኛል።

በመዳመጫ ሂደት፣ከእርጥበት፣ከአስተሻሸግ፣ አያያዠና ሌሎችም ለምርት ጥራቱ መጓደል መንስኤ ናቸው ።

በአፋር ክልል የሚገኘው የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል በአገር አቀፍ ደረጃ ብሔራዊ የጥጥ ምርምርን  በማስተባበር ይታወቃል።በዚህ ረገድ ማዕከሉ ምን እየሰራ እንደሆነ ለመቃኘት ወደ ማዕከሉ ጎራ ብለን ነበር። 

አቶ ደስታ ገብሬ የማዕከሉ ዳይሬክተር ናቸው።እሳቸው እንደሚሉት ማዕከሉ ባለፉት ዓመታት በጥጥ ቴክኖሎጂ ዙሪያ ውጤታማ ተግባራትን አከናውኗል።

በአሁኑ ወቅትም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማፍለቅና ለማላመድ በተለያዩ ሥነ ምህዳር አካባቢዎች እየሰራ ነው የሚገኘው።

ቆላማና ሞቃታማ አካባቢዎች በዋናነት ከሚመረቱ ሰብሎች ውስጥ ጥጥ ዋንኛው መሆኑን ገልጸው ምርምሩ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ ከነበረባቸው አካባቢዎች ውሰጥ አፋር፣ ሶማሌ፣ጋምቤላ፣ መተማ፣ሁመራ እንዲሁም በደቡብ ክልል ወይጦና አርባ ምንጭን ጠቅሰዋል።

በእነዚህ አካባቢዎች በተካሄደው ሰፊ የምርምር ስራም 32 የሚሆኑ የጥጥ ዝርያዎች ከነሙሉ ፓኬጃቸው ወጥተዋል።ይሁን እንጂ አስካሁን ድረስ የተወሰኑት ዝርያዎች ብቻ ናቸው በምርት ላይ የሚገኙት።

ከጥጥ ዝርያዎቹ መካከል “ዴልታ-ባይ” የተባለው ከ20 ዓመት በፊት የተለቀቀ ሲሆን እስካሁን በስፋት እየተመረተ ነው።

የተለቀቁት ዝርያዎች በዋናነት ወደ ተጠቃሚው ያልደረሱበት ምክንያት ሲያስረዱም የጥጥ ዘር አባዝቶ ለተጠቃሚዎች የሚያደርስ አካል አለመኖር ዋነኛው ነው እንደ -ዳይሬክተሩ።

ማዕከሉ በራሱ ይዞታ የጥጥ ዝርያ በማባዛት የዘር እጥረቱን በተወሰነ ደረጃ ለማቃለል ጥረት እያደረገ ሲሆን በዚህም የአካባቢውን  አልሚዎችን እየደገፈና ተጠቃሚ እያደረገ ነው።

ከጋምቤላ፣ ደቡብ፣አማራና ትግራይ ለሚመጡና በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶችም የዘር አቅርቦት ድጋፍ ያደርጋል-ማዕከሉ።

ይህም የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል ብቸኛ የጥጥ ዘር አቅራቢና የምርምር ማዕከል ሆኖ እየሰራ ያለ ተቋም መሆኑን ያሳያል ነው ያሉት።

እንደ ዳይሬክተሩ  ማብራሪያ የጥጥ ዝርያን በባለቤትነት የሚያባዛ አካል በሀገሪቱ አለመኖር ልማቱን ለማስፋፋትና ቴክኖሎጂን ለማስረጽ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጋሬጣ ሆኗል።

ጥጥ በከፍተኛ ደረጃ በተለያዩ ተባዮች ይጠቃል የሚሉት ዳይሬክተሩ ተባዮቹን መከላከል የሚያስችሉ ኬሚካሎችን በተግባር በመፍተሽ ውጤታማነታቸው እየተረጋገጠ ጥቅም ላይ እንዲውሉም ጥረት እያደረገ ነው።

በተለይ በማዕከሉ ባለሙያዎች አማካኝነት ለአልሚዎች ተግባር ተኮር ስልጠናና የምክር አገልግሎት በመስጠት የተባይ መከላከያ ኬሚካል በአግባቡ በመጠቀምና ጥጥን በስፋት በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ከአቶ ደስታ ማብራሪያ መረዳት ተችሏል ።

በስልጠናው የተሳተፉ የአሚባራ፣ገዋኔና ዱለቻ ወረዳ ከፊል አርብቶ አደሮችና ባለሀብቶች በበኩላቸው ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ ጥጥ ብናመርትም ተገቢ ዋጋ በማጣት ተቸግረናል ይላሉ።

ለሀገር ውስጥ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ለሚያቀርቡት የጥጥ ምርት እንደ ደረጃው ለአንድ ኪሎ ግራም የተተመነው ከ32  እስከ 35 ብር ዋጋ አነስተኛና የአምራቹን ወጪና ድካም ግምት ያስገባ አይደለም ነው የሚሉት።

ይህም ለኪሳራ እየዳረጋቸው መሆኑን ነው በምሬት የተናገሩት።

ከጥጥ አልሚዎች መካከል አርብቶ አደር ኢብራሂም አሊ እንደሚሉት አንድ ሄክታር ጥጥ በመስኖ ለማልማት 25 ሺህ ብር ወጪ ያወጣሉ።ምርታቸውን ባለፈው ዓመት ለገበያ ሲያቀርቡ ግን በሄክታር ከአራት ሺህ ብር በላይ ኪሳራ እንዳጋጠማቸው አስታውቀዋል።

