“…ለኔ ከሐውልት የበለጠ ስም ነው”

01 Jan 2017
2185 times

ከአየለ ያረጋል (ኢዜአ)

ወቅቱ ከአስራ ሁለት ወራት በፊት ነው። በደቡብ ኢትዮጵያ ተራራ ለተራራ ገደል ለገደል ሲንከራተቱ በአካባቢው ነዋሪዎች ተስተውለዋል። ሁለት ነጮች። በዚህም አላበቁ በባሌ ተራራ አይጠ መጎጥ መሰል የዱር እንስሳት ሲሰበስቡ ተስተዋሉ። “ምንድነው ሊበሏቸው ነው ኦሯ!” ሳይላቸው አልቀረም አንድ ፍየሎቹን የሚያሰማራ እረኛ።

አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል! እንዲሉ እነዚህ ጸጉረ ልውጦች ግን እንዲሁ የእንስሳት ፍቅር አድሮባቸው አልነበረም። መዝናናት እደሚሹ ቱሪስቶች አልነበረም አይጥ መሰል ፍጡር የሚሰበስቡት።ጉዳዩ ወዲህ ነው! ሰዎቹ የራሽያና የጀርመን ሳይንቲስቶች ነበሩ። ጀርመናዊው ሳይንቲስት ሬነር ሃተረርና ሩሲያዊው ሳይንቲስት ላቭሬንቺንኮ። እናም በደቡብ ኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ላይ ምርምሮችን ሲያካሂዱ ነበር እነዚህን ልዩ ፍጡራን የተመለከቱት። የሰበሰቧቸውን አይጠ መጎጥ መሰል አጥቢ እንስሳት ከጭንቅላት እስከ እግር ጥፍራቸው መረመሯቸው። ዘረ መላቸው፣ ቆዳቸው፣ ክሮሞዞማቸው….ሁሉንም ዓይነት ስነ ህይወታዊ ጥናት አካሄዱባቸው። ግን እስከ አሁን በዓለም ላይ ከተስተዋሉ አጥቢዎች ልዩ ሆኑባቸው።

“እህ!” አሉ እነዚህ ሳይንቲስቶች። “ለካ ኢትዮጵያ ዋሊያና ቀይ ቀበሮ መሰል ብርቅዬ እንስሳት መገኛ ብቻ አይደለችም። እንደነዚህ አይነት ሚጢጢዬ ብርቅዬ አጥቢዎች መፍለቂያም ናት” ብለው እንደተገረሙ አስባለሁ። በሳይንሱ ዓለም ውስጥ አዳዲስ እንስሳት ለዚያውም የሚያጠባ አግኝቶ በቀልድ ማለፍ የለም። ምን ብለው እንደሚሰይሟቸው ሃሳብ ማውጠንጠኑን ተያያዙት።

…ከብዙ ዓመታት በፊት ነው። አንድ ኢትዮጵያዊና አንድ ፈረንጅ የአጥቢ ዱር እንስሳትን ባህርያት ለማወቅ ሲኳትኑ የተስተዋሉት። ኢትዮጵያዊው ግለሰብ በሀገረ እንግሊዝ ማንችስተር ዩኒቨርሲቲ ነው የሁለተኛና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን  ያገኙት። ከጎን የተስተዋሉት ነጭ ዜጋ ደግሞ የእኚህ ኢትዮጵያዊ  አስተማሪ የነበሩ እንግሊዛዊ የመካነ አራዊት ተመራማሪ ናቸው። ሁለቱ ተመራማሪዎችም አያሌ ዓመታትን እጅና ጓንት በመሆን በአጥቢ እንስሳት ዙሪያ ምርምር ሲያደርጉ ነበር የከረሙት።…

ወደ ጉዳዬ ልመለስ። በስነ በመካነ አራዊት ሳይንስ ብዙ ጊዜ አዳዲስ ፍጡራን ሲገኙ በአገር፣ በአህጉር፣ አልፎ አልፎም ትላልቅ ነገር አበርክተው ባለፉ ሳይቲስቶች መሰየም የተለመደ ነው። እና ጀርመናዊና ሩስያዊያን ተመራማሪዎች እነዚህን አጥቢዎች ምን ይበሏቸው? የ13 ወር ፀጋ? የሰው ዘር መገኛ? አዲሲቷ ኢትዮጵያ?.....ወዘተ። “ቆይ! እስኪ ሰው እንፈልግ” አሉና ኢትዮጵያ ውስጥ በዘርፉ ምርምሮችን ያካሄዱ ምሁራንን አሰሱ። ክብር ለሚገባው ክብር እንስጥ! ብለው ወሰኑ። የሁለት ተመራማሪዎችን ስም ከፍለው አዳዲስ ባገኟቸው አጥቢ የዱር እንስሳት ላይ የማይገፈፍ የስያሜ ካባ ደረቡላቸው። ምን ብለው? የሚል ይኖር ይሆናል። 

