በአምቦ ከተማ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ የተገነባ ቤተ መፃህፍት አገልግሎት መስጠት ጀመረ
አምቦ, ጳጉሜን 3 ቀን 2002 (አምቦ) - በአምቦ መሰናዶ ትምህርት ቤት ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የቤተ መጻህፍት ህንፃ ዛሬ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡ የምእራብ ሸዋ ዞን ቀይ መስቀል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በአምቦ ከተማ የከፈተው መድሃኒት ቤትም አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡

ተቋማቱን ለአገልግሎት መርቀው የከፈቱት የኦሮሚያ ክልል ኘሬዚዳንት አቶ አባዱላ ገመዳ ናቸው፡፡

የምእራብ ሸዋ ዞን ምከትል አስተዳዳሪ አቶ ሰለሞን ታደለ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት በትምህርት ቤቱ የቀድሞ ተማሪዎች፣ በአካባቢው ህብረተሰብና በመንግስት ትብብር የተገነባው ይኸው ቤተ መፃህፍት በአንድ ጊዜ አንድ ሺህ አንባብያንን የማስተናገድ አቅም አለው፡፡

ህንፃው ከቤተ መፃህፍቱ በተጨማሪ ላቦራቶሪ፣ ካፍቴሪያ፣ ቢሮዎች፣ የመማሪያ ክፍሎች፣ የእቃ ማከማቻና ሌሎችን ጨምሮ ከ40 በላይ ክፍሎችን ያካተተ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ለቤተ መጽሀፍቱ የዉስጥ ድርጅት ማሟያ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሰጥ የክልሉ ፕሬዚዳንት በዚሁ ጊዜ ቃል ገብተዋል ።

በሌላ በኩል ደግሞ በአምቦ ከተማ የተከፈተዉ የቀይ መስቀል መድሀኒት ቤት የህብረተሰብ የረጅም ጊዜ ጥያቄ ምላሽ የሰጠ መሆኑንም ተገልጧል፡፡

የከተማዋ ህብረተሰብና የቀድሞ ተማሪዎች ከመንግስት ጎን በመቆም ያደረጉት ተሳትፎ ለልማት ያለዉን ፍላጎትና ተነሳሽነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጠዉ በቀጣይም የአምስት አመቱን የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ለማሳካት ጥረቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቶ አባዱላ አስገንዝበዋል ።

ሪፖ፡12፡00 ኤዲ2 1፡20-1፡35

---END---

Headlines
በአምቦ ከተማ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ የተገነባ ቤተ መፃህፍት አገልግሎት መስጠት ጀመረ
(c) The Ethiopian News Agency