አዲስ አበባ, ሐምሌ 21 ቀን 2002 (አዲስ አበባ) - የሐረር ከተማን የንጹህ መጠጥ ዉሃ ፍላጎት ሙሉ በሙሉ የሚቀርፈው የሃረር ንጹህ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት 99 ከመቶ ተጠናቆ በከፊል ስራ ጀመረ፡፡
የሐረሬ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙራድ አብድል ሀዲ ለኢትዮጵያ ዜና እንደገለጹት በፌዴራል መንግስት በባለቤትነት ግንባታዉ የተከናወነው ይኽው ፕሮጀክት ካሉት አራቱ ፓንቦች አንዱ ስራ ጀምሯል፡፡
ሁሉንም ፓንፖቹን ሙሉ በሙሉ ለማስነሳት የሚያስችል የኤሊከትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ወይንም ትራንስፎርመር ችግር በማጋጠሙ ምክንያት ሁሉንም ፓንፖቹን ስራ ማስጀመር አለመቻሉን ጠቁመው ይህንን ችግር አስወግዶ በቅርብ ቀን ስራ ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የሐሮማያ ሀይቅ መድረቅን ተከትሎ የሐረር ከተማ ህዝብ ለንጹህ መጠጥ ዉሃ ችግር ተጋልጦ መቆየቱን የተቆሙት ርዕሰ መስተዳደሩ የክልሉ መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ የአስቸኳይ ጊዜ ጉድጓዶችን በመቆፈር የንጹህ መጠጥ ዉሃ አቅርቦት አቅሙን ቢያሳድግም ለረጅም ዓመታት የህዝቡ የንጹህ መጠጥ ዉሃ ችግር ሳይቀረፍ ቆይቷል።
ከአሁን ቀደም የከተማዉ ኗሪ በ15 ቀን አንድ ቀን ዉሃ የሚያገኝበት ሁኔታ እንደነበር አቶ ሙራድ አመልክተው የነበረዉ የዉሃ ችግር ለከተማዋ እድገት እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል።
በከተማዋ የሚካሄዱ የግንባታ ስራዎች በቦቴ በሚመጣ ዉሃ ሲከናወን መቆየቱንና በቂ ዉሃ አለመኖሩ በኢንቨስትመንት ስራ ላይ እንቅፋት እንደነበር ርዕሰ መስተዳደሩ ጨምረዉ ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምር በአሁኑ ጊዜ በከተማው ያለዉን ዝቅተኛ የዉሃ አቅርቦት ሙሉ በሙሉ በመፍታት ነዋሪዎቹን የ24 ሰዓት የንጹህ መጠጥ ዉሃ ተጠቃሚ ያደርጋል።
የዉሃ ሃብት ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ አዱኛ ጀቤሳ በበኩላቸዉ ፕሮጀክቱ ከአፍሪካ ልማት ባንክና ከኢትዮጵያ መንግስት በተገኘ ገንዘብ መከናወኑን አስታዉቀዉ ለፕሮጀክቱ ዉጤታማነት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተቢዉን ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን አስረድተዋል።
ከሐምሌ 10 ቀን 2002 ዓ.ም ጀምሮ ፕሮጀክቱ በከፊል ስራ መጀመሩን የገለጹት ሚኒስቴር ዴታዉ ይህም ሙሉ በሙሉ ስራ ሲጀምር የከተማዋን ነዋሪዎችም ሆነ ፕሮጀክቱ አቋርጦ በሚሄድባቸዉ አካባቢዎች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።
ደረጃዉን የጠበቀ የንጹህ መጠጥ ዉሃ ማግኘት መቻሉን ጠቁመው ይህም ጤናዉ የተጠበቀ ህብረተስብ ለመፍጠር ለሚደረገዉ ጥረት አጋዥ መሳሪያ ነዉ ብለዋል።
የክልሉ መንግስትም ሆነ ህብረተሰቡ ለፕሮጀክቱ ዉጤታማነት የበኩላቸዉን ድርሻ እንደተወጡ ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ ስራዎችም ይኽው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
በምዕተ አመቱ የልማት ግብ ላይ የተቀመጠዉን 70 በመቶ የንጽህ መጠጥ ዉሃ ሽፋን ኢትዮጵያ ከተባለዉ ጊዜ ቀድማ እንደምታሳካ ሚኒስቴር ዴኤታዉ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ 10 አመታት የፈጀ ሲሆን ከ400 ሚሊዮን ብር ያህል ወጪ መደረጉም ታውቋል፡፡
ሁላ ሁሉል ከሚባል አካባቢ በመነሳት ከ70 ኪ.ሜ በላይ የሚያቋርጠዉ የሐረር ንጹህ መጠጥ ዉሃ ሳኒቴሽን ፕሮጀክት በአገሪቱ የንጹህ መጠጥ ዉሃ ታሪክ በትልቅነቱ የመጀመሪያዉ ፕሮጀክት መሆኑን ሰሞኑን በስፍራው የነበረው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር ዘግቧል።
የ 8.30
ያ 9 .30---END---