አዲስ አበባ, የካቲት 22 ቀን 2002 (አዲስ አበባ) - የመድረክ አባላት የነበሩት የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ /ኢዴአን/ እና የሶማሌ ዲሞክራሲ ኃይሎች ቅንጅት /ሶዴኃቅ/ አንድነት የተባለው ፓርቲ ያደርስብናል ባሉት ጫና የተነሳ ከመድረክ መውጣታቸውን አስታወቁ፡፡የመድረክ አባል የሆነው የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ /ኢዴአን/ ከአንድነት ፓርቲ በተለይ በዕጭዎች አቀራረብ ላይ አደረሰብን ባለው ተጽዕኖ የተነሳ ራሱን በጊዜያዊነት ከአባልነት ማገዱን የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ጉዕሽ ገብረሥላሴ አስታውቀዋል፡፡
የፓርቲው ሊቀመንበር እንደገለጹት ኢዴአን የራሱ የሆነ ፕሮግራም ቢኖረውም በቅንጅት መታገል መርጦ ከመድረኩ ተቀላቅሏል፡፡ይሁንና አንድነት ፓርቲ በተደጋጋሚ በኢዴአን ላይ ጫና ስለፈጠረብንና በሌሎች ፓርቲዎች ቢመከርም ሊመለስ ስላልቻለ ለጊዜው ከመድረኩ ወጥተናል ብለዋል- ለኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቬዥን ድርጅት (ኢሬቴድ)።።
የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ቅንጅት ሶዴኃቅ ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር አህመድ ናስር ሃሰን በበኩላቸው የምርጫውን መቅረብ ተከትሎ በመድረክ ውስጥ የምርጫ ጣቢያዎችን የመቀራመት ችግር ተከስቷል ነው ያሉት፡፡
በተለይ የአንድነት ፓርቲ ጫና ስላበዛብንና በአዲስ አበባ በአንድም ጣቢያ እንዳንወዳደር ስለተደረግን በመድረክ ውስጥ የመቀጠል ፍላጎት የለንም ብለዋል፡፡
ስለሆነም የመድረክን ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ አቋርጠው መውጣታቸውን እንደገለጹ ኢሬቴድን ጠቅሶ የኢትዮጵያ ዜና አገልገሎት ዘግቧል፡፡
---END---