|
የጤና አቅርቦትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የጤና ጣቢያዎችን ግንባታ አጠናክሮ ቀጥሏል
|
|
|
ፍቼ ጥር 28/2005 የጤና አቅርቦትን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የጤና ጣቢያዎችን ግንባታ አጠናክሮ መቀጠሉን የኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር ገለጸ።
የአስተዳደሩ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ ቂጤሳ ጫላ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት ዘንድሮ ለሚገነቡ 12 ጤና ጣቢያዎች 36 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ለ14 ወረዳ ተከፋፍሏል።
ወረዳዎቹ የጤና ጣቢያዎቹን ግንባታ ለመጀመር በተለያዩ ደረጃዎች ላይ እንደሚገኙ የጠቆሙት አቶ ቄጤሳ ከጤና ጣቢያዎቹ ግንባታ በተጓዳኝ የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን ጨምሮ ሌሎች የማትጊያ ስልቶች በመጠቀም ከፍተኛ የጤና ባለሙያዎችን የማሟላት ተግባር ጽህፈት ቤቱ እያካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል ።
አምና ግንባታቸው የተጀመሩ 13 ጤና ጣቢያዎች በተያዘው ዓመት ተጠናቅቀው በቀጣይ ዓመት ስራ እንደሚጀምሩ ጠቁመዋል ።
የጤና ጣቢያዎቹ ሙሉ ለሙሉ ከሁለት ዓመት በኋላ ስራ ሲጀምሩ ቀደም ሲል 89 በመቶ የነበረውን የጤና ሽፋን ወደ 96 በመቶ ከፍ እንደሚያደርገውና የዞኑን 1ነጥብ 5 ሚሊዮን ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን አስታውቀዋል ።
በጤና ዘርፍ ላይ ትልቅ ለወጥ እንደሚያመጣና እናቶችና ሕፃናት የተሻለ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ የምዕት ዓመቱን የጤና ልማት ዕቅድ ለማሳካት እንደሚያስችል ጠቁመዋል ።
አንድ ጤና ጣቢያ 35 ሺህ ሰው እንዲያገለግል ፣አንድ ሃኪም በተመላላሽ ህክምና ከ35 እስከ 50 ሰዎች እንዲያክምና በቀን ከ200 እስከ 300 በሽተኞች በአንድ ጤና ጣቢያ እንዲገለገሉ የሚያስችል ስልት መነደፉን አስታውቀዋል ።
የጤና ጣቢያዎቹ በአቅራቢያቸው ከሚገነቡባቸው አካባቢያቸው መካከል የኩዩና ደገም ወረዳ ነዋሪዎች እንዳመለከቱት ለበርካታ አመታት የጤና አገልገሎት ፍለጋ ከፍተኛ ወጭ በማውጣት ርቀው ይጓዛሉ።
አሁን ግን በአቅራቢያቸው ተቋማቱ በመገንባታቸው በጥቂት ወጭ ህክምና ከማግኘት በተጨማሪ የጤና ተኮር ትምህርት በማግኘት ገንዛቤያቸውን ማስፋት እንደቻሉ ተናግረዋል ።
የኩዩ ወረዳ ነዋሪ አቶ መሀመድ ሰይድ ፣የደገም ወረዳ ነዋሪ አቶ ጥበቡ ተሾመና ወይዘሮ አጀቡሽ ጉታ እንደገለፁት መንግስት ለችግራቸው ትኩረት በመስጠት የሚያካሄደው የጤና ተቋማት ግንባታ የወደፊት ህይወታቸውን የሚያለመልም በመሆኑ ደሰታቸውን ገልፀዋል ።
|
|
|
|
|
|
|
|
|
|
|
|
|
|
|