"ማርሽ ቀያሪው" የኢትዮጵያ ባለውለታ

26 Dec 2016
2360 times

በይብራህ አምባዬ /ኢዜአ/

ትውልዱ ሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ነው፤ የትውልድ መንደሩን አዲግራት ተራራማና ዳገታማ ቦታዎች መውጣት መውረድ የማይታክት የነበረው ይህ ሰው ጋሪ ነጂ፣ የፋብሪካ ሰራተኛም ነበር። በፋብሪካ ሰራተኝነቱ ብዙም ሳይገፋ  በዚያን ጊዜዋ ደብረ ዘይት በአሁኗ ቢሾፍቱ ከተማ አየር ኃይልን ተቀላቀለ።

የአየር ኃይል ካፒቴን ሆኖ በማገልገል ላይ ሳለ የወቅቱ የአየር ኃይል አትሌቲክስ ክለብ አሰልጣኝ ብቃቱን በማየት በክለቡ ውስጥ ልምምድ እንዲሰራ ጋበዘው። በዚህ ጅማሬም ወደ አትሌቲክሱ ዓለም ተቀላቀለ። ይህ ሰው በ1980 የሞስኮ ኦሊምፒክ ዓለምን ጉድ ባሰኘው የአምስትና 10 ሺህ ሜትር ውድድሮች አጨራረሱና ድሉ "ማርሽ ቀያሪው" የሚል ስያሜ የተሰጠው አትሌት ምሩፅ ይፍጠር ነው።

አትሌት ምሩጽ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1972 ለመጀመሪያ ጊዜ በጀርመን ሙኒክ ኦሊምፒክ በ10 ሺህ ሜትር ተወዳድሮ የነሐስ ሜዳሊያ አስገኝቷል። በወቅቱ በአምስት ሺህ ሜትር ይወዳደራል ተብሎ ሲጠበቅ አሰልጣኙ በመዘግየቱ ወደ ውድድር እንዳይገባ ተደረገ።

ወደ አገሩ ሲመለስ የጠበቀው ላስገኘው የነሐስ ሜዳሊያ ሽልማት ሳይሆን ወህኒ ቤት መወርወር ነበር። ለስምንት ወራት አገርህን ወክለህ ሂደህ ለምን በአምስት ሺህ ሜትር ሳትወዳደር ቀረህ በሚል ሰበብ በእስር ላይ ቆይቷል።

በወቅቱ ይህን ያደረጉትም አሰልጣኙና የቡድን መሪው ሲሆኑ ራሳቸውን ከተጠያቂነት ለማዳን ሲሉ ነበር። ምሩጽ ለመወዳደር ፍላጎት እንደነበረውና አሰልጣኝ ባለመኖሩ ምክንያት ሳይወዳደር መቅረቱን በማስረዳቱ ከእስር እንዲፈታ ተደረገ።

ከአንድ ዓመት በኋላ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1973 በናይጄሪያ ሌጎስ በተካሄደው የመላ አፍሪካ ጨዋታ ኢትዮጵያን በመወከል በ10 ሺህ ሜትር ወርቅ፣ በአምስት ሺህ ሜትር የብር ሜዳሊያ አስገኝቷል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1977ና በ1979 በተካሄደው የዓለም ሻምፒዮናም በአምስትና በ10 ሺህ ሜትር ተከታታይ ድል ተጎናጽፏል። በሁለቱም የዓለም ሻምፒዮና ውድድሮች በአምስትና በ10 ሺህ ሜትር በድምሩ አራት የወርቅ ሜዳሊያ ማስገኘት የቻለ አትሌትም ነው።