ከፊል አርብቶ አደር ሁሴን አህመድ ወደ ጥጥ ልማት ከገቡ ስድስት አመት ማስቆጠራቸውን ይናገራሉ።በዚህ ጊዜ ውስጥ የሚያለሙትን ሦስት ሄክታር መሬት ወደ 20 ሄክታር ለማስፋፋት ቢችሉም ለምርታቸው ሳቢና ተመጣጠኝ ዋጋ በማጣት ተቸግረዋል።

በአካባቢያቸው ለጥጥ አምራቾች የተመቻቸ ነገር እንደሌለም ይግልፃሉ።አዳዲስ የጥጥ ምርጥ ዘር አቅርቦት እንዲመቻችና የተሻለ የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸውም ይጠይቃሉ።

ዘንድሮ በ25 ሄክታር ይዞታቸው ላይ ያለሙት ጥጥ በመልካም ቁመና ላይ ስለሚገኝ 750 ኩንታል ምርት አገኛለሁ ብለው ይጠብቃሉ።

በአሚባራ ወረዳ ከሚገኙ ጥጥ አልሚ ባለሀብቶች መካከል የደሃሞ የጥጥ እርሻ ልማት ድርጅት ባለቤት አቶ አህመድ መሐመድ በሰጡት አስተያየት “የጥጥ ልማቱን በአምስት ሄክታር መሬት ላይ የጀመሩት በ1996 ዓ.ም ነው”።

በየዓመቱ የሚያለሙትን መሬት እያስፋፉ በመምጣት በ2008/09 ምርት ዘመን ብቻ በአዋሽ ወንዝ ከአንድ ሺህ 70 ሄክታር በላይ መሬት አልምተዋል።ከልማቱም 30 ሺህ ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ ነግረውኟል።

በአሁኑ ወቅት ምርት የማሰባሰቡ ተግባር ውስጥ ቢገቡም ከፍተኛ የሰው ሃይል እጥረት ስላጋጠማቸው ምርታቸው እንዳይበላሽ ሰግተዋል።

 ሰፊ መሬት ተከራይተው ጭምር የማያካሂዱት የጥጥ ልማት ለትርፍ ባያበቃኝም የወደፊቱን ተስፋ በማድረግ እየሰራሁ ነኝ ባይ ናቸው አቶ አህመድ።

የጥጥ ሰብል በከፍተኛ ሁኔታ በተባይ መጠቃቱና መደሐኒትም በወቅቱ አለመገኘቱ በምርታማነታቸው ላይ ተጽዕኖ እያሳደረባቸው ስለሆነ መንግስት መፍትሄ እንዲፈልግ ጠይቀዋል።

የራሳቸው የሆነ የጥጥ ማዳመጫ ስለሌላቸው ተከራይተው ነው የሚጠቀሙት ባለሀብቱ።ነገር ግን በወረዳው ያለው አንድ የጥጥ ማዳመጫ ብቻ ስለሆነ  ሶስትና አራት ወራት ወረፋ ለመጠበቅ ይገደዳሉ።ይህ ደግሞ በስራቸው ላይ  ጫና ፈጥሯል።

በአካባቢው የሚታየው የማዳመጫ መሳሪያ እጥረት እንዲቃለል  ለሚመለከታቸው አካላት በተደጋጋሚ ቢያሳውቁም  ምላሽ እንዳላገኙ ያወሳሉ።

ጥጥ አምርተውና ዳምጠው የሚያሰረክቡት ሀገር ውስጥ ለሚገኙ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ብቻ በመሆኑ እነሱ በወሰኑት ዋጋ ብቻ ለማስረከብ መገደዳቸው ሌላው የጥጥ አልሚዎች ተግዳሮት ነው።

ባለሀብቱ እንደሚሉት “አምና 15 ሺህ ኩንታል ጥጥ አምርተው ለገበያ በማቅረብ 17 ሚሊዮን ብር ገቢ አግኝተዋል”።  

በአፋር ክልል የአሚባራ ወረዳ የአርብቶ አደርና ግብርና  ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሃሰን ዲኒ “በጥጥ አምራቾች ዘንድ የሚስተዋሉትን የገበያ ፣የምርጥ ዘርና የተባይ መደሐኒት አቅርቦት ተግዳሮት ለማቃለል ጽህፈት ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እየሰራ ነው”።

የገበያ ችግርን ለማቃለል በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ምርት የማስተዋወቅ ስራም እየተሰራ  ነው።

በወረዳው የምርት ጥራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ የመጣበት ሁኔታ ስለሚታይ የዋጋ ማሻሻያ እንዲደረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ስመምነት ላይ ለመድረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተመልክቷል።

በወረዳው እስካሁን 15 ሺህ ሄክታር መሬት በጥጥ ልማት መሸፈኑን ገልጸው ከዚህ ውስጥ 2 ሺህ 225 ሄክታር የሚሆነው በአነስተኛ ከፊል አርብቶ አደሮች  ቀሪው ደግሞ  በባለሀብቶች የለማ ነው።

በወረዳው ከሚገኙ 19 የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ በ14ቱ የጥጥ ልማት እየተካሄደ ሲሆን  በልማቱም ከሦስት ሺህ የሚበልጡ ከፊል አርብቶ አደሮችና ባለሀብቶች እየተሳተፉ ናቸው።

ኃላፊው እንዳሉት በወረዳው በአጠቃላይ በ2008/09 ምርት ዘመን በጥጥ ከለማው 10 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ከ350 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን