ሊቀመንበሩ ከረጅም ጊዜ መንገላታትና ስቃይ በኋላ በአጋቾች በተገደለው ፈረንሳዊ ሞት ማዘናቸውን ገለጹ
አዲስ አበባ, ሐምሌ 21 ቀን 2002 (አዲስ አበባ) - የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ከረጅም ጊዜ መንገላታትና ስቃይ በኋላ በአጋቾች በተገደለው ፈረንሳዊ ሞት ኀዘናቸውን ገለጹ።በሳህል-ሳህራ አካባቢ እያቆጠቆጠ ያለውን አሸባሪነት ለመግታት የተጠናከረ ጥረት እንደሚደረግም አረጋገጡ።

ኅብረቱ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ ሊቀመንበሩ ዶክተር ዤን ፒንግ በአጋቾች እጅ ለበርካታ ወራት ቆይቶ ሕይወቱን ባጣው ፈረንሳዊ ሞት የተሰማቸውን ኀዘን ለሟቹ ቤተሰቦችና ለፈረንሳይ መንግሥት ገልጸዋል።

በሳህል-ሳህራ አካባቢ የሚገኙ አገሮች ጸረ ሽብር እንቅሰቃሴያቸውን በግልና በጋራ ጥረት ማድረግ ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን በማንኛውም መልኩ የሚካሄዱ የሽብር ተግባራትን እንደሚያወግዝና ለዚህም ጠንካራና ዘላቂ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑንም ሊቀመንበሩ አረጋግጠዋል።

የአፍሪካ መንግሥታት በሙሉ ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጋር በመቀናጀት ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የሚያደርጉትን ትግል በእጥፍ ማሳደግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

የኮሚሽኑ አካላት አሸባሪነትን ለመከላከል በአባል አገሮች መካከል መረዳዳት የሚጠናከርበት አሰራር ለመዘርጋት ዝግጁ መሆናቸውንም ዶክተር ፒንግ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

---END---

Headlines
ሊቀመንበሩ ከረጅም ጊዜ መንገላታትና ስቃይ በኋላ በአጋቾች በተገደለው ፈረንሳዊ ሞት ማዘናቸውን ገለጹ
(c) The Ethiopian News Agency