ENA


ባለፉት ስድስት ወራት 700 ሺህ ለሚጠጉ ዜጎች የሥራ እድል ተፈጥሯል

  አዲስ አበባ የካቲት 05/2005 በመላው አገሪቱ ባለፉት ስድስት ወራት ከተለያዩ ግዙፍ የመንግስት ፕሮጀክቶች ጋር በተፈጠረ ትስስር ከ700 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ እድል መፈጠሩን የፌዴራል ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡ የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ዋና አስተባባሪ አቶ አሰፋ ፈረደ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ከመደበኛ፣ ከመንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶችና ከብረታ ብረት ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር በተፈጠረው ትስስርም 39 በመቶ ሴቶች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ የዕቅዱን 87 በመቶ በተከናወነው በዚህ ፕሮጀክትም ከፍተኛውን የስራ ዕድል የፈጠረው የኮንስትራክሽን ዘርፍ መሆኑንም አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡ ይህም ከአለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ15 በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል፡፡ አስተባባሪው እንዳሉት ይህ ውጤት ሊገኝ የቻለው አስፈፃሚ እና ባለድርሻ አካላት በተሻለ ሁኔታ ተቀናጅተው መስራታቸው የሚጠቀስ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ እንዲሁም የመንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶች አብዛኛዎቹ ወደ ግንባታ በመግባታቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጋቸውንም አስረድተዋል፡፡ ከቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኤጀንሲ ከመንገዶች ባለሥልጣን ጋር በጋራ በመሆን በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚሠማሩ የባለሙያዎች ብቃት ምዘና መሳሪያ ተዘጋጅቶ መሪ መዛኞችና አሰልጣኞች በበቂ ሁኔታ ለማፍራት መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡ በዚህም በተጠቀሱት ወራት 6 ሺህ ባለሙያዎች የተመዘኑ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 90 መሪ መዛኞችን ማፍራት ተችሏል ብለዋል፡፡
 
 
 
 
  Leave Your Comments Here  
Name:  
Email:  
Comment: