አዲስ አበባ, መጋቢት 4 ቀን 2002 (አዲስ አበባ) - ምርጫው ነፃ፣ ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና በሕዝብ ዘንድ ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅና የምርጫ አዘጋገብ ሥነ ምግባር ደንብ አክብረው እንደሚሰሩ አንዳንድ የግልና የመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች አስታወቁ።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለግልና ለመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በምርጫ አዘጋገብ ሥነ ምግባር ላይ ለአምስት ቀናት ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ትናንት ሲጠናቀቅ ባለሙያዎቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰጡት አስተያየት በአገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲጎለብት ሙያው በሚፈቅደው ሥነ-ምግባር በመመራት እንሰራለን ብለዋል።
ከሰንደቅ ጋዜጣ የመጣው ጋዜጠኛ ዘርይሁን ሙሉጌታ በሰጠው አስተያየት ካለፈው የምርጫ ልምድ ሲታይ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በምርጫ አዘጋገብ ሥነ ምግባር ላይ ያተኮረ ስልጠና መሰጠቱ እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ ገልጿል።
ከዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል የመጣችው ጋዜጠኛ እፀገነት ተስፋዬ በሰጠችው አስተያየት ስልጠናው ሕብረተሰቡ የምርጫ ዘገባዎችን ትክክለኛ ስለመሆናቸው የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የሚያወጧቸውን መረጃዎች ማመሳከር እንደሚገባው ገልጻለች።
ከዛሚ 90 ነጥብ 7 ኤፍ ኤም የመጣው ጋዜጠኛ ዘሪሁን ግርማ በበኩሉ ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በተለይም ዜጎች ከምንጊዜውም በላይ ጥሩ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያስችል ትምህርት ማግኘቱን ተናግሯል።
ከኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን የመጣው ጋዜጠኛ በሀይሉ ጌታቸው በበኩሉ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በምርጫው ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚያደርጉ ስለሆነ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሥነ ምግባር ላይ ያተኮረ ስልጠና መሰጠቱ ጥሩ እንደሆነ ገልጿል።
ከአፍሮ ኤፍ ኤም 105 ነጥብ 3 የመጣችው ጋዜጠኛ ሊያ ሀይሌ በሰጠችው አስተያየት ደግሞ የምርጫ ዘገባ የራሱ የሆነ ባህርይ ያለው በመሆኑ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ሚዛናዊ ዘገባ ማቅረብ ይገባቸዋል ብላለች።
---END---