አዲስ አበባ, መጋቢት 4 ቀን 2002 (አዲስ አበባ) - በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ወጪ በ168 ነጥብ 74 ሚሊዮን ብር በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሚገነባው የኦሮሚያ ባህል ማዕከል ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ።
በ4 ነጥብ 1 ሄክታር ላይ የሚገነባውን የባህል ማዕከል በየካ ክፍለ ከተማ የሚኖሩ የብሔሩ ተወላጆች ዛሬ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
የባህል ማዕከሉ ዘጠኝ ሕንፃዎች በ2 ነጥብ 7 ሄክታር ላይ የሚገነቡ ሲሆን ግንባታቸው ጥቅምት 26 ቀን 2001 ዓ.ም. የተጀመረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 40 በመቶው ተጠናቋል።
የክፍለ ከተማው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ ጽህፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ አቶ ደረጀ አበራ የጉብኝቱን ዓላማ በተመለከተ እንደተናገሩት በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ለብሔሩ ተወላጆች ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው።
በክልሉ እየተካሄደ ያለው ልማት እንዲፋጠን የብሔሩ ተወላጆች በቀበሌ ደረጃ በማህበር ተደራጅተው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
የባህል ማዕከሉ መገንባት የኦሮሞ ሕዝብ ባህልና ቋንቋ ተጠብቆ እንዲቆይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።
መንግስት ድህነትን ለመቀነስ በሚያደርገው ርብርብ የክልሉ ተወላጆች በልማቱ ተሳታፊ በመሆን የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበዋል።
የክልሉ ተወላጆች በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያን በአጭር ጊዜ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ በሚደረገው ርብርብ መንግስት ጎን በመቆም የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ገልጸዋል።
በጉብኝቱ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የባህል ማዕከሉ ሙዚየም፣ ቲያትር ቤት፣ ቤተ መጽሐፍት፣ የቋንቋ አካዳሚና ወመዘክር፣ የስብሰባ አዳራሽና ሬስቶራንት አካቷል። እንዲሁም እስከ 400 ተሽከርካሪዎች የሚያስተናግድ የመኪና ማቆሚያ ስፍራ አለው። ግንባታው በ14 ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
---END---