በአዲስ አበባ አስተዳደር ውጤት ተኮር አሰራር ሂደት /ባላንስድ ስኮር ካርድ/ ጥናት በመጪው መስከረም በሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች ተግባራዊ ይሆናል
አዲስ አበባ, መጋቢት 4 ቀን 2002 (አዲስ አበባ) -

የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙ አካል የሆነው የአዲስ አበባ አስተዳደር ውጤት ተኮር አሰራር ሂደት/ባላንስድ ስኮር ካርድ/ ጥናት በመጪው መስከረም በሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች ተግባራዊ እንደሚደረግ የአስተዳደሩ ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ አስታወቁ፡፡

የውጤት ተኮር የአሰራር ሥርዓቱ ጥንቃቄና እውቀት የሚጠይቅ በመሆኑ ሁሉም አካላት ጥናቱን በአትኩሮት ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀት እንዳለበትም ከንቲባው አሳስበዋል፡፡

የአስተዳደሩ አቅም ግንባታ ቢሮ የስትራቲጂ ዝግጅትና የባለንስድ ስኮር ካርድ ጥናት ማጠናቀቅን አስመልክቶ ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ የተገኙት ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ እንዳሉት የከተማውን ራዕይና ተልዕኮ እውን ለማድረግ ጥናቱን በጥንቃቄና በጥራት ተግባራዊ ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡

ይህ ጥናትም ከዚህ ቀደም ሥራ ላይ የነበረውን የሲቪል ሰርቪስ መሠረታዊ ችግሮች በማስወገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለው የመሰረታዊ የአሰራር ሂደት ለውጥ ተከታይ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

የውጤት ተኮር አሰራር ሥርዓት የሥራ ሂደቶችን፣የተቋማትን፣የቡድንና የግለሰቦችን የሥራ አፈጻጻም የሚመዝን መሆኑንና

ዋነኛ ትኩረቱም አሰራርን፣የሰዎችን እውቀትና ክህሎት በማሻሻል ብቃት ያለው ተቋም መፍጠር ነው ብለዋል፡፡

እያንዳንዱ የአመራር አባልና ሠራተኛው በየእለቱ ሥርዓቱን ከስትራቴጂው ጋር በማስተሳሰር ሥራውን ማከናወን እንዳለበት የጠቁሙት አቶ ኩማ ይህ ጥናትም በቅርቡ በሙከራ በካቢኔ ደረጃ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል ፡፡

የአዲስ አበባ አስተዳደር አቅም ግንባታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ በበኩላቸው እንዳሉት በጥናቱ በመሰረታዊ አሰራር ሂደት ውስጥ በክፍለ ከተማ ደረጃ ግንባር ቀደም ባለሞያዎችን በመምረጥ እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡

እንዲሁም ለከተማ አስተዳደርና በከተማ ደረጃ የየሴክተሩ ጥናት ለሚያካሂዱ 170 ባለሞያዎችም በተግባር ላይ የተደገፈ ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጎ ወደ ስራው መግባታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተለይም በከተማ ደረጃ የስትራቴጂ ዝግጅትና ውጤት ተኮር የስራ ሂደት ጥናት ትግበራና ዕቅድ በከተማ አስተዳደር ካቢኔ ውይይት ተደርጎ እንዲጸድቅ ከተደረገ በኋላ ጊዚያዊ ኮሚቴና የቴክኒክ አማካሪ እንዲቋቋም ተደርጎ መጀመሩ ስራውን ውጤታማ እንዲሆን አድርጓታል ብለዋል፡፡

በዛሬው ፕሮግራም ላይ በጥናቱ የተሳተፉ ሴክተር መስሪያቤቶች፣ ክፍለ ከተሞችና ልዩ ልዩ አካላት ከከንቲባ ኩማ ደመቅሳና ከምክትል ከንቲባው አቶ ከፍ ያለው አዘዘ ሽልማት ተቀብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ህጻናትና ወጣቶች ቲያትር ቤት አባላት "ለልማት ሰራዊት ነን" የሚል መዝሙር ቀርቧል፡፡

ስ.7.00 የ.11.12 ሪ.11.14 ያ12.46

---END---

Headlines
በሱማሌ ክልል የምርጫ ቁሳቁስ ለማሰራጨት ዝግጅት እየተደረገ ነው
በአዲስ አበባ አስተዳደር ውጤት ተኮር አሰራር ሂደት /ባላንስድ ስኮር ካርድ/ ጥናት በመጪው መስከረም በሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች ተግባራዊ ይሆናል
(c) The Ethiopian News Agency