የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ ሰበሰበ
አዲስ አበባ, ሐምሌ 21 ቀን 2002 (አዲስ አበባ) - የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተጠናቀቀው የ2002 በጀት ዓመት ከታክስ ነክ፣ ታክስ ካልሆኑና ከማዘጋጃ ቤት የገቢ ርዕሶች 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡

አስተዳደሩ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጸው የተሰበሰበው ገቢ በዓመቱ ለመሰበሰብ ከታቀደው 5 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ውስጥ ከ84 በመቶ በላዩን አሳክቷል፡፡

የከተማው አስተዳደር ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ በላይ ታፈሰ እንደገለጹት ከገቢው ውስጥ ታክስ ነክ ገቢ ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡

ቀጥተኛና ቀጥተኛ ካልሆኑ ታክስ ገቢዎች በዓመቱ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ተችሏል፡፡

አዳዲስና ነባር የመሬት ሊዝን ከሚያካትተው ታክስ ያልሆነ ገቢም ከታቀደው 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ውስጥ የተሰበሰበው 753 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገለጻ ከማዘጋጃ ቤት ነክ ገቢ 900 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 653 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ተችሏል፡፡

በተጠናቀቀው የ2002 በጀት ዓመት የተሰበሰበው ገቢ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው፡፡

ለገቢው ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱት የመሠረታዊ የሥራ ሂደት ለውጥ ትግበራ፣ የመረጃ ሥርዓቱ መጠናከር፣ ለባለሙያዎች፣ ለሠራተኞችና ለግብር ከፋዮች የተሰጡ ሥልጠናዎችና የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በወቅቱ ለመክፈል ያሳዩት ተነሳሽነትና ለባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በሚሰጧቸው አስተያየቶች አማካኝነት እርምት በመውሰድ የተጠናከረ ሥራ መሰራቱ፣ የግብር ሕጎች ተግባራዊ መደረጋቸውና ውዝፍ ግብሮችም መከፈላቸው ለገቢው ማደግ በምክንያትነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ለከተማዋ ዕድገት ዋነኛ አንቀሳቃሽ ከሆነው ታክስ ከዚህ በላይ ገቢ መሰብሰብ ስላለበት በሚቀጥሉት ዓመታት የታክስ አስተዳደር ሥርዓቱን በማጠናከር የበለጠ ገቢ እንደሚሰበሰብ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

በ2003 በጀት ዓመት ጠንካራ አሰራሮችን የበለጠ በማጠናከር 9 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱንም ይፋ አድርገዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ 5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ የታቀደው ከታክስ ነክ ገቢ እንደሆነ ለአስተዳደሩን ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ሪ እና ኤ ከ10፡00 - 10፡17 ጠሰድ 0፡17

---END---

Headlines
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ ሰበሰበ
የሐረር ንጹህ መጠጥ ዉሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት በከፊል ስራ ጀመረ
(c) The Ethiopian News Agency