ኢትዮጵያ ውስጥ ለብሔር ብሔረሰቦች ሙሉ እውቅና የሰጠ ፌዴራላዊ ህገመንግስት በመመሥረቱ የሀገሪቱ አንድነት እንዲጠበቅ ረድቷል
አዲስ አበባ, መጋቢት 6 ቀን 2002 (አዲስ አበባ) -

ኢትዮጵያ ውስጥ ለብሔር ብሔረሰቦች ሙሉ እውቅና የሰጠ ፌዴራላዊ ህገመንግስትና የፖለቲካ ማህበረሰብ በመመሥረቱ ብሔር ብሔረሰቦች ቀደም ሲል የነበራቸውን በጎ ትስስር እና አንድነት ይበልጥ አጠናክረው በታሪክ የተከሰቱ የተዛቡ ግንኙነቶች ዳግም እንዳይከሰቱ የተሟላ ህጋዊና ተቋማዊ ጠበቃ የተበጀ መሆኑን ኢህአዴግን ወክለው የሚወዳደሩት ዕጩ አቶ ሽመልስ ከማል አስታወቁ፡፡

"የፌዴራሊዝም ሥርዓት በኢትዮጵያ ያለው ጠቀሜታ ምንድነው" በሚል ርዕስ የልደታ ክፍለ ከተማ ኢህአዲግ ሊግ ባዘጋጀው ውይይት ላይ በወረዳ ሦስት ኢህአዲግን ወክለው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩት አቶ ሽመልስ የሃገራችን ፌዴራላዊ ስርአት በቀድሞ ስርአቶች ወስጥ የሰፈነው ብሄራዊ ጭቆና ሀገሪቱን የመበታተን ጠርዝ ላይ የገፋትን ያላባራ የእርስ በርስ ጦርነትና የጥፋት ቀውስ ለማስቆም የቻለ መሆኑን ለተሰብሳቢዎቹ ገልፀዋል ፡፡

ሲቀርቡበት የነበሩ መጥፎ ትንቢቶችንና ሟርቶችን መና ቢስነት በተግባር ያረጋገጠው የሃገራችን ፌዴራል ስርአት ባለፉት አስራ አምስት አመታት የሀገሪቷ ብሄር ብሄረሰቦች ራሳቸውን ለማስተዳደር ያላቸውን የተሟላ መብት በማረጋገጥ በፌደራሉ አባል መንግስታት መሀከል በተግባር የተፈተነ የመከባበር፣ የመተማመን፣ የመተጋገዝና የመደጋገፍ መንፈስን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ያጠናከረ የተረጋጋ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ መፍጠሩን አስታውቀዋል፡፡

የፌደራል ስርአቱን የመሰረተው ህገ መንግስትም ተቃዋሚዎች እንደሚሉት ሳይሆን ተቃዋሚዎችን ጨምሮ በርካታ የሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮችን ባሳተፈ የአርቃቂ ኮሚሽን ተረቆና መጠነ ሰፊ የሆነ የህዝብ ውይይትና ምክክር ተደርጎበት ህዝቡ በቀጥታ ምርጫ በመረጣቸው የህገመንግስት ጉባኤ አባላት አማካይነት በህዝቡ ፈቃድና ፍላጎት የፀደቀ መሆኑን አስታውሰዋል ፡፡

ተቃዋሚዎች በቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት እና በምስራቅ አውሮፓ የሶሽያሊስት ጎራ ውስጥ የነበሩና ለውድቀትና ለብተና የተዳረጉ አገሮችን ማስረጃነት በመጥቀስ የፌዴራል ስርአቱን ፋይዳ በማዋደቅ የሚያቀርቡት ወቀሳ የማይነፃፀሩ ጨርሶ የተለያዩ ነገሮችን በማመሳሰል የቀረበ የሸፍጥ ክርክር መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሽመልስ እነዚህ ስርአቶች በአንድ ፓርቲ አምባገነንነት ቀንበር ስር የወደቁ ፣ የመድበለ ፓርቲ ዲሞክራሲ ያልተመሰረተባቸው ፣የአዋቃሪ ክልሎቹን የልማትና የእድገት ተስፋ ያመከኑና ቀድሞውንም ቢሆን በጉልበትና በጫና የተመሰረቱ አስመሳይ ፌዴራል ስርአቶች መሆናቸውን አውስተዋል፡፡

