የአፍሪካ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴሮችና የኤች አይ ቪ ኮሚሽኖች በስነተዋልዶ ጤናና መብቶች ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት ይገባቸዋል፡-ፕሬዝዳንት ግርማ
አዲስ አበባ, የካቲት 2 ቀን 2002 (አዲስ አበባ) - የስነተዋልዶ ጤናን ከኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከል ስትራቴጂ ጋር ለማስተሳሰር የአፍሪካ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴሮችና የኤች አይ ቪ ኤድስ ኮሚሽኖች በስነተዋልዶ ጤናና መብቶች ላይ ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንደሚገባቸው የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት አስታወቁ።

ከየካቲት 1 ቀን እስከ 5 ቀን 2002 ዓ/ም ድረስ የሚቆየው 4ኛው የአፍሪካ የስነተዋልዶ ጤናና የቤተሰብ ምጣኔ መብቶች ጉባዔ ትናንት አዲስ አበባ ውስጥ በይፋ ተከፍቷል።

ጉባዔውን በንግግር የከፈቱት ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የስነተዋልዶ ጤና ትምህርት በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ በመካተቱ ወጣቶች ተጠቃሚ እንሆኑ አስችሏቸዋል።

ዓለም አቀፉን ማዕቀፍ ለማረጋገጥ በተለይ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ሲቪል ማህበረሰብ፣ የግል ድርጅቶች፣ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የልማት ደጋፊዎች መተባበር ይገባቸዋል ብለዋል።

ሕብረተሰቡን ስለ ስነተዋልዶ ጤናና ኤች አይ ቪ ኤድስ ለማሳወቅ መንግስታት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በቅርበት መሥራት እንዳለባቸውም ፕሬዝዳንት ግርማ ተናግረዋል።

በገጠር አካባቢዎች የሚኖሩ ደሃ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለስነተዋልዶ ጤና ችግሮች ተጋላጭ በመሆናቸው የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎቱን ለማዳረስ መሠረተ ልማትን መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል።

የሚሌኒየሙን የልማት ግቦችና የዓለም አቀፍ ስነ-ሕዝብና ልማት ኮንፈረንስን ለመደገፍና ለማሳካት እንዲሁም የመንግስትን ተነሳሽነት ለመደገፍና የፆታና ስነ-ተዋልዶ ጤና እንዴት ከኤች አይ ቪ ኤድስ ማዕቀፍ ጋር ማስተሳሰር በሚቻልበት ላይ ጉባዔው በጥልቅ መምከር እንደሚገባው ተናግረዋል።

እንዲሁም የሚሌኒየም የልማት ግቦችና የዓለም አቀፍ ስነ-ሕዝብና ልማት ኮንፈረንስን ለማሳካት እንዴት ሀብትን ማዘዋወር እንደሚቻል ጉባዔው በስፋት መወያየት እንዳለበትም ፕሬዝዳንት ግርማ አሳስበዋል።

የኢፌዲሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም በበኩላቸው የጉባዔው ዓላማ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2004 በጆሃንስበርግ፣ በ2006 በናይሮቢና በ2008 በአቡጃ የስነተዋልዶ ጤናና መብቶች ላይ የተላለፈው ውሳኔና አህጉራዊ ውይይቶችን ማስቀጠል ነው ብለዋል።

የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎትን ከኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከል ጋር በፍጥነት ለማስተሳሰር በኢትዮጵያ መሠረታዊ የጤና አገልግሎትን ለማረጋገጥ 30 ሺህ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ሰልጥነው ሕብረተሰቡን በማገልገል ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

በሚሌኒየም የልማት ግቦች ውስጥ በተራ ቁጥር 4፣ 5ና 6 ላይ ከተቀመጡት የጤና ግቦች ጋር የስነ-ተዋልዶ ጤና መብቶችን ለማስተሳሰር ጉባዔው ወቅታዊና የተለየ እንደሆነም ተናግረዋል።

በቀሩት አምስት ዓመታት ሁሉም የአፍሪካ አገራት በሚሌኒየም የልማት ግቦች በተራ ቁጥር 4ና 5 ላይ የተቀመጡትን የጤና ግቦች ለማሳካት በጋራ ተባብረው በመሥራት ለውጥ ማምጣት እንዳለባቸው ዶክተር ቴዎድሮስ ገልጸዋል።

በጉባዔው ላይ የአፍሪካ አገራት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴሮችና የኤች አይ ቪ ኤድስ ኮሚሽኖችና የዓለም አቀፍ የጤና ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል።

ለአምስት ቀናት በሚቆየው ጉባዔ ላይ በባህላዊ፣ ጎጂና ልማዳዊ ድርጊቶች ላይም ውይይት ይደረጋል።

ሪ 4፡00 ያ 7፡00 ኤ7፡52

---END---

Headlines
ኢትዮጵያ 18 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር አዲስ የውጭ እርዳታና ብድር አግኝታለች
የአፍሪካ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴሮችና የኤች አይ ቪ ኮሚሽኖች በስነተዋልዶ ጤናና መብቶች ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት ይገባቸዋል፡-ፕሬዝዳንት ግርማ
(c) The Ethiopian News Agency