በቅርብ ሳምንታት በመገናኛ ብዙኃን አዳዲስ ጥንድ ስሞች ወደ አድማጭ እዝነ ልቦና አቃጨሉ። በአንባቢ አይነ ህሌናም ውልብ አሉ። “ክሮስዲዩራ አፈወርቅ በቀላይ” እና “ክሮስዲዩራ የልዶኒ” የሚሉ ስያሜዎች እንደዋዛ ተወርተው አለፉ። እነዚህ ስያሜዎች ከላይ ጣልቃ ያስገባኋቸው ባለታሪኮች ስሞች ናቸው። የኢትዮጵያዊው ስነ መካነ አራዊት ተመራማሪ ፕሮፌሰር “አፈወርቅ በቀለ” እና አስተማሪያቸው እንግሊዛዊው ምሁር ዶክተር “ደሊው ኤች የልደኒ” ስሞች። ግን እነዚህ ሰዎች ምን ቢያደርጉ ነው ስማቸው ለአጥቢ እንስሳት የተሰጠው? የሚለው ጥያቄ በውስጤ ይብላላ ነበር።

ታህሳስ 10 ቀን 2009 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለአምስት ዓመታት ያክል ሲያካሂዳቸው የነበሩትን ችግር ፈች ጥናትና ምርምሮች አውደ ጥናት አካሂዶ ነበር። በታዋቂው የምጣኔ ሃብት ተመራማሪ ስም በተሰየመው በ “እሸቱ ጮሌ ” መሰብሰብያ አዳራሽ። እኔ ደግሞ ሁነቱን ልሸፍን ወደ ስፍራው አቅንቼ ነበር። እንዳጋጣሚ ሆኖ ሌላ መገናኛ ብዙሃን ውስጥ የሚሰራው የትምህርት ቤት ጓደኛዬ ጋር ተገናኝተን ማስታዎሻችንን ዘርግተን መረጃ እንለቅማለን። በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር አድማሱ ፀጋዬ ስለ ፕሮፌሰር አፈወርቅ በቀለ ሃሳብ ወርወር ሲያደርጉ ጆሯችን ቆመ። (በነገራችን ላይ ታህሳስ 12 የዩኒቨርሲቲው ሴኔት የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ካጎናፀፋቸው አምስት ምሁራን መካከል 31 ምርምሮችን ለዓለም አቀፍ ህትመት ያበቁት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር አድማሱ ፀጋዬ አንደኛው መሆናቸውን ልብ ይሏል።)

እናም ፕሮፌሰር የቡድናቸውን ችግር ፈች (ቴማቲክ ሪሰርች) ጥናታቸውን እንዳቀረቡ ነበር ለመቅረፀ ድምፅ የተመኘናቸው። ለቃለ መጠየቁ በለሆህሳስ ስጠይቃቸው ሳያቅማሙ ነበር ፈቃደኛ የሆኑት።  ከአዳራሹ እንደወጣን መጀመሪያ በዕለቱ ስላቀረቡት ምርምር ሲያጫውቱን ቆዩ። ሽበት የፈነጠቀበትን ሪዛቸውን እየደባበሱ ትህትና በሞላበት አነጋገር አብራሩልን። የሙያ አጋሬ ድንገት ነበር ስለ ሰሞኑ ወሬ  ጥያቄ የሰነዘረላቸው።

“ኦ! እሱማ ሰሞኑን እየተወራ አይደል። በባሌ ተራራ ኮንቴ ከተሰኘ አካባቢ ሁለት ትናንሽ አጥቢ እንስሳት ተገኝተው እኔና ሱፐርቫይዘሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በዘርፉ (በተለይም በአጥቢ እንስሳት) ላደረግነው የጥናትና ምርምር አስተዋፆ ነው በስማችን የተሰየሙልን።…” በፈገግታ ተረኩልን።  ከአስተማሪያቸው ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት።