በ1980 የሞስኮ ኦሊምፒክ አገሩን ወክሎ ወደ ሩሲያ ያቀናው አትሌት ምሩፅ ይፍጠር ዓለምን ያስገረመ ድል ተጎናጸፈ።

በአምስትና በ10 ሺህ ሜትር ተወዳድሮ በሁለቱም ርቀቶች ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን አገኘ፤ በዚያን ጊዜ ዓለምን ጉድ ያሰኘው ሁለት ወርቅ ማግኘቱ አልነበረም፤ የወርቅ ሜዳሊያዎቹን ያገኘበት አሯሯጡ እንጂ።

ምሩፅ ሁለቱም ውድድሮች ሊጠናቀቁ ሁለት መቶ ሜትር ያህል ሲቀረው ያሳየው የአጨራረስ ፍጥነት ሙሉውን ዙር እንደሮጠረ አትሌት ሳይሆን የዱላ ቅብብል ውድድር የመጨረሻ ጨራሽ ነበር የሚያስመስለው። በዚህ የአጨራረስ ብቃቱና በሚያመጣው አዲስ ጉልበት "Miruts the Shifter" ወይንም "ማርሽ ቀያሪው" የሚል ስያሜ ተሰጠው።

አትሌቱ በሞስኮ ኦሊምፒክ በሁለቱም ርቀቶች ማሸነፉን ተከትሎ በአንድ ኦሊምፒክ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ያስገኘ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሆነ። በአምስት ሺህ ሜትር ለመጀመሪያ ጊዜ ወርቅ ያመጣ ብቸኛው አፍሪካዊ ምሩፅ ይፍጠር።

በዓለምና በአህጉር አቀፍ ውድድሮች ሰባት የወርቅ፣ አንድ የብርና አንድ የነሐስ በድምሩ ዘጠኝ ሜዳሊያዎችን ለአገሩ ያስመዘገበ አትሌትም ነው።

ምሩፅ በሞስኮ ኦሊምፒክ ሲያሸንፍ ዕድሜው 37 ነበር። ዕድሜውን የተጠራጠሩ ባለሙያዎች ምሩፅን ሲጠይቁት "ሰዎች በጎቼንና ዶሮዎቼን ሊሰርቁኝ ይችላሉ፤ ዕድሜዬን ግን ማንም ሊወስድብኝ አይችልም" የሚል ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል።

የዓለም የረጅም ርቀት ንጉስ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴን ጨምሮ ለአትሌት ቀነኒሳ በቀለ፣ ስለሺ ስህንና ሌሎችም የአገራችን ብርቅዬ አትሌቶች ዓርአያ በመሆን ታላላቆች እንዲፈሩ ያደረገ ታላቅ አትሌትም ነው።

አትሌት ምሩፅ በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ካደረጋቸው ከ410 በላይ ውድድሮች 271 ጊዜ በአሸናፊነት ማጠናቀቅ ችሏል። ምሩፅ ከዓለም አቀፍ የስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበርም የወርቅ ጫማ ሽልማት ተበርክቶለታል።

የአትሌት ዕድሜ ሲገፋ እግር ነበር የሚያጥረው፤ ምሩጽን ያጠረው ግን እግር ሳይሆን ትንፋሽ ነበር።

በወርሃ ግንቦት 1937 ዓ.ም ወደዚህች ዓለም የተቀላቀለው አትሌት ምሩፅ ይፍጠር ባደረበት ህመም ምክንያት በካናዳ ህክምና ሲከታተል ቆይቶ ታህሳስ 14 ቀን 2009 ዓ.ም በ72 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

የአትሌቱ አስከሬን በዚህ ሳምንት ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጣ እየተጠበቀ ነው። በሕይወት ዘመኑ ብዙም ድጋፍ እንዳልተደረገለት ለሚነገረው፤ የአገሩ ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባዮች ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ በማድረግ ለዋለው ውለታ ለ"ማርሽ ቀያሪው" ዘላለማዊ ሃውልት ይገባዋል እንጂ አይበዛበትም።

ለመላ ቤተሰቡና ወዳጆቹ መፅናናትን ተመኘን። ነፍስ ይማር!

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን