አዲስ አበባ, መጋቢት 6 ቀን 2002 (አዲስ አበባ) - ወጣቱ በመጪው ምርጫው ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ዴሞክራሲያዊ መብቱን እንዲጠቀምና ተስፋ ሰጪ ዕድገት እያስመዘገበች ያለችውን የአገሩን ዕድገት እንዲያፋጥን አንድ የቀድሞ ዲፕሎማት አሳሰቡ፡፡
በተለያዩ አገሮች በዲፕሎማትነት ያገለገሉት አቶ ቶማስ ገብረማሪያም ዛሬ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የወጣቶች ፌዴሬሽን ባዘጋጀው ቶክ ሾው ፕሮግራም እንደተናገሩት ወጣቱ በግንቦት ወር በሚካሄደው ምርጫ በንቃት መሳተፍ የዜግነት ግዴታውን መወጣትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል።
አገሪቱ አሁን የደረሰችበት የዴሞክራሲ ሂደት የቀደምት ወጣቶች መስዋዕትነት ወጤት መሆናቸውን አስታውሰው፣በዚህ ላይ በመመስረት የነገዋን ኢትዮጵያ የበለጠ ብሩህ ለማድረግ ወጣቱ በምርጫው ተሳታፊ መሆን ይገባዋል።
በመሆኑም ወጣቶች ይበጀናል የሚሉትን ፓርቲ በሰከነ አዕምሮ አጢነውና ፈትሸው ድምጻቸውን እንዲሰጡ አቶ ቶማስ አሳስበዋል።ወቅቱ ለሰላም ለዴሞክራሲና ለልማት የሚቆምበት እንጂ፤የአመጻና የሁከት እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሚከናወኑት ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች አገሪቱ በተለይም ለወጣቱ ትውልድ ተስፋ ያላት መሆኗን እንደሚያሳይ አመልክተው፣ አገሪቱ በአሁኑ ወቅት በዓለም ፈጣን ዕድገት ካስመዘገቡ አምስት አገሮች አንዷ መሆኗን እኚሁ አንጋፋ ዲፕሎማት ተናግረዋል።
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የወጣቶች ፌዴሬሽን ሰብሳቢ ወጣት ዮርዳኖስ ታደሰ በበኩሉ ወጣቱ የለውጥና የዕድገት ኃይል ከመሆንም አልፎ ተዓምር ሊሰራ እንደሚችል ገልጾ፣ዘንድሮ በሚካሄደው ምርጫ መብቱን ለማስከበር ድምጹን እንዲሰጥ አሳስቧል።
ወጣቱ ኢትዮጵያ በምታካሂደው የልማት አቅጣጫ ላይ የጠራ ግንዛቤ ሊኖረው እንደሚገባም አመልክቷል፡፡
የቶክ ሾው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በአመላካከት ብዥታ ሳቢያ በ1997 ተከስቶ የነበረው ስህተት በዘንድሮው ምርጫ ፈጽሞ እንዳይደገም ጥረት እናደርጋለን ብለዋል፡፡
ፌዴሬሽኑ በወቅታዊ አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት በወጣቱ ዘንድ ለመፍጠር የዛሬውን ጨምሮ የተለያዩ መድረኮች በፌዴሬሽኑ አባል አደረጃጀቶች ሲያዘጋጅ መቆየቱ ተገልጿል፡፡
ስ/2፡30መ/6፡00ሪ/6፡15ያ/6፡46 ተ 7፡30 ጠሰድ 5፡00 ጥከ
---END---