አርዕስተ ዜና

ገንዘቤ-የድርብ ድል ባለቤቷ ኢትዮጵያዊት አትሌት

4719 times

ይሁኔ ይስማው /ኢዜአ/

ብዙዎቻችን ደስታችን ከልክ ሲያልፍ እንባ በጉንጫችን ይፈሳል። ስሜቱን እንቆጣጠረው ብንል እንኳ ከውስጥ ፈንቅሎ የሚወጣ በመሆኑ የሚቻል አይደለም፤ ይህን ስሜት ከሚፈጥሩብን አጋጣሚዎች መካከል አንደኛው ደግሞ የአትሌቶቻችን ድል ነው።

አትሌቶቻችን በዓለም አቀፍ መድረክ ብርቱ ፉክክር አድርገው ሲያሸንፉና ከድሉ በኋላ የአገራቸው ሰንደቅ አላማ ከፍ ብሎ ሲውለበለብ የደስታ ስሜት ፈንቅሏቸው እንባ ሲተናነቃቸው፣ ገደቡንም አልፎ በጉንጫቸው ሲወርድ፤ ይህን ስሜታቸውንም ሲያጋቡብን ደጋግሞናል።

ይህ ስሜት እንዲፈታተናቸው ምክንያት የሚሆነው ደግሞ ከአባቶቻቸው የወረሱትን የኢትዮጵያዊነት ወኔ ታጥቀው እልህ አስጨራሽ ትግል አድርገው በመጨረሻም አሸንፈው አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ሰንደቅ ዓላማችንን ከፍ አድርገው ሲያውለበልቡ ነው።

ከሻምበል አትሌት አበበ ቢቂላ የሮም ኦሎምፒክ ድል ጀምሮ የአትሌቶቻችን ድል አድራጊነት በብዙ ውድድሮች እስከ አሁንም በመቀጠሉ ሰንደቅ ዓላማችን ከፍ ብሎ መውለብለቡ፤ አትሌቶቻችን በደስታ ማንባታቸው እኛም የእነሱን ስሜት መጋራታችን ልማድ ሆኗል። ይህ የኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ድል አድራጊነት በኦሎምፒክ ይጀመር እንጂ በዓለም ሻምፒዮና በሌሎች አለምና አህጉር አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች ለመታየት ብዙም ጊዜ አልወሰደም።

የአትሌቶቻችን ጀግንነት ከአበበ ቢቂላ ቀጥሎ በአትሌት ደራርቱ ቱሉ በ1984 ዓ.ም. በስፔን ባርሴሎና ኦሎምፒክ አሸናፊ በመሆን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን መላ አፍሪካዊያንን ያኮራ ድል በማስመዝገብ በሩጫው ዓለም ሌላ ታሪክ መስራት ቻለች።

ከዚያ በኋላ በኢትዮጵያ በኩል በኦሎምፒክ ብቻ ሳይሆን በአለም ሻምፒዮና እና በቤት ውስጥ ውድድሮች አገርና ህዝባቸውን ያኮሩ አትሌቶች አያሌ ናቸው። ጥቁሮች እንደ ነጮች ሁሉ ማሸነፍ የሚችሉ መሆናቸውን በአድዋ ድል የተጀመረው አርያነት በአትሌቲክሱም በጀግናው አበበ ቢቂላ ሮም ላይ ነበር የታየው።

አፍሪካዊያን በአትሌቲክሱ በተለይም የምስራቅ አፍሪካ አገሮች የረጅም ርቀት አሸናፊ መሆናቸው በተደጋጋሚ በማሳየት የርቀቱ የበላይ መሆናቸውን እያረጋገጡ መጥተዋል። ይሁን እንጂ ያደጉት አገሮች ብዙም በአፍሪካ የልምምድ ቦታ ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ የተሻለ የማሸነፍ እድል እናገኝበታለን ያሉትን የቤት ውስጥ ውድድር በ1979 ዓ.ም. ጀምሮ ይዘው ብቅ ብለዋል። ውድድሩ ለዓለም ከተዋወቀ በኋላ ከአህጉራችን ኢትዮጵያ ብርቱ ተፎካካሪ በመሆን ታሪክ መጻፍ ከጀመረች ዋል አደር ብላለች።

በየሁለት ዓመቱ በሚደረገው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና እስካሁን 17 ውድድሮች ሲካሄዱ ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ከተካሄደው ሻምፒዮና ጀምሮ ተሳታፊ ናት። በሻምፒዮናው በ16 ውድድሮች ላይ ተካፍላም 27 የወርቅ፣ 10 የብርና 13 የነሀስ ሜዳሊያዎች በመሰበስብ ከአሜሪካና ከሩሲያ ቀጥሎ በሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥም ችላለች።

እስካሁን በተካሄዱ ውድድሮች በዚህ ሻምፒዮና ተካፍለው የአገራቸውን ስም ካስጠሩ አትሌቶች መካከል አትሌት መሰረት ደፋር አራት ወርቅ አንድ ብርና አንድ ነሀስ እንዲሁም አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ አራት የወርቅ ሜዳሊያዎች አምጥተዋል።

