ደብረ ታቦር, ሐምሌ 21 ቀን 2002 (ደብረ ታቦር) - በደቡብ ጎንደር ዞን አራት ወረዳዎች በመኽር አዝመራ ከ26ሺህ 531 ሄክታር ባላይ መሬት ታርሶ በሩዝ ሰብል እየለማ መሆኑን የዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት ጽህፈት ቤት ገለጠ፡፡በጽህፈት ቤቱ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ቴዎድሮስ ተስፋዩ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት የሩዝ ልማቱ እየተካሄደ ያለው በደራ ፣በፎገራ፣በወረታና ሊሞ ከምከም ወረዳ ነው፡፡
በሩዝ ሰብል የተሸፈነው መሬት ካለፈው አመት በ4ሺህ 150 ሄክታር መሬት ብልጫ እንዳለው ገልጠው ብልጫ ያለው መሬት የለማው አዳዲስ መሬት በመታረሱና ሩዝ ከሌሎች ሰብሎች በዋጋ የተሻለና በሄክታር ከፍተኛ ምርት ስለሚሰጥ በመሆኑ የአርሶ አደሩ ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ ነው ብለዋል፡፡
በመኽር አዝመራ በሩዝ ልማት ከ40ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮች ተሰታፊ መሆናቸውን ገልጠው ሩዝ በአራቱ ወረዳዎች በሄክታር ከ65 እስከ 70 ኩንታል ምርት የሚሰጥና በአንዳንድ ቦታዎች ጥሩ ክብካቤ ከተደረገት በሄክታር እስከ 100 ኩንታል ምርት እንደሚያስገኝ አስታውቀዋል፡፡
በሌሎች አካባቢዎች ሩዝ ለማምረት ማዳበሪያ የመጠቀም ልምድ መኖሩን የገለፁት አቶ ቴዎድሮስ እነዚህ አካባቢዎች ግን ውሀ ስለሚተኛባቸውና አፈሩም ለም በመሆኑ ምንም አይነት ማዳበሪያ እንደማያስፈልጋቸው አስታውቀዋል።
ሩዝ ለእንጀራ፣ ለዳቦ፣ ለጠላና ለመሳሰሉ የምግብ አይነቶች እንደሚውል ገልጠው የሩዝ ገለባ ደግሞ ለማገዶ፣ለቤት መስሪያ ስለሚውል ለአርሶ አደሩ ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥ ሰብል እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ከመኽሩ የሩዝ ልማት አንድ ሚሊዩን 724ሺህ 515 ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀው የዝናቡ ስርጭት የተሻለ በመሆኑ ምርቱ ከዚህ ይበልጣል ተብሎ እንደሚገመት ገልጠዋል፡፡
ሪፖ6፣00 ኤዲ2 9፣40 9፣50 ጠሰድ10ደ ጥመ
---END---