በንፅፅር የሃገራችን ፌደራላዊ ስርአት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመሳሳይ በሆኑ ስርአቶች ውስጥ የሚታዩ የወል ባህርያትን አሟልቶ የያዘ መሆኑን በመግለፅ የብሄሮች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት በአለም አቀፋዊ ህግና ልማዳዊ አሰራሮች ውስጥ እውቅናን የተጎናፀፈ መብት መሆኑንና በመብቱ ላይ የሚፈፀም ጭቆናን ለማስቀረት የመገንጠል አማራጭም በአለም አቀፍ ህግ ተርጓሚ አካላት እውቅና የተሰጠው የመብቱ ገፅታ መሆኑን አብነቶችን በመጥቀስ አብራርተዋል ፡፡

የጦርነት ቀውስን ለማስወገድና ሀገሪቱን ከማያባራ የጦርነት አዘቅት ወስጥ ለማውጣት የነበረው አማራጭ የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ማክበርና ይህን ሊያከብር የሚችል ፌዴራላዊ ሥርዓት መመሥረት አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተለያዩ ሀገራት ፌዴራል መንግሥቱን የፈጠሩ ክልሎች የሚወከሉባቸው አሠራሮች መኖራቸውን ያወሱት አቶ ሽመልስ ረዥም ዘመን ያስቆጠሩ በብሄር ላይ የተመሰረተ ፌዴራላዊ ስርአት ያላቸው አገሮች ተሞክሮ የፌዴራል አወቃቀሮች መገንጠልን በብቃት የማስቀረት ብቃት እንዳላቸው ያረጋግጣል ብለዋል፡፡

ጥያቄው ቢነሳ እንኳን መገንጠልን የማስቀረት ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባህል፣ መዋቅራዊ አሠራርና አደረጃጀት ስላላቸው ግፊቱን በሚገባ ለመመከት እንደሚችሉ የካናዳ ተሞክሮ እንደሚያሳይ ገልፀዋል፡፡

የፌዴራል ሥርዓቶች የመገንጠል ፍላጎትና ግፊት ያላቸው ቡድኖች በሚነሱበት ወቅት ለነዚህ ቡድኖች ጥያቄዎቹን በማፈን ሳይሆን ከመገንጠል ወይም ከመበተን ይልቅ አንድነትን በማጠናከርና አንድነትን አዋቅሮ በመያዝ የሚገኘውን ጥቅም አስመልክቶ ሰፊ የሆነ ሥራ በመሥራት የመገንጠል ጥያቄው እንዲከስም እንደሚያደርጉም አመልክተዋል፡፡

በማህበረሰቡ ውስጥ የተማላ መብት ካለ የመገንጥል አደጋ እንዳማይኖር ጠቁመው ለዚህም የብሄሮች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት የተሟላ ህጋዊና ተቋማዊ ዋስትና የተጎናፀፈበት የጋራ ልማትና ብልፅግናን የሚያረጋግጥ ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታ መፍጠሩ አማራጭ የለውም ብለዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት ከተሳታፊዎቹ ልዩ ልዩ ጥያቄዎች ተነስተው አቶ ሺመልስ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ስ 2፡00 መ 7፡30 ሪ 9፡40-10፡20

---END---

---END---

Headlines
ኢትዮጵያ ውስጥ ለብሔር ብሔረሰቦች ሙሉ እውቅና የሰጠ ፌዴራላዊ ህገመንግስት በመመሥረቱ የሀገሪቱ አንድነት እንዲጠበቅ ረድቷል
(c) The Ethiopian News Agency