ENA


ሞዴል የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቪሽንና ባዛር ይከፈታል

  አዲስ አበባ ጥር 23/2005 በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ለ4ኛ ጊዜ የሚዘጋጀው ሞዴል የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቪሽንና ባዛር በመጪው ቅዳሜ ይከፈታል፡፡ '' የተቀናጀ የገበያ ልማትና ትስስር ለኢንተርፕራይዞች እድገት ቁልፍ ሚና አላቸው '' በሚል መሪ ቃል የሚዘጋጀው ኤግዚቪሽንና ባዛር ላይ አዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ጨምሮ አብዛኛው ክልሎች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ የፌዴራል የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት አስተባባሪ አቶ አሰፋ ፈረደ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የኤግዚቪሽኑ ዋና ዓላማ የዘርፉን ምርቶች ለኀብረተሰቡ ለማስተዋወቅ፣ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ገበያ ዕድልን ማመቻቸት ነው፡፡ በዘርፉ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞችን ለፈጠራ ሥራዎቻቸው የሚያግዙ መረጃዎችን የሚያሰባስቡበት መድረክ ፣ የምርጥ ተሞክሮ ልውውጥ እና የእርስ በእርስ ትውውቅ የሚፈጥሩበት መድረክ ለመፍጠር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም በየደረጃው ያሉ የክልል ከተሞች ተመሳሳይ ኤግዚቪሽንና ባዛሮችን የማዘጋጀት ተነሳሽነትና ተሞክሮ እንዲያገኙ ማድረግ ተጠቃሽ ተግባራቶች መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡ በኤግዚቪሽኑ ላይ የጨርቃ ጨርቅ አልባሣት፣ የእንጨትና ብረታ ብረት፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ የምግብ ዝግጅት፣ የእደ ጥበብ ውጤቶች፣ የፈጠራ ስራዎች፣ በከተማ ግብርና ውጤቶች እና በአገልግሎት ዘርፎች የሚቀርቡ የጥቃቅን አነስተኛ ምርትና አገልግሎት ይጎበኛሉ፡፡ ኤግዚቪሽንና ባዛሩን አስመልክቶ የመገናኛ ብዙሃን ኀብረተሰቡ በቂ መረጃዎችን በማግኘት ምርቶቹን እንዲጎበኝ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ዋና አስተባባሪው አስታውቀዋል፡፡ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ለሀገሪቷ አስተማማኝና ሰፊ መሰረት ያላቸው ተወዳዳሪ የዘርፉ ኢንተርፕራይዞች የመፍጠር ራዕይ ዓለው ብለዋል፡፡ ኤጀንሲው በሚያዘጋጀው ኤግዚቪሽንና ባዛር ላይ ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ 161 የዘርፉ ሞዴል ኢንተርፕራይዞችና ባለድርሻ ተቋማት ይሳተፋሉ፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ለስድስት ቀናት የሚቆየው ኤግዚቪሽንና ባዛር ላይ 15 ሺህ የሚጠጉ የኀብረተሰብ ክፍሎች ይጎበኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅና በዚህም ከአስር ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር ይፈጠራል የሚል ግምት እንዳላቸውም አቶ አሰፋ ገልጸዋል፡፡
 
 
 
 
  Leave Your Comments Here  
Name:  
Email:  
Comment: