ህዳር ሲታጠን...

10 Dec 2016
2309 times

ዮናታን ዘብዴዎስ (ኢዜአ)

የጠዋቱ ነፋስ ባህሪውን ቀይሯል፡፡ የስራቸው ባህሪ አስገዳጅ ሆኖባቸው ገና ጎህ ሲቀድ በጎዳናው ጠርዝ የቆሙ ታክሲ  ወይም ባጃጅ የሚጠባበቁ ሰዎች አልፎ አልፎ ይታያሉ ።

የለም ለምን ? ሰሞኑን በከተማው ለህዘብ አገልግሎት እንዲሰጡ በማህበር ተደራጀተው የሚሰሩ ባጃጆች በታሪፍ ጫኑን የሚሉዋቸውን ሰዎች ‹‹ አንሰማችሁም›› ካሉ ሰነባብተዋል ።

ለዕለት ጉርሱ እርሾ ለመጣል ነግቶ ሳይጨርስ ማልዶ በባዶ ሆዱ ከቤቱ የወጣ ምስኪን እንዴት ከአንድ ኪሎ ሜትር የማይልቅ መንገድ 40 እና 50 ብር ከፍሎ ሊሄድ ይችላል? አጠገቤ ቆሞ የሚያማርረው 50 ብር ቢኖረው ከሞቀ አልጋው ባልተነሳ፡፡

የበረሃ ቆጭቆጫ (ዳጣ) እንደበላ ሰው ቀዝቃዛውን አየር ወደ ውስጥ እየሳበ ሄድድድድድድድድ ይላል፡፡

ከባጃጅ ጠባቂዎች አንዱ ነበርኩኝ፡፡ እውነት ነው  የሰሞኑ የሐዋሳ ከተማ የጧት ነፋስ ከቆዳ አልፎ፣ ስጋን ተሻግሮ ፣ ከአጥንት ዘልቆ መቅኔህን ያቀዘቅዛል፡፡

 ባጀጅ ፍለጋ ግራ ቀኝ ሳማትር በባጃጅ ፍለጋ የታከተው ዓይኔ አራት እናቶች ላይ አረፈ፡፡ ትኩረቴን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠሩት፡፡

እማማ... ረጅም ፤ ደርበብ ያለ ቀምስ ለብሰዋል፡፡ ወፈር ያለ ሹራብ ደርበዋል፡፡ ከላዩ ላይ አንፀባራቂ ሰደሪያ ነገር ጣል አድርገውበታል፡፡

እማማ እጃቸው ላይ በጨበጡት ሰፊ መጥረጊያ አስፋልቱን ያቦኑታል፡፡ የውሃ ኮዳዎችን፣ የጫት ጋራባዎችን፣ ከቤት ተጠርገው የተጣሉ የሚመስሉ ደቃቃ ቆሻሻዎችን ከግራ ወደ ከቀኝ፣ ከቀኝ ወደ ግራ እያሾሩ ስብስብ አድርገው በሆነ ከረጥት ይጨምራሉ ፡፡

አቧራው እጃቸው የያዙት መጥረጊያና አስፋልቱ በሚፈጥረው ሰበቃ ይቦናል፡፡

መነሻውን እዚህ ጋር ያደረገው አቧራ ሰውነታቸውን አልብሶ ከአፍንጫቸው አልፎ ወደ ሰማይ ይሄድ ይሄድና የሆነ ቦታ ሲደርስ ይሰወራል፡፡ እነ እማማ ጉንፋን አይዛቸውም እንዴ?

ጎንበስ ስል  ምድር ተጠርጎ ንፁህ ነው፡፡ እነሱ ባፀዱት ምድር ላይ ቆሜ ነው ለካ እያማረርኩ ያለሁት ። ያለወትሮው  ብዙዎችን እያስከፋ ያለው የሀዋሳ ከተማ የጧት ቆፈን   እነ እማማን  ግድ አልሰጣቸው ይሆን ? ፡፡

የህዳር ወር እየተገባደደ ነው፡፡   ቅዝቃዜና ህዳር ... ፤ የነማማ ፅዳትና  ህዳር…  እያዛመድኩ ሳለ ህዳር ሲታጠን ትዝ አለኝ ፡፡ የዛሬ አንድ መቶ ዓመታት ገደማ የኋሊት እንድጓዝ ተገደድኩኝ፡፡

