ጎንደር, የካቲት 2 ቀን 2002 (ጎንደር) - ሰሜን ጎንደር ውስጥ በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ በ274 ሚሊዮን ብር ወጪ የ112 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አስታወቁ።
የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳኘው ገብሬ ሰሞኑን ለኢዜአ. እንደገለጹት መንግስት በመደበው በጀት በ2000 ግንባታው የተጀመረው
ይኽው መንገድ የወረዳው ማዕከል የሆነቺውን የአብርሃጅራ ከተማ ከአብደራፊና ከሰሮቃ ከተሞች ጋር የሚያገናኝ መሆኑን ተናግረዋል።
የመንገዱ መሰራት በወረዳው በባለሀብቶችና በአርሶ አደሮች የሚለማውን የጥጥና የሰሊጥ ምርት በቀላሉ ለገበያ በማቅረብ ፣የሀገሪቱን የውጪ ምንዛሬ ለማሳደግ የሚረዳ መሆኑን ገልጠዋል።
እንዲሁም የወረዳው ህዝብ ምቹ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
የወረዳው ህዝብ በክረምት ወራት የትራንስፖርት አገልግሎት ስለማያገኝ ለበርካታ ዓመታት ሲቸገር መቆየቱን አስታውሰው፣መንግስት ለመንገዱ ስራ ትኩረት በመስጠቱ ህዝቡ መደሰቱን ተናግረዋል።
መንገዱ በዚህ ዓመት ተጠናቆ በመጪው ዓመት የተሟላ አገልገሎት መሰጠት ይጀምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመው፣ የወረዳው አስተዳደር ለመንገድ ስራው ድርጅት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።
አንዳንድ የወረዳው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት መንግስት ለወረዳው ልማት መፋጠን ባለፉት ዓመታት የተለያየ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውቀው ፣ የመንገዱ መሰራት ህዝቡ ለዘመናት በትራንስፖርት ዕጦት ሳቢያ ይደርስበት የነበረውን እንግልት
እንደሚያስቀር አመልክተዋል።
ሪፖ/ኤዲ/ 6.30-6.40 ጠሰድ=0.10 ጥ/ከፍ/
---END---