አልማ ዘንድሮ ባደረገው እንቅስቃሴ ከ419 ሚሊዮን ብር በላይ ለመለገስ ቃል ተገባ
አዲስ አበባ, መጋቢት 5 ቀን 2002 (አዲስ አበባ) - የአማራ አቀፍ ልማት ማህበር /አልማ/የክልሉን ልማት ለመደገፍ ዘንድሮ ባደረገው የገቢ ማሰባሰብ እንቅስቃሴ ከ419 ሚሊዮን ብር በላይ ለመለገስ ቃል እንደተገባለት አስታወቀ፡፡

ማህበሩ በቅርቡ በአዲስ አበባና በክልሉ ዋና ከተሞች ‘’ለልማት እንጓዝ’’ በሚል መሪ ቃል የእግር ጉዞ ያካሂዳል፡፡

የአልማ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ሕላዌ ዮሴፍ በኢትዮጵያ ስብሰባ ማዕከል ማህበሩ እስካሁን እያደረገ ስላለው እንቅስቃሴ ለአባላቱ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት ማህበሩ ‘’አልማ 2002 ልማታዊ ኅብረት’’ በሚል የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ዘርግቶ መንቀሳቀስ ከጀመረ ወዲህ ገንዘቡን ለመለገስ ቃል ተገብቷል፡፡

እንዲያም ሆኖ ማህበሩ እስከ ሚያዝያ 10 ቀን 2002 ድረስ ወደ 600 ሚሊዮን በር ገደማ ገቢ ያገኛል ተብሎ ይገመታል ብለዋል፡፡

የክልሉን ልማት ለማፋጠን ማህበሩ በሎተሪ ቲኬት ሽያጭ ረገድ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ አበረታች ቢሆንም የተጠበቀውን ያህል ባለመሆኑ የማህበሩ አባላት ጠንካራ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ሊቀመንበሩ አሳስበዋል፡፡

በቅርቡ ‘’ለልማት እንጓዝ’’ በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው የእግር ጉዞ በአማራ ክልል፣በክልል ዋና ከተሞችና በአዲስ አበባ ይከናወናል፡፡

በጉዞው የአልማ አባላት፣የክልሉ ተወላጆች፣ባለሐብቶችና የልማት አጋሮች የሚሳተፉ ሲሆን፣ የክልሉን ልማት ለመደገፍ የሚያስችል የገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞች እንደሚካሄዱ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡

---END---

Headlines
ወጣቱ በመጪው ምርጫው ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግና አገሩን እንዲያለማ አንድ የቀድሞ ዲፕሎማት አሳሰቡ
አልማ ዘንድሮ ባደረገው እንቅስቃሴ ከ419 ሚሊዮን ብር በላይ ለመለገስ ቃል ተገባ
ደራርቱ በናጎያ ዓለም አቀፍ ማራቶን ሁለተኛ በመውጣት አሸነፈች
(c) The Ethiopian News Agency