በ20ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያው  ዓመታት ለአለም ህዝቦች የችግር ፣ የስቃይና የሰቆቃ ነበሩ፡፡

በወቅቱ ሃያላን የሚባሉ መንግስታት ጎራ በመክፈል በከፈቱት ጦርነት አለም ትታመስ ነበረና፡፡

እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር ከ1914 እስከ 1918 ድረስ አለም አንደኛውን የአለም ጦርነትን ወደደችም ተገደደችም አስተናግዳለች፡፡

በዚህም ከ15 ሚሊዮን በላይ የሰው ህይወት ተቀጥፏል፡፡ ከ20 ሚሊየን በላይ ሰዎችም ደምተዋል፤ ቆስለዋል፡፡

አዛውንት ህጻን ፤ ልጅ አዋቂ፤ ሴት ወንድ ሳይለይ የብዙዎችን ህይወት የቀጠፈና ለእልቂት የዳረገው ይሄው ጦርነት በአለም ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የመጀመሪያው የአለም ጦርነት ሆኗል፡፡

1ኛው የአለም ጦርነት እንደማብቃት ሲል የአለም ህዝቦችም ትንሽ ፋታ እንዳገኙ  ሌላ ፍዳ  ተጋረጠባቸው፡፡

በሃያላን አገራት ተጠንስሶ ለብዙዎች ሞት ምክንያት የሆነው ጦርነት ሲከስም መላው የአለም ህዝብ ከደቡብ እስከ ሰሜን ከምዕራብ እስከ ምስራቅ በኢንፍሎንዛ በሽታ ተወረረ፡፡

ይህ ‘’የስፓንሽ ፍሉ’’ በመባል የሚታወቀው ወረርሽኝ መነሻው ከአሜሪካ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜም ከዚያች አገር በበሽታው የተጠቁት ወታደሮች እንደሆኑም ታሪክ ከትቧል፡፡

በአፍሪካ አገራትም በ1918 ዓመት የታየ ሲሆን ሴራሊዮን ቀዳሚ ነበረች፡፡ በወቅቱ የእንግሊዚ ቅኝ ግዛት ስር የነበረችው የአገሪቷ ዋና ከተማ ፍሪታውንን ብቻ አጥቅቶ አላበቃም ወደ ሌሎችም ተዛመተ፡፡

ኢትዮጵያም በአለም ከታየ ከአስር ወራት በኃላ ወረርሽኙን አስተናግዳለች፡፡ ህዳር 11 በ1911ዓ.ም፡፡

አገሪቷ ከዳር እስከ ዳር በበሽታው ተረብሻ እንደነበረች ድርሳናት ያመለክታሉ፡፡ በሽታው በወቅቱ 40 ሺህ የሚጠጋ የሃገሬን ህዝብ ለሞት የዳረገ ሲሆን የበሽታው አስከፊነት እያደገ በመሄዱ የወቅቱ የአገሪቱ ንጉስ ነጋሪት ማስጎሰም ግድ ሆኖባቸው ነበር ፡፡

በሽታው በአዲስ አበባ የቆየው ከህዳር 7 እስከ 20 1911 ዓ.ም ሲሆን በህዳር 12 በርካታ ሰዎች ለህልፈት ከመዳረጉ የተነሳ በሽታው  ‹‹የህዳር በሽታ›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡

የወቅቱ መሪ ቀዳማዊ ሚኒልክ ጉዳዩ አሳስቦዋቸው ከተለያዩ ሃገራት የህክምና ባለሙያዎች ጋር ተወያይተው እንደነበረ ታሪክ ያስረዳል፡፡

አሳሳቢ የሆነው ወረርሽ ቀጥሎ ሌሎች ሹማምንትን ጨምሮ ቀዳማዊ ኃ/ስላሴና ባለቤታቸው መነን አስፋውን ያስጨንቃቸው እንደነበረ ይታወቃል፡፡ የበሽታው መንስኤ ቆሻሻ ነው ተብሎ በመታመኑ የጽዳት ዘመቻ እንዲደረግ ታውጃል፡፡

