አርዕስተ ዜና

የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን በተለየ መንገድ ያጠናከረ ጉብኝት

2355 times

ሃብታሙ አክሊሉ(ኢዜአ)

ኢትዮዽያና አሜሪካ የረጅም አመታት የህዝብ ለህዝብ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሃገራት ናቸው። ይህ ግንኙነትም የአሜሪካው አምባሳደር ሮበርት ፒ ስኪነር በወቅቱ የኢትዮዽያ መሪ ለነበሩት ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ የሹመት ደብዳቤያቸውን ካቀረቡበት እኤአ ከ1903 ዓ.ም ይጀምራል።  

ዳግማዊ አፄ ምንልክና የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቲዎዶር ሩዝቬልት ወኪል ሮበርት ስኪነር ለዘጠኝ ቀናት ካካሄዱት ስብሰባ በኋላ ግንኙነቱ ሊመሰረት ችሏል። ይህ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲህ እየተጠናከረ በመሄድ በጃኑዋሪ 26 ቀን 1929 በተለያዩ የስምምነት ፊርማዎች እያደገ ሊመጣ ቻለ።

መደበኛ ግንኙነቱም እስከ 1935ቱ የጣሊያን ቅኝ ገዢ ወረራ ድረስ ቀጠለ።  

ሃኪም ወርቅነህ እሸቴ እኤአ በ1927 ዩናይትድ ስቴትስን ውስጥ የምትገኘውን ሃርለምን በጎበኙበት ጊዜ የራስ ተፈሪን ሰላምታ በቦታው ለሚገኙ አፍሪካ አሜሪካውያን ካቀረቡላቸው በኋላ ራስ ተፈሪ አፍሪካ አሜሪካውያኑ ወደ ሀገራችን ገብተው መኖር እንደሚችሉ ያላቸውን ፍላጎት ነገሯቸው።

ከዚያም በርካታ አፍሪካ አሜሪካውያን ወደ ኢትዮዽያ በመምጣት መኖር በመጀመራቸው የጣሊያን ወራሪ ሃይል ወደ አገራችን እስከ መጣበት 1935 ዓ.ም ድረስ አገሪቷን በማዘመን ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።

አሜሪካ በወቅቱ ከነበሩን ወዳጅ አገራት የጣሊያንን ወረራ ያወገዘች ብቸኛዋ አገር እንደነበረች አፄ ኃይለስላሴ የህይወት ታሪካቸውን በፃፉበት መፅሃፋቸው ላይ ገልፀውታል።

በ1957 የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ሪቻርድ ኒክሰን አገራችንን በጎበኙበት ወቅት ኢትዮዽያ ቀጣይነት ያለውን ወዳጅነት ከአሜሪካ ጋር ከመሰረቱ አገራት አንዷ መሆኗን ገልፀው ነበር። የመጀመሪያው የአሜሪካ የሰላም ጓድ (The Peace Corps) ኢትዮዽያ የደረሰው እኤአ በ1962 ሲሆን 2 ሺ 934 የሰላም ጓድ አባላትንም ይዞ ነበር።  

የአሜሪካ የ282 ሚሊዮን ዶላር ወታደራዊና የ366 ሚሊዮን ዶላር የግብርና፣ የትምህርት፣ የህብረተሰብ ጤና እና ትራንስፖርት ምጣኔ ሃብታዊ እገዛ ለኢትዮዽያ ያደረገችው ደግሞ እኤአ በ1978 ዓ.ም ላይ ነበር። እንዲህ እያለ የዘለቀው የሁለቱ አገራት ግንኙነት በደርግ ዘመን የተወሰኑ መቀዛቀዞችን አልፎ ኢህአዴግ ሀገሪቷን ከተቆጣጠረ በኋላ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ለዚህም ማሳያ ሊሆን የሚችለው እኤአ በጁላይ 27 ቀን 2015 በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ባራክ ሁሴን ኦባማ በኢትዮዽያ ኦፊሴላዊ ጉብኝት ማድረጋቸው ነው። በርካታ የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጉብኝቱን አስመልክተው ሰፋ ያሉ ዘገባዎችን ሲያሰራጩም እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። በወቅቱም ባራክ ኦባማ ሽብርተኝነትን ከመከላከል እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ምክክር ማድረጋቸውን በታላቁ ቤተ መንግስት በሰጡት የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረው ነበር።

በጋራ ጥቅም መርህ ላይ የተመሰረተው የሁለቱ አገራት ግንኙነት አንዳቸው ለአንዳቸው በመከባበርም እያጠናከሩት የመጣ ግንኙነት ነው። የሃገራቱን ፍላጎት ከግምት ያስገባው ግንኙነትም መሻሻሎችን እያሳየ እስካሁን ዘልቋል።

