ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በአፍሪካ የአሜሪካ ወታደራዊ ዕዝ አዛዥን ተቀብለው አነጋገሩ
አዲስ አበባ, የካቲት 2 ቀን 2002 (አዲስ አበባ) - ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአፍሪካ የአሜሪካ ወታደራዊ ዕዝ አዛዥን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በአፍሪካ የአሜሪካ ወታደራዊ ዕዝ አዛዥ ጀኔራል ዊሊያም ዋርድን ባነጋገሩበት ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባጋጠመው አደጋ አሜሪካ ላደረገችው ድጋፍና ትብብር አመስግነዋል፡፡

በአሜሪካ የተደረገው ድጋፍና ትብብር ከአንድ ወዳጅ አገርና ሕዝብ የሚጠበቅ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስና ጀኔራል ዋርድ በአህጉራዊና ቀጠናዊ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን ውይይቱን የተከታተሉ አንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ኃላፊ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የሱዳንና የሶማሊያን ወቅታዊ ሁኔታ በሚመለከት ለአዛዡ ማብራሪያ ሰጥተዋቸዋል፡፡

በተለይ የተጀመረው የሱዳን የሠላም ሂደት ተጠናክሮ መቀጠል በሚችልበት ሁኔታና አሜሪካ መጫወት ስለሚኖርባት ሚናም ለጀኔራሉ ገለፃ አድርገዉላቸዋል፡፡

የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት በአገሪቱ ሠላምና መረጋጋት ለማስፈን ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አስረድተዋል፡፡

በሶማሊያ ዘላቂ ሠላም ለማስፈን የሽግግሩን መንግሥት ከመርዳት ውጭ ሌላ አማራጭ አለመኖሩንም ገልጸዋል፡፡

ጀኔራል ዋርድ በበኩላቸው በቅርቡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በደረሰው አደጋ በእጅጉ ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡

የአሜሪካ መንግሥት የአደጋው ሰለባዎችን ለማፈላለግና የአደጋውን መንስኤ ለመለየት ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዉላቸዋል፡፡

በእስካሁኑ ሂደትም የአደጋውን ሁኔታ ፍንጭ መስጠት የሚያስችል መረጃ ማግኘት እንደተቻለ አመልክተዋል፡፡

ጀኔራሉ በቆይታቸው ስለ አፍሪካ በአጠቃላይ በተለይ ደግሞ ስለ አፍሪካ ቀንድ የፀጥታና ደህንነት ጉዳይ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጋር ገንቢ ውይይት ማካሄዳቸውን ለጋዜጠኞች ገልጸዋል፡፡

በዚሁ ወቅት ጀነራሉ በአፍሪካ ቀንድ ሠላምና መረጋጋትን ለማምጣት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቃሚ ሃሳቦችን ማግኘታቸውን አመልክተዋል፡፡

በቀጣናው የሚታዩ የሠላም ችግሮችን ለመፍታት ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመሥራት በአፍሪካ የአሜሪካ ወታደራዊ ዕዝ ቁርጠኛ ነው ማለታቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡

---END---

Headlines
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በአፍሪካ የአሜሪካ ወታደራዊ ዕዝ አዛዥን ተቀብለው አነጋገሩ
የኤርትራ መንግስት በሶማሊያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን አሸባሪዎች የማሰልጠንና የማስታጠቅ ሥራውን ቀጥሏል
(c) The Ethiopian News Agency