የነገስታቶቹ  ሃኪም ሊባኖሲያዊው ዶ/ር አሳድ ቼባን በበሽታው ተይዞ የነበረ ሲሆን የወቅቱ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ በጉብኝት ወቅት በወረርሽኙ ምክንያት ከሞቱት ውስጥ አንዱ ነበሩ፡፡

የከተማውን የንጽህና ጉድለት የተመለከቱት የጀርመንና የጣሊያን ሃኪሞች ለበሽታው መዛመት ምክንያቱ ቆሻሻ መሆኑንና የፅዳት ጉድለት መሆኑን ለጃንሆይ በመግለጻቸው ጃንሆይ መጥረጊያ ይዘው መውጣታቸውን የጉዳዩን ክብደት የሚያመላክት ነበረ፡፡

እዚህ ጋር ከጃንሆይ ትልቅ ትምህርት መውሰድ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ስንቶቻችን እንሆን ሌላውን ሰፈር ወይም መንገድ እያቆሸሽን በተጠረገና በፀዳ መንገድ መሄድ የምንፈለግ?

አሁን ትናንት ውሃ የምትመስል አዲስ ሃይላክስ መኪና በኛ ሰፈር ስታልፍ በጥቁር ፌስታል የተቋጠረ ጥቁር ግኡዝ ነገር እንደቀልድ ጣል አድርጋ አለፈች፡፡ መኪናው ውስጥ የነበሩ ሰዎች እነማን ይሁኑ... ? መኪና ማን ይይዛል? እገሌ ብላችሁኝ እንዳልስቅ... የተማረ፣ የተሾመ...

በአዋጁ መሰረት በህዳር 11 የጽዳት ዘመቻ ተደርጎ ከዚያ ቀን ጀምሮ ህዳር ሲታጠን እየተባለ በየዓመቱ ቆሻሻ እየተሰበሰበ መቃጠሉ ቀጠለ፡፡ እንደ ባህል የሚወሰደው “ህዳር ሲታጠን“ ህዳር ሲታጠን እገሌ ተወለደ፤ ተወለደች እየተባለ የዘመን መቁጠሪያም ሆነ፡፡

ባለፈው ዓመት በአገሪቱ የተለያዩ አከባቢዎች ታይቶ የነበረው አሁንም ጨርሶ እንዳልጠፋ የሚነገርለት የግልና የአከባቢ ንፅህናችንን ባለመጠበቅ የሚከሰተው አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት /አተት/ የቅርብ ጊዜ ትዝታቸውን ነው፡፡

በርካቶች የሃኪም ቤት ደጅ ጠንተዋል፡፡አንዳንዶችም እስከወዲያኛው አሸልበዋል፡፡

የቆሻሻ አወጋገዳችን ስርዓት ችግር ያለበት መሆኑን ነው በከተማው ጽዳት ላይ የተሰማሩ ማልደው መጥረጊያቸው ከአስፓልቱ የሚያኖሩት ወ/ሮ እቴነሽ ይልማ የነገሩኝ፡፡

ጓደኛቸው ወ/ሮ ገነት በከራ የሀዋሳ ከተማ ስም በውበትና ፅዳት እንዲነሳ ምክንያት መሆናቸውን ሲናገሩ በመሉ እምነት ነው፡፡

ግን ከንፈራቸውን የሚያሥመጥጥ ነገር መኖሩን አልደበቁንም፡፡ ሃላፊነት የማይሰማው፣ ግድየለሽ፣ ከአሁን ወዲያ ያለውን ጊዜ የማያይ ትውልድ ተፈጥሯል ይላሉ፡፡ 

እነማማ ህዳርን የማይጠብቁ ነገር ግን ነጋ ጠባ የከተማዋን ፅዳት እየጠበቁ የሚኖሩ፤  ያኔ የዛሬ 100 ዓመት ገደማ የታወጀውን የህዳር 11ቀን 1918 ዓ.ም አዋጅ ዛሬም ድረስ የሚፈፅሙ፣ ከጃንሆይ በተረከቡት መጥረጊያ አደራቸውን የሚወጡ የሃዋሳ ከተማ የፅዳትና የውበት አምባሳደሮች ናቸው፡፡