ከዚህ ቀደም በዕርዳታ መስጠትና መቀበል ላይ በዋነኝነት አተኩሮ ሲካሄድ የነበረው የሃገራቱ ግንኙነት በዚህ ወቅት ደግሞ ምጣኔ ሃብታዊ ትብብርን ለማሳደግ አልሞ እየተከናወነ ይገኛል። 

በዚህ ረገድም የኢትዮዽያ ስትራቴጂካዊ አጋር የሆነችው ሀገረ አሜሪካ በአሁኑ ወቅትም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን ለማሳደግ እየሰራች ትገኛለች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን ወቅታዊ ጉብኝትም ይህንኑ ታሳቢ እንዳደረገ ልብ ይሏል። ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ሃገራችን የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማክሰኞ አመሻሽ ላይ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን ጨምሮ በአሜሪካ የኢትዮዽያ አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን ተቀብለዋቸዋል።

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሃገራችን በነበራቸው ቆይታም በምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮች፣ በዲሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ፣ በፀጥታ እንዲሁም በሽብርተኝነት መከላከል ዙሪያ ምክክር ያደረጉ ሲሆን ሃገሪቷ አሁን ያለችበትን ሁኔታ እንደሚገነዘቡና መንግስት ችግሩን ለመቆጣጠር እየወሰደ የሚገኘውን እርምጃ እናደንቃለን፤ አገሪቷ  ከለችበት የአስቸኳይ ጊዜ  በተቻለ ፍጥነት ብትወጣት መልካመ ነው ብለዋል፡፡

"While we appreciate the government's responsibility to maintain control … it is important that country moves on past the state of emergency as quickly as possible," he said.

ዶክተር ወርቅነህ በበኩላቸው ከአሜሪካ አቻቸው ጋር በሁለቱ አገራት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቶች፣ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታና በሌሎች ዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ገልፀው በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እና መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት አስመልክቶ ለቲለርሰን ገለጻ እንዳደረጉላቸው ተናግረዋል።

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ ማህማት ጋር ባደረጉት ቆይታ የአፍሪካ ተሃድሶ አካል የሆነውን ነፃ የንግድ ቀጣና የመፍጠር እሳቤ ስኬታማ እንዲሆን አሜሪካ ድጋፍ እንደምታደርግ ተናግረዋል። አሜሪካ ከአፍሪካ አገራት ጋር የቆየ ግንኙነት እንዳላት የተናገሩት ኮሚሽነሩ ይህንንም ግንኙነት ለማሳደግ አሜሪካ እንደምትፈልግ መረዳታቸውን ካደረጉት ጠቃሚ ውይይት መገንዘባቸውን አስረድተዋል።

‘የአፍሪካ ኅብረትን ምጣኔ ኃብታዊ የቀጠና ውህደት አጀንዳ እንደግፋለን፤ የንግዱን ትስስር ሊያቀጭጩ የሚችሉ ጉዳዮችን በመቀነስ የተሻለ የንግድ ትስስር ለመፍጠር እንደግፋለን፤ የኅብረቱ ዋነኛ አጀንዳ የሆነውን ነጻ የንግድ ቀጠና እውን እንዲሆን እንተባበራለን፤ በቀጣይም በተመሳሳይ ለመደገፍ እንሰራለን፤ ይህም ደግሞ የአሜሪካ የግል ዘረፉን ወይንም የንግድ ማኅበረሰቡ በአፍሪካ ተሳትፎ አንዲያደርግ ያስችለዋል’ በማለት ነው እንግዲህ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ያስረዱት።

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲለርሰን ለጉብኝታቸው ትኩረት ያደረጉበትን ፍሬ ሃሳብ ስንመለከት ከሃገራችንም ሆነ ከአህጉራችን ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንደ ቀድሞው አንደኛው ለአንደኛ በሚሰጠው ዕርደታ ዙሪያ ብቻ ሳይሆን በእርስ በርስ መጠቃቀም ውስጥ ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገትንም እንዴት መሻሻል እንደሚገባ ሃሳብ የተለዋወጡበት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። ባለፉት አስርት አመታት ከተመዘገቡት ፈጣን የምጣኔ ሃብት ዕድገቶች አምስቱን ከያዘችው አህጉረ አፍሪካ ጋር ሊጠናከር የሚገባው ግንኙነት እንደ ቀድሞው ሊሆን እንደማይገባው አሜሪካ ከምንጊዜውም በላይ የተረዳችው ይመስላል። 

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን