አዲስ አበባ, ሐምሌ 21 ቀን 2002 (አዲስ አበባ) -ኢትዮጵያ ባለሃብቶች በሻይ ቅጠል ልማት ለመሰማራት የሚችሉበት ከስድስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬትና አመቺ ሁኔታ እንዳላት የግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከሚኒስቴሩ ያገኘው መረጃ እንዳመለከተው ኢትዮጵያ ባለሃብቶች በዘርፉ ተሰማርተው ቅጠሉን ሊያለሙ የሚችሉበት ሰፊ መሬት፣ተስማሚ የአየር ንብረትና የሰው ሃብት አላት፡፡
ለልማቱ የሚሆነው መሬት በኦሮሚያ፣በደቡብ፣በጋምቤላና በአማራ ክልሎች በስፋት እንደሚገኝም ገልጿል፡፡
የአገሪቱ የደጋ ሻይ ጣዕም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተፈላጊነትና ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
በአገሪቱ በአሁኑ ጊዜ በሻይ ቅጠል የለማው መሬት 2 ሺህ 700 ሄክታር መሬት ብቻ መሆኑንና ከዚህም የሚገኘው ዓመታዊ ምርት ከሰባት ሺህ ቶን እንደማይበልጥ አመልክቷል።
ኢትዮጵያ ሻይ ጠጪ አገሮች በቅርበት በሚገኙበት ስትራቴጂ ክልል የምትገኝ አገር መሆኗም ገበያውን አስተማማኝ ያደርገዋል ብሏል፡፡
ይህንን መሠረት በማድረግም ሚኒስቴሩ ባዘጋጀው የሻይ ቅጠል ልማት ቢዝነስ ዕቅድ ባለሃብቶች ሰባት ሺህ ሄክታር በሚደርስ መሬት ላይ ልማቱን እያካሄዱ መሆናቸውንም የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
---END---