ህዳርና ህዳር ሲታጠንን አስመልክቼ ከአንዳንድ የሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ማውራቴ አልቀረምና ‹‹ህዳር ሲታጠን ተምሳሌት እንጂ ቆሻሻችን  ከርሞ ዘመቻ የምንወጣበት መሆን የለበትም›› አሉኝ፡፡

የዛሬ 100 ዓመት  ገደማ የተደረገውን የ‹‹ህዳር ሲታጠንን ›› ዘመቻ እየኮነንኩ አለመሆኔ ከግንዛቤ እንዲገባ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ቆሻሻ እያቃጠልን አካባቢ እንበክል ማለት አይደለም፡፡

በዚያን ጊዜ የነበረው ቴክኖሎጂ ቆሻሻን ሰብስቦ ማቃጠል ሊሆን ይችላል ፡፡ አሁንስ ? አሁንማ ቆሻሻ የሃይል ምንጭ ሆኖ የለም እንዴ?

በነገራችን ላይ እነ እማማ እቴነሽ መሰል 1 ሺህ 096 እናቶች ዘወትር ለሀዋሳ ከተማ ፅዳት ዘብ ይቆማሉ፡፡

ይህንን የነገሩኝ የከተማው ማዘጋጃ ቤት ፅዳትና ውበት አረንጓዴ ልማት ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አበባው ዋቅጅራ ናቸው፡፡

51 ማህበራትም ቆሻሻ በማስወገድ ሥራ ተሠማርተዋል ። በእነዚህ ሰዎች አማካይነት የተሰበሰበው ቆሻሻ በዓይነት ዓይነት ተለይቶ ይቀመጣል አሉኝ፡፡

ይቀመጣል ? ... ለምን ማለት አይቀርምና ለምን ?  አልኩኝ ፡፡

"ፒላስቲኩ ከወዲያ ለብቻ ፣ ብርጭቆና ቶሎ የሚበሰብሱና ለማዳበሪያነት የሚውለውን ለየቅል ያስቀምጣሉ"  ሁሉም ቆሻሻ አይጣልም ። ለሀዋሳ ከተማ ውበት ለሆኑ አረንጓዴ ስፍራዎች ማዳበሪያነት ይውላሉ፡፡

በከተማው ኮምፖስት በማምረት የተሠማራ ማህበር ለኮምፖስት ይሆነኛል የሚለውን ቆሻሻ ለይቶ ይወስዳል፡፡

ማህበሩ የወሰደውን ቆሻሻ በጥንቃቄ ያዋህድ፥ ያቀነናብርና አበስብሶ ወደ ኮምፖስት ለውጦ መልሶ በከተማው በአረንጓዴ ልማት  ስራ ለተደራጁ ማህበራት ይሸጣል፡፡ ቆሻሻ'ኮ ሃብት ነው፡፡ እንጀራ፡፡

"አባኮዳ"  ከሚባል የውጭ ድርጅት ጋር በመተባበር እንዳደጉት አገራት ወደ ኃይል ለመለወጥ ፕሮጀክት ተቀርፆ ፣ቦታ ተመርጦ ወደ ተግባር ሊገባ እንደሆነም አቶ አበባው ጠቁመውኛል፡፡

አቶ አበባው ቀጥለውም የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓታችን ከፊት የሄደው የሙዝ ልጣጭ ይጥላል ፤ ከኋላው ያለው  ያነሳል፡፡  ይኸው ነው፡፡ ሲሉ ትዝብታቸውን ነገሩኝ፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ህዝብ መሳተፍ አለበት ያሉት አቶ አበባው 4ሺህ 1መቶ 11 የ1ለ 5 አደረጃጀቶች፣1ሺህ 005 ብሎክና 169 መንደሮች አሉን ።እነዚህን ተጠቅመን እንሠራለን፡፡

እነዚህ ሁሉ ታዲያ የውቢቷ ሃዋሳ ሚስጢሮች ለተከታታይ ዓመታት በከተሞች ቀን ዋንጫ ያሸለሙዋት ናቸው፡፡ ህዳር ሲታጠንን በማይጠብቁ የንጋት ጽዳት አምባሳደሮች ውጤት የህዳር ሲታጠን ትዝታየ ስንቱን አስወራኝ - ቸር እንሰንብት ! ፡፡

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን