አዲስ አበባ, ታህሳስ 25 ቀን 2002 (አዲስ አበባ) -የጥሩነሽ ቤጂንግ ዘመናዊ ሆስፒታል ግንባታ 25 ከመቶ መከናወኑን የአዲስ አበባ አስተዳደር ጤና ቢሮ አስታወቀ።የጤና ቢሮው ተወካይ አቶ ወንድሙ ደንቡ ትናንት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማው እየተገነባ ያለው የሆስፒታሉ ግንባታ በመፋጠን ላይ ነው፡፡
የሆስፒታሉ የመሰረት ግንባታ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ቀሪው ግንባታ በጥሩ ሁኔታ በተፋጠነ ሁኔታ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
በሕዝባዊት ቻይና መንግሥት ወጪው ሙሉ በሙሉ የሚሸፈነው
የሆስፒታሉን ግንባታን በ19 ወራት ለማጠናቀቅ የታቀደ ቢሆንም፤የሥራ ተቋራጩ ግንባታውን ቀድሞ ለማጠናቀቅ ከቀን ከሌሊት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
የሆስፒታሉ ግንባታ በዚህ አኳኋን ከቀጠለ ከተያዘለት የጊዜ ገደብ ቀድሞ ግንባታው ይጠናቀቃል የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ ወንድሙ ተናግረዋል፡፡
የሆስፒታሉ ግንባታ ሲጠናቀቅም ቻይናውያን የሕክምና ባለሙያዎች በሆስፒታሉ እንዲያገለግሉ ስምምነት ተደርሷል፡፡
የሆስፒታሉ መገንባት በኢትዮጵያና በቻይና መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ እየተጠናከረ መምጣቱን እንደሚያመለክትም ተወካዩ ገልጸዋል፡፡
በተለይ እናቶች በወሊድ ጊዜ የሚገጥማቸውን የተወሳሰበ ችግር ለማቃለል ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ የታመነበት ይህ ሆስፒታል፣ ወላዶች ለከፍተኛ ሕክምና ራቅ ወዳሉ ሌሎች ሆስፒታሎች ለመሄድ ይገደዱ የነበረበትን ሁኔታ ለማስቀረት ያስችላል ብለዋል፡፡
ግንባታውን በማከናወን ላይ ያለው ጂያንግ ሺ ኮርፖሬሽን የፕሮጄክት ሥራ አስኪያጅ ታንግ ዊ የጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል
ግንባታ ሲጠናቀቅ የተመላላሽና ተኝተው የሚታከሙ ሕሙማን የሚስተናገዱባቸው የሕክምና ክፍሎችና የሠራተኞች መኖሪያ ይኖሩታል፡፡
በተጨማሪም ሲቲ ስካን ጨምሮ ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎች በቻይና መንግሥት ይሟሉለታል፡፡
የሆስፒታሉ ስያሜ በጀግናዋ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባና በቤጂንግ መሰየሙ ሆስፒታሉ ታሪካዊ እንደሚያደርገው ሚስተር ታንግ ተናግረዋል፡፡
ይህም በኢትዮጵያና በቻይና መካከል ያለውን የሕዝብ ለሕዝብ ወዳጅነት ያጎብለተዋል ብለዋል፡፡
የሆስፒታሉ ግንባታ ሲጠናቀቅ በክፍለ ከተማው የመጀመሪያ የመንግሥት ሆስፒታል ያደርገዋል፡፡
ይኸው ሆስፒታል አንድ ሚሊዮን ለሚሆን የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማና የኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ ለሌሎች አጎራባች ክፍለ ከተሞች ሕዝብ አገልግሎት እንደሚሰጥም የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው፡፡
---END---