አዲስ አበባ, የካቲት 2 ቀን 2002 (አዲስ አበባ) - የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዓለም አቀፍ ታዛቢዎች የሥነ ምግባርና የአሰራር መመሪያ አዘጋጀ፡፡የቦርዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና እንደገለጹት ቦርዱ ያዘጋጀው የዓለም አቀፍ ታዛቢዎች መመሪያ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ምርጫ ሕጋዊነት የሚረጋገጠው በአገሪቱ ተቋማት ሕግ እንዲሁም በአገሪቱ ሕዝብ መሆኑን ይገልጻል፡፡
በምርጫ ሂደት ውስጥ የታዛቢዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን የሚያትተው መመሪያ፣ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎችም የምርጫው ሂደት በገለልተኝነትና ተዓማኒነት ባለው መንገድ በመታዘብ የራሳቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት እንዳለባቸው ያስገነዝባል፡፡
ቦርዱ ያዘጋጀው የዓለም አቀፍ ታዛቢዎች የሥነ ምግባር መመሪያም ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችንና ከምርጫ 97 የተገኙ ልምዶችን ማካተቱን አስረድተዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች በመንግሥት ጋባዥነት ሲመጡ የአገሪቱን ሕግና ልዑላዊነት እንዲሁም የምርጫ ቦርድ ሕግን በማክበር እንዲንቀሳቀሱ ለማስቻል መመሪያው መዘጋጀቱ ወሳኝ እንደሆነም ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡
በመመሪያው ላይ ዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢዎች በማን እንደሚጋበዙ፣ ሥራቸውን በምን ሁኔታ እንደሚያካሄዱ፣ በሥራቸው ወቅት ሊከተሏቸው ስለሚገቡት ሕጎች፣ የምርጫውን ሂደት በተመለከተ በምን ሁኔታ አስተያየት እንደሚሰጡና ሌሎች ጉዳዮችን መካተቱንም አስታውቀዋል፡፡
በቦርዱ በተዘጋጀው የዓለም አቀፍ ታዛቢዎች የሥነ ምግባርና የአሰራር መመሪያ ዙሪያ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ጋር ቦርዱ ሰፊ ውይይት አካሂዷል፡፡
በመመሪያው ላይ በቀረቡት ሐሳቦች ላይ ውይይት እንደሚያደርና ሐሳብ እንደሚቀበልም የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅትን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል፡፡
---END---