አዲስ አበባ, የካቲት 2 ቀን 2002 (አዲስ አበባ) ኢትዮጵያ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በየዓመቱ ከዘጠኝ ሺህ በላይ የሴት ምሁራን ለማስመረቅ መቻሏ መንግሥት ለሴቶች ትምህርት የሰጠውን ትኩረት እንደሚያሳይ የትምህርት ሚኒስትሩ አስታወቁ፡፡ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ፉአድ ኢብራሂም ዛሬ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የግንባር ቀደም ሴት መምህራን ውይይት ማጠቃለያ ላይ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በዓመት ከአንድ ሺህ በታች ሴት ምሁራንን ታስመርቅ ከነበረበት ወጥታ ከፍተኛ እመርታ ማስመዝገቧ ለዘርፉ የሰጠችውን ትኩረት አመልካች ነው።
የሴት ተማሪዎችን ቁጥር ከፍ ማድረግና የመንግሥት ፍላጎት መሆኑን ገልጸው፣ ግንባር ቀደም ሴት መምህራን ሴት ተማሪዎች ያሉባቸውን ችግሮች ለማስወገድ በስብሰባው የደረሱበትን ስምምነት ወደ ሥራ ለመተርጎም ሚኒስቴሩ አብሯቸው ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠውላቸዋል፡፡
መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በሚያቀርቡት ጥያቄ መሰረት በዓመት ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ ላይ እንደሚገኝና የበጀቱ አመዳደብም ሥራ ፈላጊ ምሁር ብቻ ከማፍራት ራሱ ሥራ ፈጣሪ የሆነ ዜጋ ለማፍራት በተያዘው |ዕቅድና ስትራቴጂ መሰረት እንደሆነ ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ለሁለት ቀናት በተካሄደው በዚህ ስብሰባ የተካፈሉት 300 ግንባር ቀደም ሴት መምህራን ባወጡት የአቋም መግለጫ መካከል ከወንድ መምህራን አጋሮቻቸው፣ ከወላጆች፣ ከትምህርት ቤት አመራርና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለሴት ተማሪዎች የትምህርት ጠቃሚነትን በማሳወቅ ለሚያጋጥማቸው ችግሮች መፍትሔ እንደሚያፈላልጉ አመልክተዋል፡፡
የስብሰባው ተሳታፊዎች አርአያነታቸውን ለተማሪዎችና ለኅብረተሰቡ በማሳየትና ሌሎች አጋሮቻቸውን ከጎናቸው በማሰለፍ ለሴቶች የትምህርት ተሳትፎ፣ውጤታማነትና እኩልነት እንዲረጋገጥ እንደሚጥሩም ገልጸዋል፡፡
በትምህርት ቤቶች አከባቢ ለመማር ማስተማሩ ሂደት እንቅፋት የሚፈጥሩትን የጫት መቃሚያ፣ የሺሻ፣ የቪዲዮ ማሳያ ቤቶች ለሴት ተማሪዎች ትምህርት መጉላላት እንቅፋት የሚሆኑትን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት በግንባር ቀደምትነት እንደሚታገሉም አረጋግጠዋል፡፡
ከኅብረተሰቡ ግንዛቤ ማነስ በሴቶች ላይ እንደ ባህል ተደርገው የሚፈጸሙ አካላዊና ሥነ ልቡናዊ ተጽእኖ የሚያስከትሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት እንጥራለን ብለዋል፡፡
ልዩ ትኩረት የሚያስፈልጋቸውን ክልሎች የትምህርት ተሳትፎንና ውጤታማነትን ለማጎልበት መንግሥትና ኅብረተሰቡ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በመደገፍና ከጎናቸው በመሰለፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡
ተሰብሳቢዎቹ በ2002 ለአራተኛ ጊዜ የሚካሄደው ክልላዊና ብሔራዊ ምርጫ በየመኖሪያ አካባቢያቸው ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሠላማዊ እንዲሆን የዜግነት ግዴታቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል ሲል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡
በስብሰባው ከሁሉም ክልሎች፣ ከሁለት ከተሞች አስተዳደርና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡት ሴቶች በአገሪቱ በመካሄድ ላይ ባለው አጠቃላይ የሴቶች ትምህርት እንቅስቃሴ፣ልማትና የአመራር ሚና በሚሉ ርዕሶች ተወያይተዋል።
ሥ 6.30መ10.00 ሪ 1.05 ያ10.37 ተ 12፡05 ጠሰድ 5፡35 ጥከ
---END---