ፕሮፌሰር አፈወርቅ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ውስጥ የተለያ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ ለአርባ ዓመታት አገልግለዋል፤ እያገለገሉም ነው። ባለፉት ዓርባ ዓመታት ምን ያህል ጥናትና ምርምሮችን አደረጉ ፕሮፌሰር? ሌላ ጥያቄ።

“እሱማ! ” አሉ ፕሮፌሰር  ቁጥሩን ለማስታወስ ያህል ከፊታቸው ባለው ነገር ላይ አተኩረው “እሱማ በጣም ብዙ ነው። ከአንድ መቶ በላይ የማስተርስና የፒኤች ዲ ተማሪዎችን አውጥቻለሁ። በፅሁፍም ደረጃ 220 አካባቢ ኢንተርናሽናል ፐብሊኬሽን አውጥቻለሁ። ይሄ ትልቅ አስተዋፆ ነው ብዬ ነው የማስበው…” አሉኝ።

 “…ለኔ ከሐውልት የበለጠ ስም ነው” የሚል እምነት ያላቸው ጠየም፣ ወፈርና በዕድሜ ጠና ያሉት ፕሮፈሰር አፈወርቅ በፈገግታ እያጫወቱን ነው። በዩኒቨርሲቲው የነበራቸው እውቅና እንዴት እንደነበር ስንጠይቃቸው ሩቅ መሄድ እንደማያስፈልግ ነገሩን።

“ … በቅርብ ከማስታውሰው አምና ለምሳሌ በብቁ ማስተማር ስራዬና ባደረኩት ጥናትና ምርምር ከአጠቃላይ ዩኒቨርሲቲው ተሸላሚ ነበርኩኝ እንዳጋጣሚ ሆኖ…! ለአርባ ዓመታት አገልግያለሁ። አስተማሪዬ ደግሞ ከዛ በፊት ጀምሮ። በህይወት እስካለን ድረስ ማገልገል ነው በቃ… ” ፕሮፈሰር ሲያወሩ ትህትና ይስተዋልባቸዋል።

የሆነው ሆኖ “በስያሜው ምን ተሰማዎት?”  የሚለውን ጥያቄ እንደዋዛ ጣል አደረኩ። አሰያየሙ ከበፊት ጀምሮ እንዳለ ብዙውን ጊዜ ግን ሰዎቹ ካረፉ በኋላ ለዚያውም አልፎ አልፎ እንደሆነ አጫወቱን።

“ እንዲህ አይነት አጋጣሚ ሁልጊዜ የሚገኝ አይደለም፤ አልፎ አልፎ ነው። አሰያየሙ ብዙውን ጊዜ የሚሰጠው ከሞት በኋላ ነው። ለምሳሌ ሱፐርቫይዘሬ ከሁለት ዓመት በፊት አርፏል። ምናልባት ብዙ ሰው አይረዳውም፤ አያውቀውም …” እውነት ነው እኔስ መቼ አውቄው በውስጤ እየመለስኩላቸው ነበር።

 “ … ብዙ ሰው አያውቀውም። በሳይንሱ ኮሙኒቲ ግን ትልቅ ነገር ነው።” ስያሜውን ከሓውልት ጋር እያነፃፀሩም አወጉን። እንዲህ ብለው “ሓውልት ዛሬ ይሰራል። ነገ ግን ይወድቃል፤ይፈርሳል። ይህ ስያሜ ግን ትልቅ ነገር ነው። በሳይንስ ዓለም ውስጥ ሰዎች እስካለን ድረስ ምን ጊዜም ህያው ነው። በእውነቱ አላሰብኩትም፣ ያ - ስያሜ ለኔ ትልቅ ትልቅ በጣም ትልቅ በህይወቴ ከምጠብቀው በላይ ነው…ለሱፐርቫይዘሬ በመሰየሙ በጣም በጣም ደስ ብሎኛል። በዛ ላይ ከተማሪው አንድ ላይ እኩል ሲሰየም የበለጠ ደስ ይላል…”

ፕሮፈሰር አፈወርቅ ስለ “ክሮስዲዩራ አፈወርቅ በቀላይ” ማሳረጊያ ንግግራቸው የተረዳሁት ለእርሳቸው ከሓውልት ስም እንደሚበልጥ ነው።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን