አዲስ አበባ, ሐምሌ 21 ቀን 2002 (አዲስ አበባ) - አፍሪካ የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች ከግብ ለማድረስ በእናቶችና ሕጻናት ጤና ትኩረት ሰጥታ መሥራት እንደሚገባት የአፍሪካ ኅብረት 15ኛው የመሪዎች ጉባዔ ተሳታፊዎች ገለጹ።በካምፓላ፣ዑጋንዳ ሰሞኑን የተካሄደው ጉባዔ ተካፋዮች እንዳመለከቱት በአህጉሩ የእናቶችና ሕጻናት ሞትን ለመቀነስ በተደረገው ርብርብ የተገኘው ውጤት ከፍተኛ ውጤት ቢገኝም፤ውጤቱ የሚያኩራራ ባለመሆኑ ብዙ መሥራት ያስፈልጋል።
በአህጉሩ ከ16 ነፍሰ ጡሮች አንዷ በእርግዝና ወይም በወሊድ ወቅት ለሞት አደጋ የምትጋለጥበት ሁኔታ መለወጥ እንዳለበትም ተናግረዋል።
በአፍሪካ በየቀኑ 12ሺህ የሚሆኑ ሕጻናትም በቀላሉ ሊድኑ በሚችሉ በሽታዎች የሚሞቱበት ሁኔታ መቀየር እንደሚገባውም ተሳታፊዎቹ አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በጉባዔው ላይ እንደገለጹት የእናቶችና የሕጻናት ጤና አገልግሎትን በተመለከተ ያለው ችግር በአብዛኛው አገልግሎቱን ለማስፋፋት ከሚያስፈልገው ሀብት ውስን መሆን ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልጸዋል።
የአፍሪካ አገሮች ለጤና አገልግሎት ማስፋፊያ የሚያውሉት ሀብት አጠቃቀም ፍትሃዊ አለመሆንና ለጋሾች ለመስጠት ቃል የሚገቡት ሃብት በፍጥነትና ውጤታማ በሆነ መልኩ አለማቅረባቸውም ሌሎቹ ችግሮች መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በአህጉሪቱ ለጤና አገልግሎት የሚውለውን የሃብት እጥረትን ለማቃለል ዋንኛው መፍትሔ ልማትን ማፋጠን እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር አስታውቀዋል።
የሃብት አጠቃቀምን ፍትሃዊ በማድረግና ሥራውን በተለይ ሴቶችን ባሳተፈ መልኩ በመተግበር የእናቶችና ሕጻናት ጤና አገልግሎትን ለማሻሻል እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
የጤና አገልግሎቱ በተቻለ መጠን ባለው ሃብት፣ በተሻለ ጥረትና በዝቅተኛ ዋጋ ለማቅረብ መረባረብ ሌላው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል ማለታቸውን የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅትን(ኢሬቴድ)ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።
የዩጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በበኩላቸው የችግሩ ዋንኛ መፍትሄ በተለይ በመሠረተ ልማት አውታሮች ላይ ያተኮረ የተፋጠነ ልማት ማስመዝገብ መሆኑን ገልጸዋል።
የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር የማላዊ ፕሬዚዳንት ቢንግዋ ሙታሪካ በጉባዔው ማጠናቀቂያ ባደረጉት ንግግር አፍሪካን ከበሽታ፣ ከጦርነት፣ ከድህነትና ከሌሎች ችግሮች የፀዳች ለማድረግ ሁላችንም እንረባረብ በማለት ጥሪ አድርገዋል።
አፍሪካ የራሷን ችግር በራሷ መፍታት የምትችል አህጉር መሆኗን የተባበሩት መንግሥታትም ሆነ ሌሎች አካላት ሊገነዘቡት ያሉት ሙታሪካ፣ በሱዳን ያለውን ችግር ለመፍታት የአጠቃላይ የሠላም ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆን እድል ያስፈልጋል ብለዋል።
የሱዳኑን ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽርን ዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በቁጥጥር ሥር ለማዋል ያሳለፈው ውሳኔ ትክክለኛ አለመሆኑንም መግለጻቸውን ኢሬቴድን ጠቅሶ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
---END---