ከየካቲት 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለአራት ቀናት በእንግሊዝ በርሚንግሃም ከተማ በተደረገው ውድድር አትሌቶቻችን ሁለተኛውን ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበው ነው የተመለሱት። በውድድሩ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ ብቻ በ3 ሺህ እና በ1 ሺህ 500 ሜትር ሁለት የወርቅ ሜዳሊያ ስታስገኝ አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ በ3 ሺህ ሜትር ወርቅ፣ ሰለሞን ባረጋ ብር፣ ሳሙኤል ተፈራ በ1 ሺህ 500 ሜትር ወርቅ ማስመዝገብ ችለዋል።

ገንዘቤ በዚህ ውድድር ማሸነፏን ተከትሎ ከ18 ዓመት በኋላ በቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኃይሌ ገብረስላሴን ታሪክ በመድገም ታሪኩን ተጋርታለች።

ኃይሌ በ1991 ዓ.ም. በጃፓን በተደረገው የቤት ውስጥ ውድድር በ3 ሺህ እና በ1 ሺህ 500 ሜትር ሁለት የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል።

ከኃይሌ በቀር ማንም ኢትዮጵያዊ አትሌት በአንድ ውድድር ሁለት የወርቅ ሜዳሊያ ያመጣ አልነበረም፤ ገንዘቤ ግን ይህን ክብር መጋራት ችላለች።

ሌላው ገንዘቤ በዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮን የሰራችው ታሪክ ደግሞ በአንድ ውድድር ሁለት የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት በዓለም ላይ ከሚገኙ እንስት አትሌቶች ቀዳሚ መሆኗ ነው።

ገንዘቤ በዚህ ውድድር ሁለት ወርቅ ማግኘቷን ተከትሎ በቤት ውስጥ ውድድር ለአገሯ ያገኘቻቸውን የወርቅ ሜዳሊያዎች ብዛት ወደ አምስት ከፍ በማድረግ በኃይሌና መሰረት ደፋር ተይዞ የነበረውን አራት የወርቅ ሜዳሊያ ክብር ወሰን መስበርም ችላለች።

አትሌቷ ከድሉ መልስ ቦሌ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል ሲደረግላቸው ከጋዜጠኞች ጋር በነበራት ቆይታ ''በ17ኛው የበርሚንግሃም ውድድር በነበረው ቅድመ ዝግጅት ላይ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ለአገርሽ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያ በማምጣት የእኔን ታሪክ መድገም አለብሽ ብሎኝ ነበር ያንንም ማድረግ ችያለሁ'' ነው ያለችው።

ከዚህ ውድድር ከስድስት ወራት ቀደም ብሎ ተካሂዶ በነበረው የዓለም ሻምፒዮና ላይ ገንዘቤ ሜዳሊያ ታመጣለች ተብሎ ሲጠበቅ ይህን ማድረግ አልቻለችም ነበር። ይህን ደግሞ በወቅቱ በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃንና በህዝቡ የተሰጠው አስተያየት ስሜቷን እንደጎዳው ተናግራለች። በለንደኑ የዓለም ሻምፒዮና ውጤት ያጣችው በወገብ ህመም ምክንያት እንደነበረም ነው የገለጸችው።

ይህንን እውነታ ካለመረዳት የአትሌቷ ስም ባልተገባ መንገድ ሲነሳ እንደነበር ይታወሳል። አትሌቶቻችን አገራቸውን ወክለው ሲወዳደሩና በተለያዩ ምክንያቶች ውጤት ሲያጡ ተገቢ ያልሆኑ አስተያየቶች ሲሰጡ ይስተዋላል፤ ነገር ግን አንድ አትሌት ዳጎስ ያለ ሽልማት በሚያስገኝ ውድድር ላይ ለመካፈል ስምና ዝናውን ከፍ ማድረግ አለበት።

አትሌቶችም ስማቸውን የሚገነቡት አገራቸውን ወክለው በሚሮጡባቸው ውድድሮች ላይ ነው። አገሩን ወክሎ በመወዳደር በኦሎምፒክ በዓለም ሻምፒዮናና ሌሎች አገር አቋራጭ ውድድሮች አሸናፊ በሆነ ቁጥር በግል ውድድር አዘጋጆች በኩል ለውድድር ድምቀት ሲባል መጋበዝ ይጀምራሉ።

አትሌት ገንዘቤም ሲሰጣት ለነበረው ያልተገባ ትችት ቦታ ሳትሰጥ ተግታ በመስራት ለአገሯ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቷ እጅጉን እንዳስደሰታትና በቀጣይም ለአገሯ ተጨማሪ ሜዳሊያዎች ለማምጣት እንደምትሰራ ተናግራለች።

በያዝነው የፈረንጆቹ 2018 ዓመት ደግሞ በእህቷ ጥሩነሽ ዲባባ የተያዘውን የ5 ሺህ ሜትር ክብረ ወሰን የመስበርና የዲባባ ስም ሳይቀየር ጥሩነሽን በገንዘቤ ለመተካት ማቀዷን ተናግራለች፤ እኛም ስኬትን ተመኝተንላታል።

 

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን