የኔፓድ መሰረታዊ ሰነዶች አፍሪካ ካደጉ አገራት ጋር በሚኖራት ግንኙነት ላይ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የትብብር ዘርፎች ለመለየት ትኩረት ሰጥቷል
አዲስ አበባ, ሐምሌ 21 ቀን 2002 (አዲስ አበባ) - የአፍሪካ ልማት አዲስ አጋርነት /ኔፓድ/ መሰረታዊ ሰነዶች አህጉሪቱ ከበለጸጉ አገራት ጋር የሚኖራትን ግንኙነት ውጤታማ ለማድረግ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የትብብር ዘርፎችን ለመለየት ትኩረት የሰጠ መሆኑ ተመለከተ፡፡

በኡጋንዳ ካምፓላ በተካሄደው 23ኛው የኔፓድ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተሰራጨው መረጃ መሰረተ ልማት፣ የሰው ኃይል ልማት፣ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የምሁራን ፍልሰትን መከላከል፣ ባደጉ አገራት ለአፍሪካ ምርቶች ከፍተኛ ገበያ እንዲፈጠር ማድረግ እና የውጪ ቀጥታ ኢንቨሰትመንትን መሳብ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ዘርፎች እንደሆኑ ይፋ አድርጓል።

የኔፓድ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የመሪዎቹን ጉባኤ በንግግር ሲከፍቱ እንዳሉት የኔፓድ እየተጠናከረ መሄድ በነዚህ ዘርፎች እየተካሄዱ ያሉ ትብብሮችን ውጤታማነት እያሳደገ ነው፡፡

ኔፓድን በአፍሪካ ህብረት ውስጥ በማዋሃድ በተቀናጀ መልኩ ለመንቀሳቀስ እየተካሄደ ያለው ተግባር ውጤታማ በሆነ መልኩ ከተጠናቀቀ አፍሪካን የአለም ኢኮኖሚ መዘውር አካል ለማድረግ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ሲሉ መግለጻቸውን ኢዜአ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅትን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የማላዊው ፕሬዚዳንት ቢንጉዋ ሙታሪካ በበኩላቸው ኔፓድን በአፍሪካ ህብረት ውስጥ በማዋሃድ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የመሰረተ ልማት አውታሮችን በማስፋፋት ድህነትን ለማስወገድ የሚያስችል ጠንካራ አቅም ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አፍሪካ የጀመረችውን ጥረት ስኬታማ ለማድረግም በቀጣዮቹ አምስትና አስር ዓመታት ጊዜ ውስጥ እውን ለማድረግ ከያዘችው ራእይ ጋር በተጣጣመ ሁኔታ መንቀሳቀስ ይገባል ብለዋል፡፡

በመሪዎቹ ጉባኤ ላይ የተገኙት የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ጎርደን ብራውን አፍሪካ በአለም አቀፉ ኢኮኖሚያዊ እንቅሰቃሴ ተጠቃሚ ብቻ ሳትሆን ዋነኛ ተዋናይ ጭምር መሆኗ በግልጽ መታየት መጀመሩን መስክረዋል፡፡

አህጉሪቱ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ብቻ ያስመዘገበችው እድገት በአንድ ምእት አመት ጊዜ ውስጥ ያልታየ ውጤት ነው ብለዋል፡፡

ጎርደን ብራውን እንደተናገሩት ማንኛውም አለም አቀፍ መድረክ ውጤታማ እንዲሆን ካስፈለገ የአፍሪካን ውክልናና ሃሳብ ከግንዛቤ ውስጥ መግባቱን ማረጋጋጥ ያስፈልጋል፡፡

---END---

Headlines
የኔፓድ መሰረታዊ ሰነዶች አፍሪካ ካደጉ አገራት ጋር በሚኖራት ግንኙነት ላይ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የትብብር ዘርፎች ለመለየት ትኩረት ሰጥቷል
አፍሪካ የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች ከግብ ለማድረስ ለእናቶችና ሕጻናት ጤና ትኩረት ሰጥታ መሥራት አለባት
የትምህርት ልማት ፓኬጅ ውጤት እያስመዘገበ ነው
ኢትዮጵያ ባለሀብቶች የሻይ ቅጠል ሊያለሙበት የሚችል 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት አላት
(c) The Ethiopian News Agency